ዋዜማ ራዲዮ- የደራሲና ሐያሲ አለማየሁ ገላጋይ አዲስ የልቦለድ ሥራ ዛሬ ረፋድ ላይ (ረቡዕ) ለአንባቢ ደርሷል፡፡ “በፍቅር ሥም” የሚል ርዕስ የተሰጠው ይህ ሥራው መታሰቢያ የተደረገው “በሕይወትና በጥበብ ጉዞ ሞት መነጠልን እስኪያሳርፍ ድረስ” አብረውት ለነበሩት ለሀያሲ አብደላ እዝራና ለደራሲ አስማማው ኃይሉ (አያ ሻረው) ነው፡፡
መጽሐፉ በቅርጹ ያልተለመደ አካሄድን የሚከተል ሲኾን በክፍል አንድ ብቻ በተቀራራቢ ርዕስ 20 ንዑስ ትረካዎችን የያዘ ኾኖ ተሰናድቷል፡፡ ሁሉም ርዕሶች የሚጀምሩት እኔ እከሌና እከሌ በሚል አካሂድ ነው፡፡ እኔ፣ ጠቢቡ ሰለሞንና አባቱ፣ እኔ እናቴና የአባቴ ፉርጎ፣ እኔ ኦፋ አቡኮ እና አባ ኪሮስ፣ እኔ ሁኔታዬና ወጥ የመሆን ሽሽት…ወዘተ….እያለ እስከ 110 ገጽ ይሄዳል፡፡
ክፍል ሁለት በተመሳሳይ መልኩ 18 ተከታታይ ትረካዎች ሲኖሩ ሁሉም መታሰቢያ የተደረጉት በሸጎሌው ጥይት ፋብሪካ ፍንዳታ ሕይወታቸውን ላጡ ዜጎች ነው፡፡
የዓለማየሁ ገላጋይ በፍቅር ስም የተሰኘው ይህ 5ኛ የልቦለድ ሥራው 216 ገጾች ሲኖሩት በሄሪቴጅ ማተሚያ ቤት ታትሞ በ71 ብር ዋጋ ነው ለአንባቢ የቀረበው፡፡ ዓለማየሁ ከዚህ ቀደም አጥቢያ፣ ቅበላ፣ የብርሃን ፈለጎች እና ወሪሳ የተሰኙ የፈጠራ ሥራዎችን ለአንባቢ አድርሷል፡፡ ይህ አምስተኛ ሥራውን ለአንባቢ እስኪያቀርብ ድረስ በእስር ላይ የሚገኘው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ያሳትማቸው በነበሩ መጽሔትና ጋዜጦች መንግሥትን የሚሸነቁጡ ተከታታይ መራር ወጎችን በማቅረብ ቆይቷል፡፡