Addis Ababa City Hall, head of the adminstration
Addis Ababa City Hall, head of the adminstration
  • ክስተቱ በከተማው የመሬት ሊዝ ታሪክ የመጀመርያው ነው

ዋዜማ ራዲዮ- በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽሕፈት ቤት ለ23ኛ ዙር ካወጣቸው በርካታ የጨረታ ቦታዎች ዉስጥ በዛሬው ዕለት (ሐሞስ) ዉጤታቸው የተገለጹ 21 ቦታዎች በተጫራች መጓደል ሊሰረዙ ችለዋል፡፡ በከተማዋ የሊዝ ታሪክ ይህን ያህል ቁጥር ያለው ቦታ ተጫራች ሲያጣ ለመጀመርያ ጊዜ ነው ተብሏል፡፡

በቦሌ፣ በየካ፣ በኮልፌ ቀራንዮ፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶና በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተሞች በተመላከቱ አንድ መቶ ሃያ አራት ቁልፍ ቦታዎችን በሊዝ ደንብ ለአልሚዎች ለማስተላለፍ ግልጽ ጨረታ የወጣው ባለፈው ዓመት መገባደጃ ላይ ነበር፡፡ ከተገባደደው ዓመት የነሐሴ ወር መጨረሻ ጀምሮ በነበሩ ተከታታይ 13 ቀናት ያህል የጨረታ ሰነድ ሲሸጥ ከርሞ ነበር፡፡ የጨረታ ሰነዱን በርካታ ባለሀብቶች እንደገዙ ቢገለጽም ሁኔታዎች ከወትሮው ተመሳሳይ እንዳልነበሩ ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡ በማዘጋጃ ቤት የለማ መሬት ማስተላለፍ ቢሮ አካባቢ በተለየ ሁኔታ መቀዛቀዝ እንደበር ለሊዝ መሬት ግብይት ቅርብ የሆኑ ሰዎች በሳምንቱ መጀመርያ ላይ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ ኾኖም ከስካዛሬ የሊዝ ግብይት ልምድ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከሚታየው የተጋነነ የመሬት ፍላጎት አንጻር ሃያ አንድ ቦታዎች ገዢ ያጣሉ የሚል ግምት በማንም ልቦና ላይ ያድራል ተብሎ አይታመንም፡፡

ተጫራቾች የጨረታ መልስ ማቅረቢያ ሰነድ፣ ሲፒኦና ማንነታቸውን የሚገለፁ ሰነዶችን በኤንቨሎፕ በማሸግ ለዚሁ በተዘጋጀ ሳጥን ዉስጥ ማስገባት የጀመሩት ከሦስት ቀን በፊት ባሳለፍነው ሰኞ ሲሆን ይህም እስከ ምሽቱ 11 ሰዓት ድረስ ዘልቆ ነበር፡፡ የጨረታ ሰዓት መጠናቀቁን ተከትሎም የጨረታ ማስገቢያ ሳጥኖቹ በክልሉ የጥበቃ አባላት ሲጠበቁ ነበር፡፡ ከ11 ሰዓት በኋላ የጨረታ ዉጤት ከማክሰኞ ጀምሮ እንደሚገለጽ ተነግሮ ተጫራቾቹ በአዲስ አበባ ቴአትርና ባሕል አዳራሽ በነገታው እንዲገኙ ጥሪ ቀርቦላቸው ተበትነዋል፡፡

