Ethiopia Hotel-FILE
Ethiopia Hotel-FILE

ዋዜማ ራዲዮ-ከብሔራዊ ቴአትር ፊትለፊት የሚገኘውና ቀድሞ የበጎ አድራጎት ሕንጻ በመባል የሚታወቀው ታሪካዊው ሕንጻን ለማፍረስ እንዲያስችል ተከራዮች በአንድ ወር ጊዜ ዉስጥ ለኪራይ ቤቶች አስተዳደር ቦታውን አስረክበው እንዲወጡ ታዘዋል፡፡

በርካታ ሱቆችና አገልግሎት መስጫዎችን ይዞ የነበረው ይህ ሕንጻ ታሪካዊ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ላለፉት ሁለት አመታት እንዳይፈርስ በርካታ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ ኾኖም ለልማት ጥያቄዎች ላይ አልደራደርም የሚል አቋም በተደጋጋሚ የሚያንጸባርቀው የድሪባ ኩማ አስተዳደር ቦታዉን ሙሉ በሙሉ አፍርሶ አቶ በላይነህ ክንዴ ለተባሉ ባለሀብት ለማስተላለፍ ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀ ታውቋል፡፡

አቶ በላይነህ ክንዴ በዋናነት በሰሊጥ ንግድና ትራንስፖርት ላይ የተሰማሩ የከበሩ ባለሀብት ሲሆኑ ከስድስት ዓመታት በፊት ከያኔው የፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ እጅግ ዝቅተኛ በሚባል ዋጋ ኢትዮጵያ ሆቴልን መግዛታቸው ይታወቃል፡፡

በወቅቱ ኢትዮጵያ ሆቴልን ባለሀብቱ የገዙት በ92 ሚሊዮን ብር ብቻ ሲሆን አሁን በዚህ ዋጋ የሚሸጥ በከተማው ዳርቻ የሚገኝ ሰፊ መዝናኛ እንኳ ለማግኘት አዳጋች ነው፡፡

ኢትዮጵያ ሆቴል 110 ክፍሎች ሲኖሩት ከዚህ ቀደም የሦስት ኮከብ ደረጃ የነበረናውና በአዲሱ የሆቴሎች ደረጃ ግን ወደ አንድ ኮከብ ሆቴልነት የወረደ በከተማዋ እምብርት የሚገኝ ነው፡፡ ሆቴሉ ከሚሰጠው አገልግሎት ይልቅ የሚገኝበት ሁነኛ ቦታ በተገልጋዮች ተመራጭ ያደርገዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሆቴሉ የተገነባው ከ55 ዓመታት በፊት በንጉሡ ዘመን እንደሆነና ለያኔው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንግዶች ማረፊያ እንዲሆን ቀን ተሌት እየተገነባ ቆይቶ በአስቸኳይ እንዲደርስ የተደረገ ሆቴል እንደነበር ይነገራል፡፡

አሁን እንዲፈርስ የተወሰነበት የበጎ አድራጎት ሕንጻ ኢትዮጵያ ሆቴልን ተጎራብቶ የሚገኝና በርካታ የንግድና አገልግሎት መስጫዎች በስሩ ያቀፈ ነው፡፡ ቀድሞ ነቢል ካፌ ይባል የነበረውና አሁን ፒክኒክ ካፌ በመባል የሚታጠራው ካፌና ሬስቶራንት፣ ሺ ሰለሞን ኃይሉ ሱፐርማርኬት፣ ባለ ምድር ቤቱ ላየን ባር፣ አንደኛ ፎቅ ላይ የሚገኘው ቴራስ ሬስቶራንት እና ሌሎች አገልግሎት መስጫዎችን ያቀፈው ይህ ሕንጻ እስከዛሬም በቅርስነት አለመመዝገቡ ለማፍረሱ ዉሳኔ መጽደቅ ምክንያት እንደሆነ ይነገራል፡፡

በሥነ ሕንጻ ዉበት አንጻርም አስፋልት ተሻግሮ ከሚገኘው የብሔራዊ ትአትር ቤትና ከዙርያ ገባው የሚናበብ በአርክ ቅርጽ የተዋቀሩ የድንጋይ ኮለሞች ያሉት ዉብ ሕንጻ ሲሆን ጥላ መሆን የሚችል በረንዳ (Arcade) ዙርያውን እንዲኖሩት ተደርጎ የተሰራ ነው፡፡ ይህ አይነቱ ግንባታ በጣሊያኖች የሚዘወተርና የዚያን ዘመን ሥነ ሕንጻ ይትባህል ከሚያሳዩ ጥቂት የከተማዋ ሕንጻዎች አንዱ ያደርገዋል፡፡

