ዋዜማ ራዲዮ- የሰሞኑ ኮስተር ያለ ሕዝባዊ ተቃውሞ የአገር ዉስጥ የንግድ እንቅስቃሴ ክፉኛ ሳያሽመደምደው አልቀረም፡፡ ይህን የሚያስረዳ የተፍታታ ጥናት ባይኖርም የአገር ዉስጥ ግብይት ሙቀት መለኪያ የሆነችው መርካቶ ግን ብዙ ትናገራለች፡፡
መርካቶ ባሳለፍነው ቅዳሜ ያልተለመደ ጭርታ ጋርዷት ነበር የዋለችው፡፡ ከከሰዓት በኋላ ብዙ ሱቆች ተዘግተው ነበር፡፡ የአንዳንዶቹ ምክንያት በደፈናው ‹‹ሥራ የለም›› የሚል ቢሆንም የንግዱ መቀዛቀዝ የአገሪቱን አለመረጋጋት ተከትሎ መሆኑን ነጋዴዎቹ እምብዛምም የተረዱት አይመስልም፡፡ በርግጥም አንዳንድ ክስተቶች ይህንኑ የሚያጠናክሩ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በአትክልት ተራ ከወትሮው በተለየ አውራጅና ጫኝ አይሱዙ መኪናዎች በቁጥር አንሰው ታይተዋል፡፡ ተመሳሳይ ሁኔታ በመርካቶዋ ቦንብ ተራም ተስተውሏል፡፡ ‹‹ንግድ መቀዛቀዙን የምታውቀው መርካቶ ዉስጥ መኪና በፍጥነት መንዳት ስትችል ነው፡፡ ተመልከት እንደዚያ አስጨናቂ የነበረው የመኪና መንገድ እንዴት ነጻ እንደሆነ፡፡›› ይላል ትናንትና ከዋዜማ ሪፖርተር ጋር ሐሳብ የተለዋወጠ፣ በብትን ጨርቅ ንግድ ላይ የተሰማራ ጎልማሳ፡፡
‹‹ቦምብ ተራ›› በአመዛኙ የሸቀጣሸቀጥ ግብይትን የሚቆጣጠር ቁልፍ ማዕከል ነው፡፡ ወትሮ የጭነት መኪኖች መፈናፈኛ የማያገኙበት ከመሆኑም ባሻገር ከዕሁድ በስተቀር ከሰኞ እስከ ሰኞ ሁካታና ግርግር የማይለየው የመርካቶ ደማቁ የግብይት ጥግ ነበር፡፡ ከባለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ግን ነገሮች መልካቸውን ቀይረዋል፡፡ ‹‹የክፍለአገር ደንበኞቻችን ሲቀሩ ነው ረብሻ እንዳለ የጠረጠርኩት፡፡›› ይላል የዋዜማ ሪፖርተር ባሳለፍነው ሰኞ ያነጋገረው የሸቀጥ ጅምላ አከፋፋይ፡፡
ባሳለፍነው ቅዳሜና ሰኞ ምንጮቻችን በስልክ ያነጋገሯቸው የመርካቶ ነጋዴዎች የሕዝባዊ ተቃውሞዉን ስፋትና መጠን በውል የተገነዘቡት አይመስሉም፡፡ ‹‹የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ናቸው የረበሹት›› ብለው የሚያስቡት በቁጥር ጥቂት አልነበሩም፡፡ ብዙዎቹ ግን በጎንደር በኩል ረብሻ እንዳለ በጭምጭምታ መስማታቸውን አልካዱም፡፡
