Sibhat Nega
Sibhat Nega
  • እኔ የትግራይ ሕዝብን አንተን የመሰለ የለም ካልኩት ገድየዋለሁ ማለት ነው፡፡
  • አሁን ያለንበት ሁኔታ ፈታኝ ነው፤ ከዘጠና ሰባቱ የአሁን ይከፋል፡፡
  • መታደስ ማለት ከእንግዲህ ወዲህ ተሀድሶ የለም ማለት ነው፡፡
  • ብሔራዊ መግባባት የሚባለው ቃሉም ብዙ አይገባኝም፡፡
  • ኢህአዴግ ችግር ላይ ያሉ ግለሰቦችን ለማዳን ብሎ የሐገር ክደት አይፈጽምም፡፡
  • ኢህአዴግ ችግሮችን ከመፍታት ዉጭ አማራጭ የለውም፤ ይሄን ካላደረገ ግን በአንድ ሀገር ተሰብስቦ የመኖር ነገር አስቸጋሪ ይሆናል፡፡
  • “የትግራይ ሕዝብ ኦሮሚያ ዉስጥ የተሰበሰበን ገንዘብ ላኩልኝ ይላል ወይ…?

ዋዜማ ራዲዮ- አዲስ ዘመን ጋዜጣ በዛሬው ዕትሙ የፊት ገፅ ዘገባው “አቶ ስብሐት ነጋ ይናገራሉ!” በሚል ርዕስ ከዚህ ጋዜጣ ባህሪ ወጣ ባለ መልኩ ጠጠር ካሉ ጥያቄዎች ጋር ነባሩን ታጋይ አቦይ ስብሐትን ይዞ ወጥቷል፡፡ 

ከኢህአዴግ ነባር አመራሮች ደፈር ያለ ግላዊ አስተያየት በመስጠት የሚታወቁት አቶ ስብሐት ነጋ ዛሬ ረቡዕ ታኅሳስ 26 ከታተመው ዕለታዊው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያለና ጥንቃቄ የተሞላበት የሚመስል አስተያየታቸውን አንጸባርቀዋል፡፡

ቃለ መጠይቁ ከጥልቅ ተሀድሶና አገሪቱ አሁን ካለችበት አጣብቂኝ ጋር በተያያዘ በገጠማት ፈተና ላይ የሚያጠነጥን ቢኾንም የኚህ ጉምቱ ፖለቲከኛ የግል አስተያየት የማይመስሉ፣ መጪ እርምጃዎችን የሚጠቁሙ የሚመስሉና በኢህአዴግ ዉስጥ ያለው አሰላለፍ ወጥና እንከን የለሽ እንዳልሆነ የሚያመላክቱ ነጥቦች ተነስተውበታል፡፡

ጋዜጣው የከፍተኛ አመራሮች እስከዛሬ በሕግ አለመጠየቅ ጉዳይ አንስቶ “ሕዝቡ ግን ይህ እርምጃ ተወስዶ ማየት ይፈልጋል”፣ እርስዎ ምን ይላሉ ብሎ ጠይቋቸው ነበር፡፡ አቦይ ስብሐት ሲመልሱ “ይህ ነገር መቼ ይጀምራል፣ ከማን ይጀምራል የሚለው ጥያቄ ነው ያለኝ እንጂ ኢህአዴግ ተቻችሎ መሄድ የሚያበቃበትን ሥርዓትን ለመገንባት ቆርጧል” ብለዋል፡፡

ጋዜጣው በበኩሉ ይህ የሚኾንበት ቁርጥ ቀንና እነማን ለሕግ እንደሚቀርቡ “እርስዎ የቅርብ መረጃ አለዎት ወይ?” ሲል ጠጠር ያለ ጥያቄ አንስቶላቸው ነበር፡፡

አቦይ ሲመልሱ “እኔ አሁን የቅርብ መረጃ የለኝም”፤ ካሉ በኋላ ኢህአዴግ ይናገራል እንጂ አያደርግም እየተባለ እንደሚታማ ገልጸው አሁን ግን ወደ ተግባር እንደሚገባና ይህን ሲያደርግም ከላይ ከከፍተኛ አመራር እንደሚጀምር ያላቸውን እምነት አስረግጠው ተናግረዋል፡፡