ማክሰኞ ከጠዋቱ 3 ሰዓት ጀምሮ ጥቂት ባለሐብቶችና ወኪሎቻቸው የጨረታውን ዉጤት ለመከታተል የተገኙ ሲሆን በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 (ሰሚት አካባቢ) እና ወረዳ 11 (ቦሌ ለሚ አካባቢ) ለውድድር ቀርበው የነበሩ 31 ቦታዎች ዉጤት ይፋ ሆኗል፡፡ ብዙዎቹ ቦታዎች በአማካይ በካሬ 10ሺ ብር ቀርቦባቸው ተጠናቀዋል፡፡ በቀጣዩ ቀን ማለትም ማክሰኞ መስከረም 10 ላይ በወረዳ 10 ልዩ ስሙ አያት ፀበል አካባቢ ለጨረታ ቀርበው የነበሩ 33 ቦታዎች ዉጤት ይፋ የተደረገ ሲሆን ለቦታዎቹ የቀረቡ ዋጋዎች ከሌሎች ዙሮች አንጻር የተረጋጋ የሚባል እንደነበር እማኞች ይገልጻሉ፡፡ አብዛኛዎቹ ኪስ ቦታዎች ከ9ሺ እስከ 14ሺ ብር ለካሬ የቀረበባቸው ሲሆን እንደወትሮው የተጋነነ አንድም ዋጋ እንዳልተሰማ ጨረታውን የተከታተሉ ይገለጻሉ፡፡

የተለየ ክስተት ያጋጠመው ግን ዛሬ ሐሙስ መስከረም 12 ነበር፡፡ ከጠዋቱ 3 ሰዓት ጀምሮ ለጨረታ ዉጤት ኤንቨሎፓቸው የተከፈቱት 41 ቦታዎች ሲሆኑ ሁሉም በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1፣ ወረዳ 4 እና ወረዳ 9 የሚገኙ ኪስ ቦታዎች ነበሩ፡፡ የብዙዎቹ አገልግሎት ቅይጥ በሚል የተገለጸ ሲሆን ይህም ለመኖርያና ለቢዝነስ አገልግሎት የታለሙ እንደሆኑ አመላካች ነው፡፡ ቀሪዎቹ ቦታዎች ግዙፍ የገበያ ማዕከል መስሪያ እንዲሆ የቀረቡ ሰፋፊ ቦታዎች ነበሩ፡፡ ኾኖም ከነዚህ በሦስት የተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ 40 ቦታዎች ዉስጥ ተጫራች ማግኘት የቻሉት አስራ ዘጠኙ ብቻ መሆናቸው አነጋጋሪ ክስተት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ በአዲስ አበባ የሊዝ ታሪክ ተጫራች በዝቶ እንጂ ተጫራች ጠፍቶ አያውቅም ነበር፡፡

“የሊዝ ዉጤት ተገልጾ ያበቃው ከምሳ ሰዓት በፊት ቀደም ብሎ ነው” ይላሉ በሕጋዊ የተጫራች ወኪልነት የጨረታውን ዉጤት ሲከታተሉ የነበሩ ግለሰብ የጉዳዩን አስገራሚነት ለመግለጽ፡፡ የጨረታ ሳጥን አንድ ጊዜ ከተከፈተ ሳይጠናቀቅ መዝጋት ስለማይቻል ወትሮ የጨረታ ዉጤት ሲገለጽ እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት የሚቆይበት ጊዜ የነበረ ሲሆን በዚህ ዙር ከምሳ ሰዓት በፊት ዉጤት ተገልጾ መጠናቀቁ አስገራሚ ሆኗል፡፡ ከቀረቡት ቦታዎች ከግማሽ በላዩ ተጫራች በማጣታቸው በግማሽ ቀን ተጫራች ሊበተን ሆኗል፡፡ ይህም በአዲስ አበባ የሊዝ ጨረታ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ የሆነ ነው፡፡

ጨረታው ከሌላው ጊዜ የተቀዛቀዘ ለመሆኑ ተጨማሪ ማስረጃ የሚያቀርቡት እኚህ የተጫራች ህጋዊ ወኪል ለቦታዎቹ የቀረቡ ዋጋዎችን በመጥቀስ ነው፡፡ ለምሳሌ አቶ ክብረአብ የተባሉ ግለሰብ በ2222 ብር 326 ካሬ ቦታን ማሸነፍ ችለዋል፡፡ ይህ ዋጋ ባለፉት ጥቂት አመታት ዉስጥ ለሊዝ ቦታ የቀረበ እጅግ ዝቅተኛ ዋጋ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

