በድርቅ ክፉኛ የተጠቁ ወረዳዎች ቁጥር በታህሳስ ወር ከነበረው ማሻቀቡን ከተባበሩት መንግስታት የእርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ የወጣ ሪፖርት አመለከተ፡፡ ትላንት ሚያዝያ 4 የወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው ድርቅ ካጠቃቸው ወረዳዎች ውስጥ ቅድሚያ ትኩረት ሊያገኙ ይገባሉ በሚል በታህሳስ ወር ከተለዩት 186 ወረዳዎች በተጨማሪ 33 ያህል ወረዳዎች በመጋቢት ወር ተደምረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ካሉ 700 ወረዳዎች ግድም ገሚሱ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው በታህሳስ ወር የወጣው የመንግስትና ለጋሾች የጋራ የሰብዓዊ እርዳታ ሰነድ አሳውቆ ነበር፡፡ በሰነዱ የተጠቀሰው የ429 ወረዳዎች ቁጥር በመጋቢት ወር ወደ 443 ከፍ ማለቱን የማስተባበሪያ ቢሮው ሪፖርት ያሳያል፡፡
መንግስትና ለጋሾች ለእርዳታ ክፍፍል ይመቻቸው ዘንድ ወረዳዎቹን በችግራቸው ጥልቀት መጠን በሶስት ምድብ ይከፋፍሏቸዋል፡፡ ወረዳዎቹ ከሚከፋፈሉባቸው መስፈርቶች መካከል ያለባቸው በምግብ ራስን ያለመቻል ችግር፣ በምግብ እጥረት የተጎዱ ሰዎች መጠን፣ ወደ መመገቢያ ፕሮግራሞች የሚገቡ ተጠቃሚዎች መጨመር እና መቀነስ ይጠቀሳሉ።
በመጀመሪያው ምድብ የሚገኙ ወረዳዎች አስቸኳይ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው የሚባሉ ሲሆን በመጋቢት ወር ቁጥራቸው 219 መድረሱን የማስተባበሪያ ቢሮው ሪፖርት ይጠቁማል። ከታህሳስ እስከ መጋቢት በሁለተኛው ምድብ የነበሩ ወረዳዎች በ7 ቀንሰው 147 መሆናቸውን እና በሶስተኛ ምድብ ውስጥ የነበሩ ወረዳዎች ቁጥር ከ89 ወደ 77 መውረዱን ሪፖርቱ ያብራራል።