የክፍለ አገር ነጋዴዎች አዲስ አበባ ለመምጣት የኦሮሚያ ከተሞችን ማቋረጥ አለባቸው፡፡ በኦሮሚያ አንዳንዳንድ ከተሞች ደግሞ መንገዶች ተዘግተዋል፡፡ የክፍለ አገር ነጋዴዎች መጥተው ካልገዙ ነግዶ መግባት አስቸጋሪ ነው ይላሉ ያነጋገርናቸው ባለሱቆች፡፡ ‹‹ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ አንድም የክፍለ አገር ነጋዴ ዕቃ ከኔ ቤት አልጫነም፡፡ 35 ጌጅ ቆርቆሮ ገዢ በማጣቱ 105 ብር ገብቷል፣ ነገሩ በዚህ ከቀጠለ በጣም ያስፈራል››ይላሉ ሌላ የሕንጻ መሳሪያ ነጋዴ የሆኑ ሰው፡፡
በኮንስትራክሽን ዘርፍም ተመሳሳይ ሁኔታ ይታያል፡፡ አሸዋ በብዛት ከዝዋይ ነው የሚመጣው፡፡ ‹‹‹መኪና ኦሮሚያ ዉስጥ ይቃጠላል ስለሚባል ባለ ሲኖትራኮች ፈርተው ቆመዋል፡፡ ደፋር ሾፌሮች ካልሆኑ ሥራ አይሰሩም፡፡ ርቀው ወደ ክፍለ አገር ለመሄድ አይደፍሩም፡፡ ግንባታ ያለ አሸዋ ደግሞ አስቸጋሪ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ከሰሞኑ የአንድ መኪና አሸዋ ዋጋ ከ7ሺ ብር በአንድ ጊዜ 7500 እና 8ሺ ገብቷል›› ይላል ሐሳቡን ለዋዜማ ያጋራ በአሸዋና ጠጠር ንግድ የተሰማራ ግለሰብ፡፡
አዲስ አበባ
ቅዳሜ ማለዳ ‹‹ወደ ስቴዲየም አካባቢ ረብሻ አለ›› የሚለው ወሬ በአጭር ሰዓት ዉስጥ ነበር የተራባው፡፡ ኾኖም ረብሻው ፖለቲካዊ መልክ እንዳለው የጠረጠረ አልነበረም፡፡ የብዙዎች ግምት ‹‹ቡናና ጊዮርጊስ ጨዋታ ነበራቸው እንዴ?›› ከሚል የዘለለ አልነበረም፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው በአዲስ አበባ እምብርት ደፍሮ ተቃውሞ ለማሰማት ጎዳና የሚወጣ ሰው ይኖራል ተብሎ ባለመገመቱ ነበር፡፡ ረብሻውን ተከትሎ ስቴዲየምና አካባቢው ለአጭር ሰዓት ለትራንስፖርት ዝግ ሆነ፡፡ ሰልፍ ለማድረግ የሞከሩ ወጣቶች በፀጥታ ኃይሎች ቆመጥ በከፍተኛ ሁኔታ የተደበደቡ ሲሆን ከነዚህ ዉስጥ 3 ሰልፈኞች በአካባቢው ሰዎች ቤተዛታ ሆስፒታል ተወስደው ሕክምና ማግኘታቸውን የሆስፒታሉ ሰራተኞች አረጋግጠውልናል፡፡ ኾኖም አንድም የሞት አደጋ አልተመዘገበም፡፡
በቀበሌ መዋቅር የወጣት ሊግ አባላት በአስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠሩ የተወሰነ ሲሆን ብዙ ወጣቶች ግን ለመሰብሰብ ፍቃደኛ ባለመሆናቸው በብዙ ቀበሌዎች የተገኙ አባላት ቁጥር አነስተኛ ሆኗል፡፡ በቀጣይ በየቀበሌው የአካባቢ ነዋሪዎችን በሰላም አስፈላጊነት ዙርያ ለመሰብሰብ እቅድ ተይዟል፡፡ ደንብ አስከባሪዎች ማንኛውንም በአካባቢያቸው የሚስተዋሉ ለየት ያሉ እንቅስቃሴዎች በአስቸኳይ ሪፖርት እንዲያደርጉ ስልክ ቁጥሮች ታድለዋል፡፡ ‹‹ተጨባጭ እንቅስቃሴን ሪፖርት ለሚያደርጉ ልዩ ማበረታቻ ይኖራል ብለውናል›› ይላል ለዋዜማ ቃሉን የሰጠ አብነት አካባቢ የሚኖር ወጣት ፡፡