ሕንጻው በኪራይ ቤቶች አስተዳደር ሥር ለአመታት ሲተዳደር የቆየ ሲሆን ባለሐብቱ አቶ በላይነህ ክንዴ በ92 ሚሊዮን ብር የገዙትን ኢትዮጵያ ሆቴልን ጨምሮ አካባቢውን በሙሉ ለማልማት እንዲያስችላቸው 1700 ካሬ የሚሆን ቦታ እንዲሰጣቸው ለመስተዳደሩ ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡ ጥያቄውን ባቀረበቡት ቅጽበት የልማት ጥያቄያቸው በአስቸኳይ እንዲፈጸምላቸው መስተዳደሩ ለቂርቆስ ክፍለ ከተማ ትእዛዝ አስተላልፎ ነበር፡፡ ኾኖም በአካባቢው የሚገኙ የንግድ ሱቆቹ ኮሚቴ አቋቁመው ቦታው መፍረስ እንደሌለበትና ታሪካዊነቱ ተጠብቆ መቆየት እንዳለበት፣ የግድ መፍረስ ካለበትም ራሳቸው አካባቢውን ለማልማት አቅሙ እንዳላቸው አቋም ይዘው ሲከራከሩ ቆይተዋል፡፡

የላየን ባር ባለቤት ወይዘሮ ሰብለ ጸጋዬና የሺሰለሞን ሱፐርማርኬት ባለቤት አቶ ሞገስ ኃይሉን ጨምሮ ሌሎች 13 የሚሆኑ ግለሰቦች አቤቱታቸውን በመያዝ ታኅሳስ ወር 2005 ላይ ለጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ደብዳቤ ያስገቡ ሲሆን እስከዛሬም ጥያቄያቸው ምላሽ ሳያገኝ ቆይቶ ትናንት በአስቸኳይ በአንድ ወር ዉስጥ ቦታውን ለኪራይ ቤቶች እንዲያስረክቡ የሚያዝ ደብዳቤ ደርሷቸዋል፡፡

የደብዳቤው ይዘት እንደሚያትተውም በወረዳ 7 ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የኢትዮጵያ ሆቴል አልሚ ፕሮጀክት ተነሺ የኪቢአድ ቤቶች ከዚህ ቀደም ከከፍለ ከተማው የመሬት ልማትና ማደስ ጽሕፈት ቤት ለቦታው የፈረሳ ግምት ያወጣለት እንደሆነ አስታውሶ አሁን በሕንጻው ላይ ያሉ የመኖርያና የንግድ ቤቶች በሙሉ ደብዳቤው ወጪ ከሆነበት ቀን በአንድ ወር ዉስጥ ቤቱን በአስቸኳይ እንዲያስረክቡ የሚያሳስብ ነው፡፡

አቶ በላይነህ ክንዴ ንብረታቸው ያደረጉትን ኢትዮጵያ ሆቴልን ጨምሮ የበጎ አድራጎት ሕንጻውን ሙሉ በሙሉ በማፍረስ በምትኩ ባለ 60 ወለል ሕንጻ የመገንባት ፍላጎት አላቸው፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለአዲስ አበባም ሆነ ለምስራቅ አፍሪካ ረዥሙ ፎቅ ይሆናል የተባለለትን ባለ 46 ወለል የሚኖረውን ዋና ጽሕፈት ቤቱን በቻይናዎች አማካኝነት እያስገነባ የሚገኘው ከኢትዮጵያ ሆቴል ጎን ነው፡፡

የበጎ አድራጎት ሕንጻ የተገነባው በአምስት አመቱ የጣሊያን ወረራ ጊዜ ሲሆን በጊዜው ፓላሶ ሪቴሪያ የሚል ስያሜ ነበረው፡፡ ሕንጻው ከተገነባ 81 ዓመታት እድሜ ያለው ሲሆን ያን ጊዜ በከተማዋ ከሚገኙ ጥቂት ሕንጻዎች አንዱ እንደነበር ይታወቃል፡፡

ይህ ሕንጻ በኪነ ሕንጻ ዉበቱም ሆነ በያዘው ታሪክ እንዴት እስከዛሬ እንደ ቅርስ ሳይመዘገብ እንደቆየ ብዙዎቹን እያነጋገረ ይገኛል፡፡ አንድ በከተማው የቅርስ ጥበቃና ምዝገባ ጽሕፈት ቤት የሚገኙ ኦፊሰር እንደሚሉት የበጎ አድራጎት ሕንጻ በቅርስነት ለመመዝገብ ብዙዎቹን መለኪያዎች የሚያሟላ ነው፡፡ ምናልባት በከተማዋ ከዚህ ቀደም እንደቅርስነት እንዲታዩ ከተመዘገቡ ዉስጥ ላይካተት የቻለው ተዘንግቶ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አላቸው፡፡ አንድ ጊዜ ሳይመዘገቡ የታለፉ ሕንጻዎችን ተመልሶ ለመመዝገብ ሂደቱ አስቸጋሪ ነው፤ እድሉም የለም ማለት ይቻላል ይላሉ፡፡