አዲስ ዘመን ጥያቄዉን አጠናክሮ በመቀጠል ” ስለዚህ ቀደም ባሉት ዓመታት ወደ ማረሚያ ቤት የገቡትን ሚኒስትሮች የሚቀላቀል ሚኒስትር ይኖራል ወይ? ሲል መሪ ጥያቄ አንስቶላቸው ነበር፡፡አቦይ ስብሐት ለዚህ ጥያቄ ቀጥተኛ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ተዘዋዋሪና አሻሚ መልስ መስጠትን መርጠዋል፡፡ ” የእነሱም ቢኾን [ቀድመው የታሰሩ ሚኒስትሮች] ሥርዓቱ ሳይስተካከል ነው የሄዱት፡፡ ሰው መልቀምም ብቻውን ዋጋ የለውም፡፡ ኢህአዴግ ያንን የቅጥፈት ሁኔታ የፈጠረውን ስርዓት እስወገደ በምሬት እንደሚሄድበት ነው ያለኝ ግምት” ብለዋል፡፡ ዘመን ጋዜጣ በበኩሉ “ካልሄደበትስ” የሚል አጭር ጥያቄን ያስከተለ ሲኾን አቦይ ስብሐት “ካልሄደበት… ሀገርም ይፈርሳል” ሲሉ ደምድመዋል፡፡

“በአሁን ጊዜ ለሰው ታስቦ ሀገር የሚካድበት ሁኔታ የለም፤ ለግለሰቦችም ተብሎ ተቻችሎ መሄድ አይኖርም፣” ሲሉ ሀገሪቱ ያለችበትን አጣብቂኝ ጊዜ የሚሰጥ እንዳልሆነ ለማንጸባረቅ ሞክረዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አጥፊ የተባሉ ከፍተኛ አመራሮች በሕግ መጠየቅ እንዳለባቸው አበክረው የገለጹ ሲሆን ተቻችሎ መቀጠል ያበቃለት መሆኑን ለማሳየት ሞክረዋል “ኢህአዴግ ለግለሰብ ሲል ሕዝቡን ይከዳል የሚል እምነት የለኝም፡፡ [ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ተጠያቂ ማድረግን] ካልሄደበት አገርንና ሕዝብን መክዳት ነው፤ ኢህአዴግ ይህን ካላደረገ ሕዝብን መክዳት ነው፤ አገር ማፍረስ ነው” ሲሉ ጠንካራ አቋም የሚመስል አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡

ዘመን ጋዜጣ  አቦይን “እንደ አንድ ፖለቲከኛ ወደ ኋላ ሄጄ ባስተካክለው ብለው የሚመኙት ነገር ካለ” ሲል ላነሳላቸው ጥያቄ ” ለመጥፎ ያዋልኩት ጊዜ የለም፤ ለጥሩ ያላዋልኩት ጊዜ ግን አለኝ” የሚል የተዳፈነ መልስ ሰጥተውታል፡፡

አዲሱ ካቢኔ በምሁራን መጥለቅለቁ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ተጠይቀውም ” ትምህርት በራሱ ጸጋ ነው የሚባለው ዉሸት ነው፤ ትምህርት እዳም ሊሆን ይችላል” ሲሉ ዘርዘር ያለ ምላሽ ለጋዜጣው ሰጥተዋል፡፡ ትምህርት እዳ ሊሆን እንደሚችል በምሳሌ ሲያስረዱም “ፕሮፌሰር ኾነው ያን የጨለማና የእልቂት ዘመን ደጉ ዘመን ብለው የሚናፍቁ አሉ” ሲሉ ግለሰብ ላይ ያነጣጠረ የሚመስል አስተያየት ሰጥተዋል፤ አቦይ ስብሔት፡፡