ከዕሑድ ጀምሮ በፉሪ፣ በአቃቂ ቃሊቲ፣ በጣፎና በለቡ ወደ ከተማ በሌሊት የሚገቡና የሚወጡ መኪኖች እየተፈተሹ ነበር፡፡ በቡድን ሆነው በከተማዋ የሚንቀሳቀሱ ወጣቶች እየታፈኑ ተወስደዋል፡፡ ሌሎች ኪሳቸው እየተበረበረ ተለቀዋል፡፡ የሞባይል ስልክ ከፍታችሁ አሳዩ የተባሉ ወጣቶችም ነበሩ፡፡ በፒያሳ ጣይቱ ፊት ለፊት በሚገኘው የአራዳ ፖሊስ ጣቢያ ቅዳሜ ከሰዓት መፈክር የያዙ በቁጥር ከ10 የማይበልጡ ወጣቶች በፒክ አፕ መኪና እየተጫኑ ወደ ጣቢያው ሲገቡና የያዙት መፈክር በኤግዚቢትነት ሲመዘገብ ታይተዋል፡፡
ቅዳሜና ዕሁድ በተለይ በአዲስ አበባ በሁሉም ዋና ዋና አደባባዮች ፌዴራል ፖሊስ የጫኑ ፒክ አፕ የፖሊስ መኪኖች ከ10-15 የሚሆኑ የፀጥታ ኃይሎችን ይዘው ይታዩ ነበር፡፡ የሬዲዮ መገናኛ የያዙ ፖሊስ አዛዦች መልዕክት ሲለዋወጡ መስማት እንግዳ ነገር አልነበረም፡፡ ከሰኞ ጀምሮ ግን በከተማዋ የሚዘዋወሩ ልዩ ፖሊሶችና ፌዴራል ፖሊሶች በክልሉ ፖሊሶች ተተክተዋል፡፡ ኾኖም በዋና ዋና አደባባዮች አሁንም ከ3-5 ታጣቂ ፌዴራል ፖሊሶች ይታያሉ፡፡
የዋዜማ ሪፖርተሮች በተዘዋወሩባቸው የመገናኛ፣ የሲግናል፣ የጀርመን አደባባይ፣ የአድዋ ድልድይ ሴቶች መታሰቢያ አደባባይ፣ ካዛንቺስ ሱፐርማርኬት አካባቢ፣ ሴንጆሴፍ የኦህዴድ ጽሕፈት ቤት ዙርያ፣ ጥላሁን ገሰሰ መታሰቢያ አደባባይ፣ እንዲሁም በብዙዎቹ ባለኮከብ ሆቴሎች በር ላይ መጠነኛ የፖሊስ ኃይል የሚታይ ሲሆን አሁንም ድረስ ብዙዎቹን የከተማዋን ዋና ዋና አደባባዮች መሳሪያ ያነገቱ፣ የዝናብ ልብስ የለበሱ ታጣቂ ፖሊሶች አልተለይዋቸውም፡፡
ቅዳሜና ዕሁድ በቤተመንግሥት በር ላይ እንዲሁም ከሂልተን ሆቴል ወረድ ብሎ የሚገኘው መስቀለኛ መንገድ አድማ በታኝና ብረት ለበስ ተሸከርካሪዎች በብዛት ይስተዋሉ ነበር፡፡ በፓርላማና በ4 ኪሎ ቤተመንግሥት ዋና መግቢያ ላይ እንዲሁም በግቢ ገብርኤል ታችኛው በር 4 ተመሳሳይ ብረት ለበስ የወታደር ካሚዮኖች ቅዳሜና ዕሁድ ቆመው ታይተዋል፡፡ ከሰኞ ረፋድ ጀምሮ ግን መኪኖቹ ከቦታቸው አልነበሩም፡፡
ቦሌ ሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር ዝቅ ብሎ ጥሩነሽ ዲባባ ከምታሰራው ሕንጻ ማዶ ዎርቤክ ሕንጻ አካባቢ የሚገኘው ድልድይ ወትሮም መጠነኛ የፖሊስ ኃይል በቋሚነት የሚታይበት ሲሆን በአካባቢው የአቶ በረከት ስምኦንን መኖርያን ጨምሮ በርካታ የኤህአዴግ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ቤቶች የሚገኙበት በመሆኑ ይመስላል በተለየ ሁኔታ የተጠናከረ ጥበቃ ሲደረግለት ማስተዋል ችለናል፡፡ በአካባቢው የሚታየው የፖሊስ ኃይል አሁንም በቁጥር ከፍ ያለ እንደሆነ አይቶ መረዳት ይቻላል፡፡
