Addis Ababa Yellow Cab -Photo AddisFortune
Addis Ababa Yellow Cab -Photo AddisFortune

ዋዜማ ራዲዮ- የትራንስፖርት ሚንስትር የነበሩትና በቅርቡ ወደ ኦሮሚያ ክልል አመራርነት የመጡት ወርቅነህ ገበየሁ መስቀል አደባባይ ተገኝተው “ለአዲስ አበባ ሕዝብ የአዲስ ዓመት ስጦታ ይዤ መጥቻለሁ” ያሉት ጳጉሜ፣2008 ነበር፡፡ የሚመሩት መሥሪያ ቤት በበኩሉ በነገታው ጋዜጠኛ ጥሩልኝ አለ፡፡ በመስከረም መጀመርያ ታሪፍ ተምኜ፣ ታርጋ አስለጥፌ መልከኞቹን ታክሲዎች በሙሉ ኃይል ወደሥራ አሰማርቼ የትራንሰፖርትን ችግር ድራሹን አጠፋለሁ ሲል ለሕዝብ ቃል ገባ፡፡

አሁን አዲስ ዓመት ገብቶ፣ ጥቅምት እየተገጋመሰ ነው፡፡ ወፍ የለም!

እርግጥ ነው ቢጫዎቹ ታክሲዎቹ በያደባባዩ ዉርወር ይላሉ፡፡ በየጎዳናው ሽው እልም ይላሉ፣ ይምነሸነሻሉም፡፡ ሙሽራ እንደቀረበት ሚዜ ትክዝ ብለው በየጥጋጥጉ የሚቆሙም አሉ፡፡

ወፍ የለም!

ወያላና ከራር ፀሐይ ያለርህራሄ የሚረባረቡበት የሸገር ሕዝብ መልከኞቹን ታክሲዎች ቁልጭልጭ እያለ ከመመልከት ዉጭ “ታክሲ!” ብሎ በሙሉ አፉ ሊጠራቸው፣ የኔ ብሎ ሊሳፈርባቸው አልደፈረም፡፡ይጠጌ- አይነኬ” ናቸው ይላሉ የተማሩ ተሳፋሪዎች፡፡ “የዉበት እስረኞች” ይሏቸዋል ፊልም አዘውታሪዎች፡፡

“እኔምልህ? ለምንድነው “የዉበት እስረኞች” የተባላችሁት ግን?” አልኩት ቴድሮስን፣ ፡፡

“ያው ምን መሰለሽመሸጥ መለወጥ አንችልም፣ እናምራለን ግን ባለ እዳ ነን፡፡ ለዚያ ይመስለኛል” አለ፣ መሪዉን በቄንጥ እያሾረ፡፡

ቴዲን ያገኘሁት እስጢፋኖስ ጋ ነበር፡፡ ላንድ አጣዳፊ ጉዳይ ጀሞ መድረስ ነበረብኝ፡፡ ከ300 ብር ብሞት አልወርድም አለ፡፡ ሰዓቱ ቀትር ስለነበር ፀሐይዋ ናላዬን አዞረችው መሰለኝ ከጠራው ሒሳብ 50 ብር ብቻ አስቀንሼ ተሳፈርኩ፡፡

“ቤተሰብ! ፈታ ብለሽ ቁጭበይ! በማስተዋወቂያ ዋጋ ነው የጫንኩሽ፡፡ ጀሞ በዚህ ዋጋ አይታሰብም” አለኝ፣ እንደ አምባሳደር ከኋላ ተደላድዬ መቀመጤን በዉስጥ ስፖኪዮ ከተመለከተ በኋላ፡፡

እውነት ለመናገር የቴዲ ሊፋን ትመቻለች፡፡ አዲስ ስለሆነች ነው መሰለኝ አዲሱ ኤይርባስ ላይ የተሳፈርኩ ያህል ተሰማኝ፡፡ ቴዲም የዋዛ አይደለችም፡፡ ብርቅ ሆናበት ነው መሰለኝ የወንበሯን ላስቲክ እንኳ አልላጠውም፡፡ ፈራ ተባ እያልኩ ለምን ላስቲኩን እንዳላጠው ስጠይቀው ግን ተከዘ፡፡ ነገሮች ካልተስተካከሉ መኪናውን ለመሸጥ እንደሚያስብ ነገረኝ፡፡

“ቅድም መሸጥ መለወጥ አንችልም አላልከኝም እንዴ?”