አዲስ ዘመን ከአዲሱ ካቢኔ ጋር የተያያዘ ጥያቄ ሲያነሳ እርስዎ የኢትዮጵያ ፖለቲካ አባት አድርጌ ከማያቸው ሰዎች መካከል አንዱ ነዎት…” በማለት አቦይ ስብሐትን ሊያሞካሻቸው ሲሞክር “አባት ወዘተ የሚለው ይቅርና…ሲሉ አገላለጹን እንዳልወደዱለት ለማሳየት ሞክረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የካቢኔ ለውጥ በሚለው አጠራር እንደማይስማሙ ከዚያ ይልቅ የካቢኔ ማሻሻያ የሚለው የተሻለ እንደሆነ ተከራክረዋል፡፡ በአጠቃላይ “ሰው ማስቀመጥ በራሱ ለውጥ አያመጣም፤በተቋሙ ተጠያቂ ማድረግ እንጂ…ሲሉ በአዲሱን ካቢኔ ለውጥ ይመጣል የሚለውን ድምዳሜ ተችተዋል፡፡

ስለ ብሔራዊ መግባባት የተጠየቁት አቦይ ስብሐት “እኔ ይሄ ብሔራዊ መግባባት የሚባለው ነገር ቃሉም ብዙ አይገባኝም” ካሉ በኋላ ሕገ መንግሥቱም የሚለው አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ እንፈጥራለን ነው የሚለው ሲሉ ከተንደረደሩ በኋላ ይሄ ሁኔታ መሬት ላይ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ “የኦሮሞ ሀብታም የሶማሌ ሀብታም የአማራ ህበታም የትግራይ ሀብታም ወደ ሌላ ክልል ቢሄዱ ወገኖቼ ናቸው ብሎ እኩል ማየት አለ ወይ እኔ አይመስለኝም ” ብለዋል፡፡ “…ካለ ግን ብሔራዊ መግባባት ተፈጥሯል ማለት ነው ብለዋል፡፡

አቦ ስብሐት በብሔር ብሔረሰቦች መሐል ያለን የመተማመን ደረጃ ባመላከተው አስተያየታቸው ” [ይህ ሁሉ]  አንተ ትበልጣለህ የሚል አስተሳሰብ ያመጣብን ጣጣ ነው…ሕዝቡ ማወቅ ያለበት አንዱ ብሔር ሌላውን ሊጨቁን ክፍት ቦታና እድሉ አለ ወይ የሚለውን ነው፡፡” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አክለውም “የትግራይ ሕዝብ ኦሮሚያ ዉስጥ የተሰበሰበን ገንዘብ ላኩልኝ ይላል ወይ…ይሄ በተጨባጭ የለም፤ ሕዝቡ የለም ብሎ ማመን አለበት ብለዋል፡፡” ብለዋል፡፡

ከዚህ አስተያየታቸው ጋር አስከትለው በርካታ አመራሮች ሕዝቡን ራሳቸው እየበደሉት በሌላው እንደሚያላክኩ ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡ “…አንተን የሚመስል የለም እያለ የሚያቆረቁዘው ራሱ መሆኑን ማወቅ አለበት” ብለዋል፡፡….እኔ የትግራይ ሕዝብን የመሰለ የለም ካልኩት ሕዝቡን ገድየዋለሁ ማለት ነው፡፡ ዋናው ጠላቱ ካንተ በላይ የለም ያልኩት እኔ ነኝ…” ሲሉ ለዘመን ጋዜጣ ተናግረዋል፡፡

አዲስ ዘመን ጋዜጣ ይህን ቃለ መጠይቅ ሲጀምር አቦይ ስብሐትን ለምን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሚዲያ እንደራቁ ጠይቋቸው ነበር፡፡ ሲመልሱ እንዲህ ብለዋል፤

” ማንም ሰው በሚዲያ እንዳይናገር የተከለከለበት ነገር የለም፤ እንዳልከው አሁን ረዘም ላለ ጊዜ ከሚዲያ እርቄያለሁ፤ ኢህአዴግ ስህተቶቹን አስቀምጦ ለመፍታት ገበያ/ አደባባይ/ ወጥቷል፡፡ ሕዝብ የሚፈልገው እኔም የምፈልገውንም ነገር እየተናገረ ነው፡፡ ስለዚህ የእኔ መናገር አያስፈልግምና ለዚያ ነው ከሚዲያ የራቅኩት”