ዋዜማ ራዲዮ- በአማራ ክልል በተወሰኑ ቦታዎች ብቻ ቢያንስ 99 ሰዎች በመንግስት ሃይሎች መገደላቸውን አረጋግጫለሁ ሲል የኢትዮጵይ ሰብዓዊ መብቶች ፕሮጀክት ሰኞ ህዳር 19 ቀን 2009 ገለፀ። የሟቾች ቁጥር ከዚህ ሊጨምር እንደሚችል የገለፀው የፕሮጀክቱ ሪፖርት የሟቾችን ስም ዝርዝር በመግለጫው አካቷል።
ሐምሌ 29 ቀን 2008 ዓ.ም ከተከናወነው የባህርዳር ከተማ የተቃውሞ ሰልፍ ጀምሮ የመንግስት ታጣቂ ሃይሎች በወሰዱት እርምጃ ከ 50 በላይ የሚገመቱ ንፁሃን ዜጎች እንደተገደሉ የገለፅው የኢትዮጵይ ሰብዓዊ መብቶች ፕሮጀክት በክልሉ ከሚገኙ አስራ አንድ ዞኖች ስድስቱ ዞኖች የጎላ ተቃውሞ በመንግስት ላይ አድርገዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ፕሮጀክት በመንግስት ታጣቂዎች የተከናወነው ግድያ ጎንደር፣ባህርዳር፣ደብረታቦር፣ፍኖተሠላም፣ ፣ ደብረ ማርቆስ፣ወረታ፣ አዴት፣ ድብረወርቅ፣ ቻግኒ፣ቡሬ፣ ዳንግላ፣አይባ፣ አርማጮህ፣ ዳንሽ፣ በአከር፣ ሻውራ እና ምስራቅ ጎጃምን አካቷል ብሏል።
ማረጋገጥ እና መሰብሰብ ከተቻለው የሟቾች ቁጥር መካከል አብዛኛው ሟቾች የባህርዳር ከተማ ወጣቶች ሲሆኑ ጎንደር እና አርማጮህም እንደዚሁ የግድያው ሰለባው የከፍባቸው ከተሞች ናቸው።
በክልሉ የተቃውሞ ተሳታፊዎች ላይ እርምጃ የወሰዱ የመንግስት ሃይሎች ተጠያቂ እንዲሆኑ ፣ ሰለደረሰውም የሰው ህይወት እልቂት በገለልተኛ ወገን ምርመራ እንዲደረግ እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግስት የመብት ጥያቄ ያነሱ ዜጎችን ከማፈን እና ከግድያ በመቆጠብ ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጥ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ፕሮጀክት ጠይቋል።