“የአክስዮን ድርሻህን እኮ ነው የምትሸጠው፡፡ የሚገዛው ሰው የሉሲ ታክሲ ማኅበር አባል ይሆናል፡፡ መኪናውንም አብሮ ይወስዳል፡፡ እስከነእዳው ማለቴ ነው፡፡ 100 ሺ ለእጄ ባገኝ አይኔን አላሽም! ማርያምን፡፡”

ከተሳፈርኩበት እስጢፋኖስ እስካሁን ሦስት መብራት ይዞናል፡፡ የአብዮት፣ የስቴዲየም ቤተዛታና የኮሜርስ መብራት፡፡ በቁርጥ ዋጋ ባልነጋገርና በኪሎ ሜትር የምከፍል ቢሆን ኖሮ በቆምንበት ሁሉ እኔ ላይ ነበር ማሽኑ ይቆጥር የነበረው? ወይስ ምንድነው ብዬ ማብሰልሰሌ አልቀረም፡፡ ጥያቄዬን አሳደርኩት፡፡

“ሥራ ግን እንዴት ነው? ለምዶላችኋል?” ሜክሲኮ የፌዴራል ፖሊስ ሕንጻ ጋር ወደ ሳርቤት ገብሬል መስመር ሲታጠፍ ያነሳሁለት ጥያቄ ነበር፡፡

“ወፍ የለም ባክሽ!”

“እውነትህን ነው?”

Addis Ababa Yellow cab
Addis Ababa Yellow cab

“አዎ!ሰው ለምን እንደሆነ አላቅም ቢጫ ታክሲ ይፈራል፡፡ ኮማንድ ፖስት እያሉ ሙድ የሚይዙብን አሉ፡፡ ዋጋችን ዉድ ስለሚመስላቸው መሰለኝ፡፡”

ሳቅኩኝ፡፡ ቴዲ ዝም ብሎ የሚነዳ ሾፌር አይደለም፡፡ ተጫውቶ የሚያጫውት አይነት ነው፡፡

“ገና እኮ ዋጋ ሳይጠይቀን ነው ሰው ዝም ብሎ የሚሸሸን፡፡”

“እኔ እንደውም ብዙ ሰው እንደወደዳችሁ ነው የሰማሁት”

“አይምሰልህ! ያዲሳባ ሕዝብ ድሮም ወረተኛ ነው፤ አይገር ባስ ሲመጣም እንዲህ አድርጎት ነበር፣ ባቡሩ ሲመጣም ቆልቶት ነበር፡፡ ከዚያ ዞር ብሎ አያይህም፡፡አንተ ነህ ፍዳህን የምትበላው፡፡”ደርሶ ሆድ ባሰው፡፡

“ላዳ ታክሲ ግን አበቃለት ማለት ነው?”

“አይመስለኝም፡፡ እንዲያውም አሁን ሳስበው እኛንም አንደኛውን ሰማያዊ ቢቀቡን ይሻለን ነበር፡፡”

እንደገባኝ ቴዲ ቢቀልድ ቢጫወትም ዉስጥ ዉስጡን ድምጹ ስጋት የተጫነው ይመስላል፡፡ በመኪናዋ አዲስነት ደስተኛ ነው፣ የባንክ እዳው ግን ፍርሃት ለቆበታል፣ የገበያ መጥፋት ደግሞ ግራ አጋብቶታል፡፡ በወር 5850 ብር መቆጠብ አለበት፡፡

“በዛች ከርካሳ ማዝዳ ቢሆን እኮ እስካሁን አንድ አምስት መቶ ሸቃቅዬ ነበር፣ ማርያምን!”

“ማዝዳ ነበር የነበረችህ??”

“መዓዚ ነበር የምላት፡፡ ትዳር በለው፡፡ ከ97 ጀምሮ 10 ዓመት ነድቻታለሁ፡፡”

አዘንኩለት፡፡ከመአዚ ጋር ጥልቅ ፍቅርና ጠንካራ ቁርኝት እንደነበረው ከድምጹ ያስታውቃል፡፡

ጀርመን አደባባይ ተዘጋግቶ ጠበቀን፡፡ ትራፊክ የለም፡፡ ሁሉም መኪኖች ቀድመው አደባባይ ለመግባት ይሞክራሉ፡፡ ቴዲ አዲሷ ሊፋን እንዳትጋጭበት የሰጋ ይመስለኛል፡፡ እንደ ታክሲ ሾፌር አይደለም የሚነዳው፡፡

***

በሁሉ ነገር ግራ የሚገባው መንግሥት የአዲስ አበባን የትራንሰፖርት ጭንቀት ለመፍታት ብስክሌት ሳይቀር ሞክሯል፡፡ ተሳክቶለት ግን አያውቅም፡፡ ግንቦት መጀመርያ፣ 2008 ዓ.ም 08/2008 ተብሎ የሚጠራ መመሪያ አወጣ፡፡ በዚህ መመሪያ መሰረት ቀድሞ በላዳ ታክሲ ተሰማርተው የነበሩ ወይም በብሔራቸው የቦሌ ታክሲ የነበሩ ሁሉ በአክሲዮን ተደራጅተው ከመጡ አዳዲስ ታክሲ ያለቀረጥ እንዲያስገቡ እፈቅዳለሁ አለ፡፡ ይህ መመሪያ እንደተሰማ 79 ማኅበራት ትራንስፖርት ቢሮን አጣበቡ፡፡

