ዋዜማ ራዲዮ- የኢህአዴግ “ራስ” እንደሆኑ የሚታሰቡት ነባር ታጋይና አመራር አቶ በረከት ስምኦን ለአመታት ይኖሩበት የነበረው ቤት ከሰሞኑ ለህጋዊ ባለቤቱ እንዲመልሱ ሆነዋል፡፡ የቤቱ ባለቤት የዛሬ 16 ዓመት ገደማ ቤቱ አላግባብ የተወረሰባቸው ስለሆነ እንዲመለስላቸው የኢትዮጵያ ፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ወስኖላቸው ነበር፡፡ ኾኖም ይህን ለማስፈጸም የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ ዛሬ ነገ ሲል ቆይቶ ከ16 ዓመታት በኋላ ስሞኑንዉሳኔውን ተግባራዊ ማድረጉን የዋዜማ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
ቤቱ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 17 በቀድሞ አጠራር ደግሞ ቀበሌ 19 የሚገኝ ሲሆን በቤት ቁጥሩ 119 ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ በልዩ ጌት የተሠራ ዉብ የብሎኬት አጥር ያለውና ከሜሪዲያን ሆቴል ወደ አትላስ በሚያሾልክ የዉስጥ ለውስጥ አስፋልት መንገድ በስተቀኝ የሚገኘው ይህ መኖርያ ቤት ከአቶ በረከት ቀደም ብሎ ለተወሰኑ ዓመታት የቀድሞው ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ጻድቃን ገብረትንሳይ መኖርያ ሆኖ አገልግሏል፡፡ ጄኔራሉ ከዚህ ቤት ብዙም ሳይርቅ ቦሌ መድኃኒዓለም ከቢር ጋርደን ጀርባ ባለ ስፍራ አንድ ፎቅ ቤት ሰርተው ለአሜሪካን ኤምባሲ አከራይተው ይገኛሉ፡፡ ጄኔራል ጻድቃን በተለይ ወደ ንግዱ ዓለም ከገቡ በኋላ ሌሎች በርከት ያሉ መኖርያ ቤቶችንም ገንብተው በባለቤትነት ያስተዳድራሉ፡፡
የአቶ በረከት ስምኦን መኖርያ ሆኖ የቆየው ግቢ ዉጫዊ ክፍሉ ከድንጋይ የተሠራ ሲሆን ለዐይን የማይከብድ ዉብ ቪላ በግቢው መሐል ላይ ሰፍሮ ይታያል፡፡ ምንም እንኳ ባለ አንድ ፎቅ ቤት ቢሆንም ከዉጭ ዕይታ ግን ፎቅ የማይመስል ባለ አራት ማዕዘን ቅርጽ ያለው ገዘፍ ያለ መኖርያ ቤት ነው፡፡ ከቤቱ ባሻገር ዋናውን ቤት የሚከብ ሰፊ የአረንጓዴ ቦታ ሽፋን ያለው ሲሆን ግቢው በግምት ሁለት ሺ ካሬ ሜትር እስኩዌር የሚሸፍን ነው፡፡
ቤቱ ከአዋጅ ዉጭ እንደተወረሰባቸውና አሁን ግን እንዲመለስላቸው ለፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ ያመለከቱን የቤቱ ቀደምት ባለቤት አቶ መሐሪ ተወልደ ብርሃን ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ አቤቱታቸው ሰሚ እንዲያገኝ የቤቶች ኤጀንሲን ወትውተዋል፡፡ የቤቶች ኤጀንሲ በበኩሉ ካለፈው ዓመት ጀምሮ የፍርድ ቤት ዉሳኔውን ለማስፈጸም ጊዜ ይሰጠኝ ሲል ቆይቶ ነበር፡፡ ይህም የሆነው ቤቱ ዉስጥ ከፍተኛ ባለሥልጣን እየኖሩበት ስለሆነና እርሳቸውን የሚመጥን ቦታ እስኪገኝ ጊዜ በማስፈለጉ እንደሆነ ሲገልጽ ነበር፡፡ ያም ኾኖ አቶ በረከት ስምኦን ቤቱ በፍርድ ቤት እንዲመለስ ከተወሰነ ወደ ሌላ ቤት ለመዛወር ረዥም ጊዜ መውሰድ አያሻም በማለት ተለዋጭ ቤት በአስቸኳይ እንዲዘጋጅላቸው ሲጠይቁ እንደነበር ተገልጧል፡፡
ይህንኑ ጥያቄያቸውን መሠረት በማድረግ መኖርያ ቤቱ ለአቶ መሐሪ እንዲመለስ ሆኗል፡፡
አቶ በረከት መልካም የሚባሉ ጎረቤት እንደነበሩ ይወሳል፡፡ ለበዓላትም ሆነ ማናቸውም ዝግጅቶች በጎረቤቶቻቸው እንዲገኙ ሲጠሩ ያለምንም ማቅማማት ይታደሙ እንደነበር ለረዥም ጊዜ የተጎራበቷቸው የአካባቢው ነዋሪዎች በበጎ ያነሷቸዋል፡፡
ቤቱ ከረዥም ዓመታት በኋላ የተመለሰላቸው አቶ መሐሪ በኮንስትራክሽንና በዉኃ ቁፋሮ ሥራ የተሠማሩ ከፍተኛ ባለሐብት ናቸው፡፡