በዚሁ ክፍለ ከተማ አቶ ዳዊት ኪዳኔ የተባሉ ባለሀብት ለ250 ካሬ ቦታ እስራ አምስት ሺ አንድ መቶ ብር እንዲሁም አቶ ዘላለም እሸቱ ለ550 ካሬ ቦታ 15ሺ 555 ብር በመስጠት ለዙሩ ዉድ የሚባል ዋጋን በማቅረብ አሸንፈዋል፡፡

አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በአመዛኙ ለኑሮ ምቹ ተደርጎ ስለማይታሰብና የኢንደስትሪ ዞን ነው ስለሚባል በብዙ ግለሰቦች ዘንድ ለመኖርያ ተመራጭ አይደለም፡፡ ይህም ለመኖርያ ቤት ቦታ የሚፈልጉ ባለሀብቶች ዝቅተኛ ዋጋ እንዲሰጡ ያደርጋቸዋል፡፡ ኾኖም በዚህ ዙር በከፍለ ከተማው ከቀረቡት ቦታዎች አብዛኛዎቹ ለቢዝነስና ለቅይጥ አገልግሎት የሚዉሉ ሆነው ሳለ እንዴት በቂ ተጫራች ላይኖራቸው ቻለ የሚለው ብዙዎችን እያነጋገረ ነው፡፡ በሊዝ ጨረታ ሕግ አንድ ቦታ 3 የሚሆኑ ተጫራቾች ካልተሳተፉበት ጨረታው ይሰረዛል፡፡

ነገሩ አጋጣሚ ነው የሚሉ እንዳሉ ሁሉ ለሊዝ ግብይት ቅርብ የሆኑ ታዛቢዎች ክስተቱን ከወቅታዊው የአገሪቱ አለመረጋጋት ጋር ያያይዙታል፡፡ “አልሚዎች እንኳን አዲስ መሬት በውድ ዋጋ ሊወስዱ ይቅርና የሰበሰቡትንም እየሸጡ ነው፡፡ የአገሪቱ መጻኢ እድል አስጨናቂ ሆኗል፡፡ ከፍተኛ ባለሐብቶች እኮ አንድ እግራቸው ዉጭ አገር አድርገው ነው እየተንቀሳቀሱ ያሉት” ይላሉ የዋዜማ ሪፖርተር ያናገራቸው የተጫራች ወኪል፡፡ ምናልባት የ23ኛው ዙር የተጫራቾች መመናመን ከዚህ ጋር የሚያያዝ እንደሆነ የሚገምቱ ታዛቢዎች በርከት ያሉ ናቸው፡፡

የጨረታ ዉጤቱን የመግለጹ ሂደት በነገው ዕለት ቀጥሎ ይውላል፡፡ ከማለዳው 3 ሰዓት ጀምሮ በአዲስ አበባ ባሕልና ቴአትር አዳራሽ ዉጤታቸው ይገለጻል ተብሎ የሚገመቱት በየካ፣ በኮልፌ ቀራንዮና በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተሞች የሚገኙ ቀሪ ቦታዎች ናቸው፡፡

በተለይም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ልዩ ስሙ ሳርቤት ገብርኤል አካባቢ የወጡት ሦስት ቦታዎች የከፍተኛ ባለሐብቶችን ትኩረት ይስባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከ400 እስከ 500 ካሬ ስፋት ያላቸው እነዚህ 3 ቦታዎች የሚገኙት ከአፍሪካ ሕብረት ዋና ጸሐፊ መኖርያ ቤት ጀርባ መሆኑ እጅግ ከፍተኛ ዋና ሊያስገኝላቸው እንደሚችል ተገምቷል፡፡