ባሕር ዳር
በተመሳሳይ በባህርዳር ከተማ የነበረውን ሕዝባዊ ሰልፍን ተከትሎ የተፈጠረው ሁከት ከትናንት ጀምሮ ጋብ ያለ ቢመስልም ከተማዋ አሁንም በወታደር እንደታጠረች ነው፡፡ ከሰኞ ወዲህ አንድም የመንግሥትም ሆነ የንግድ ቤቶች ክፍት አልነበሩም፡፡ የክረምት ትምህርት እየሰጡ የነበሩ ትምህርት ቤቶች ላልተወሰነ ጊዜ ትምህርት ማቋረጣቸውን ለወላጆች የገለጹ ሲሆን ቱሪስቶች የሚያዘወትሯቸው ሆቴሎች በሙሉ ለአገልግሎት ዝግ ሆነዋል፡፡
ለሥራና ለጉብኝት በከተማዋ ይገኙ የነበሩ የዉጭ ዜጎች ከተማዋን ለቀው ለመውጣት በከፍተኛ ሩጫ ላይ እንደነበሩ የአይን እማኞች ገልጸዋል፡፡ የከተማዋ እንግዳ የነበረ ሁሉ የአየር ትኬት ለመግዛት ነበር ሩጫው፡፡‹‹ፈረንጆች ሳይሆኑ ለዲያስፖራ በዓል የመጡ ናቸው የሚበዙት›› ይላል ለዋዜማ በስልክ ምላሽ የሰጠ አስጎብኚ፡፡
ወደ ከተማዋ የሚገቡ የጫት ንግድን የሚያሳልጡ ‹‹በራሪ አባዱላዎች›› ሥራ አቁመዋል፡፡ በረብሻው ምክንያት፡፡ በአውቶቡስ ለመመለስ ትኬት ቆርጠው የነበሩ ዜጎች ‹‹በኦሮሚያ ከተሞች አውቶቡስ ያቃጥላሉ›› የሚል ወሬ በመዛመቱ ጉዟቸውን በአየር ለማድረግ ሲጥሩ ተስተውለዋል፡፡ አባይ ባስ ላሊበላ ባስ፣ ስካይ ባስና ሰላም ባስ ወደ ከተማዋ መዳረሻ አገልግሎት በስፋት የሚሰጡ የነበሩ ሲሆን ከረብሻው ቀደም ብሎ የጎንደሩን አመጽ ተከትሎ ሥራቸው ተሸመድምዷል፡፡ ሰላም ባስ ብዙዎቹን አገልግሎቶች አቋርጧል፡፡ አገልግሎት በሚሰጥባቸው መስመሮችም ቢሆን አንድ ታጣቂ አሳፍሮ ነው የሚጓዘው፡፡ ከአዲስ አበባ-ባሕርዳር ከአውቶቡስ ጉዞ በተጨማሪ በቀን 4 ወይም 6 ጊዜ የአውሮፕላን በረራ የሚኖር ሲሆን ዋጋውም 1351 ብር ነው፡፡
በከተማዋ ዉስጥ የትራንስፖርት አገልግሎት ከትናንት ማክሰኞ ጀምሮ በቢሾፍቱ አውቶቡሶች ብቻ የተወሰነ ሲሆን ባጃጅም ሆነ ታክሲዎች ግን በከፊልም ቢሆን ወደ ሥራ አልተመለሱም፡፡ ቢሾፍቱ ባስ ከአባይ ማዶ ወደ ከተማ በአንድ ብር ዋጋ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ተሳፋሪዎች ግን በቁጥር እጅግም ናቸው፡፡ ይህ ዘገባ በሚጠናቀርበት ሰዓት ጥቂት ባጃጆች አገልግሎት ለመስጠት ፈራ ተባ እያሉ ወደ አስፋልት መውጣታቸውን ለመመልከት ችለናል፡፡
የባህርዳር ምሽቶች ከሰልፉ ማግስት ጀምሮ ጤና ርቋቸዋል፡፡ አልፎ አልፎ ተኩስ ይሰማል፡፡ በአመዛኙ ግን ቀኑም ሌሊቱም ጭር ብሎ ነው ያለው፡፡ ሌሊት ሌሊት ብቻ በየቀበሌው የሚዘዋወሩ የደኅንነት ኃይሎች አመጽ ያስተባብራሉ የሚሏቸውን ወጣቶች ‹‹ለጥያቄ ትፈለጋላችሁ›› እያሉ ከቤታቸው የሚወስዱ ሲሆን በተለምዶ ‹‹መስጊድ ቀበሌ 1›› በሚባለው ሰፈር ይህ ሁኔታ ባለፉት ሦስት ቀናት እንደቀጠለ ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡
ከአማራ ፖሊስ ይልቅ ፌዴራል ፖሊሶች በብዛት የሚታዩ ሲሆን ትናንትናና ከትናንት በስቲያ በከፍተኛ ሁኔታ የታጠቁ ፖሊሶች በካሚዮን ተጭነው ሲያልፉ ተስተውለዋል፡፡ ‹‹የታጠቁ ወታደሮች 5-6 ሆነው ይዘዋወራሉ፡፡ ብቻውን የሚንቀሳቀስ ወታደር አንድም አላየሁም›› ይላል አንድ የከተማዋ ነዋሪ፡፡
ድብ አንበሳ ሆቴልና ሌሎች የቱሪስት ማረፊያ በሆኑ ባለኮከብ ሆቴሎች አገልግሎት የቆመ ሲሆን በሆቴሎቹ ያረፉ እንግዶች ወደ ዉጭ መውጣት በመቸገራቸው በተላላኪዎች መስተንግዶ የሚያገኙበት ሁኔታ ለማመቻቸት እየተሞከረ ይገኛል፡፡
የዕሁዱ የባሕር ዳር ሰልፍ በታሪክ ከፍተኛ ተቃውሞ የታየበት ሲሆን እስከ ረፋድ ድረስ በሰላማዊ ሁኔታ ቀጥሎ ነበር፡፡ ሰልፈኛው ጣና አካባቢ ባሕርዳር ወህኒ ቤት ሲደርስ ታሳሪዎቹ የአጋርነት ድምጽ ማሰማታቸውን ተከትሎ ‹‹ፍቷቸው እየተባለ ድንጋይ ወደ ፖሊሶች መወርወር ተጀመረ›› ይላል በሰልፉ ንቁ ታሳትፎ ሲያደርግ የነበረ ወጣት፡፡
ይህን ጊዜ ፖሊሶች ወደ ሰልፈኛው መተኮስ ጀመሩ፡፡ ያም ሆኖ ሰልፉ አልተበተነም፡፡ በከተማዋ የሚገኘው ትልቁ የዳሽን ቢራ መዝናኛ የመሸጉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፖሊሶች ላይ ‹‹ወያኔ ሌባ-ወያኔ ሌባ እያሉ የተወሰኑ ሰልፈኞች ድንጋይ ሲወረውሩባቸው ወታደሮቹ ወደ ሰማይ እየተኮሱ አልፎ አልፎም ወደ ሰልፈኛው መተኮስ ጀመሩ፡፡ ይላል ወጣቱ፡፡ ከሰልፈኞቹ ዉስጥ ወንድሙ የተገደለበት አንድ ወጣት ‹‹ድምጹን ከፍ አድርጎ የተኳሹን ስም እየጠራ አይቼሃለሁ አንተን ሳልገድል አልሞትም፣ አይቼሃለሁ፣ አይቼሃለሁ›› እያለ ይጮኽና ያለቅስ ነበር፡፡
‹‹በአሁኑ ሰዓት የወያኔ ፖሊሶች ሁሉም ቦታ ላይ ነው ያሉት፡፡ እኔ ለምሳሌ አባይ ድልድይ ሥር ትንሽዬ ረግረጋማ ቦታ አለች፡፡ እዛ ዉስጥ ወያኔዎቹ መሽገው አይቻለሁ፡፡›› ይላል ሌላ የከተማዋ ነዋሪ፡፡ ይህ ዘገባ በተጠናቀረበት የረቡዕ ምሽት በመላዉ ባሕርዳር መብራት ሙሉ በሙሉ ጠፍቶ ነበር፡፡