አንድ ሕጋዊ አክሲዮን ማኅበር፣ ወይም ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በትንሹ 50 ታክሲ ማዝገባት አለበት ሲባል 79ኙም ማኅበራት ደነገጡ፡፡ አንድ ሀምሳ ማኅራት ወዲያዉኑ ጠፉ፡፡ መንግሥትም ደነገጠ፡፡ በአንድ ማኅበር መግባት ያለባቸው ትንሹ የታክሲ ቁጥር ከ50 ወደ 35 ዝቅ እንዲል አደረገ፡፡

መመሪያው በሚያዘው መሰረት እያንዳንዱ አክሲዮኑ በባንክ ሒሳብ የመኪናውን 30 በመቶ ብር ተቀማጭ እንዲያደርጉ አዘዘ፡፡ ይህን ጊዜ ተንደርድረው ከመጡ 79 ማኅበራት 53 የሚሆኑት የገቡበት አልታወቀም፡፡ 26ቱ ብቻ የተባሉትን ገንዘብ አስቀመጡ፡፡

“ብዙዎቹ መንግሥት መኪናውን ገዝቶ በስጦታ እንዲያበረክትላቸው ጠብቀው ነበር መሰለኝ” አለኝና በረዥሙ ሳቀ፣ ቴዲ፡፡

“አሁን ከተማዋ ዉስጥ ስንት የዉበት እስረኛ ነው ያለው ግን? በዛችሁብኝ፤ በየቦታው ነው የማያችሁ፡፡”

“በዝተን አይምሰልሽ ቀዮ፤ የጠጅ ቀለም ቀብተውን ከየትም ስለምንታይ ነው የበዛንብሽ፡፡” በድጋሚ ዘለግ ያለ ሳቅ ሳቀ፡፡ ጤንነቱን መጠራጠር ጀመርኩ፡፡ ለምንድነው ይሄ ልጅ አብዝቶ የሚስቀው?

ከዉጭ አገር ከተገዙት 1163 ታክሲዎች 826 ገብተው አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡ 821 የሚሆኑትን ገንዘብ ያበደራቸው ብርሃን ባንክ ነው፡፡ ቀሪዎቹን ንግድ ባንክና ንብ ባንክ ደርሰውላቸዋል፡፡ ያኔ ነገሩ ሲጠነሰስ “አገልግሎቱ በኪሎ ሜትር ይሆናል፡፡ እያንዳንዱ ማኅበር የተማከለ የጥሪ ማዕከል ይኖረዋል” ተብሎ ነበር፡፡ እንደ ኡበር መሆን የቃጣቸው ወጣት የሶፍትዌር ሊቃውንትም በታክሲ አገልግሎት ዙርያ አዲስ ግኝት አለን ሲሉ በሚዲያ ወጣ ወጣ ማለት ጀምረው ነበር፡፡ ትራንስፖርት ሚኒስቴርና የዉበት እስረኞቹ ግን በታሪፉ ጨርሶ ሊግባቡ አልቻሉም፡፡

“ሼም አያቅም እንዴ መንግሥት? በከተማ አውቶቡስ ዋጋ ሊያሰራን ይፈልጋል እንዴ? የማነው በናታቹ?” ቴዲ የታሪፍ ጉዳይ ሲነሳባት ደርሶ ቱግ ይላል፡፡

“ስንት ወሰኑላቹ?”

“በኪሎ ሜትር ዴች”

“10 ብር? ዘርፈሽኛላ ቴዲ?” ከእስቲፋኖስ ጀሞ የተስማማሁበት ዋጋ ደርሶ ጎኔን ሰቀዘኝ፡፡

“አንሰማውም ባክሽ! ከቦሌ ጊዮርጊስ 10 ኪሎ ሜትር ነው፡፡ በመቶ ብር ልንጭለት ይፈልጋል እንዴ? ላሽ በለው?”

ቴዲ እውነቱን ነው፡፡ መንግሥት ያስኮረፈውን የአዲስ አበባን ሕዝብ በታክሲ ታሪፍ ሊክሰው እየሞከረ ይመስላል፡፡ 10 ብር አሁን ፓኮ ኒያላ አይገዛም፡፡ አንድ ስፖኪዮ ቢሰበር አንድ ሺ ብር አይበቃም፡፡ ሰርቪስ አለ፡፡ ፍሬን ሸራ አለ፡፡ የትራፊክ ቅጣት አለ፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ የባንክ እዳ እነ ቴዲን ግሮሯቸው ላይ ቆሟል፡፡ እንዴት ነው በ10 ብር ታሪፍ ይህን ሁሉ የሚሸፍኑት? እርግጠኛ ነኝ አይሰሩለትም፡፡

“ሊፋኖቻችሁ እዚህ ነው አይደል የተገጣጠሙት?”

“ኸረ አይደለም! ከዉጭ ነው የመጡት፡፡ ሊፋን መሆናቸውን አይተሸ ነው?” ቴዲ ጮኸ፡፡ በስፖኪዮው ገላመጠኝ፡፡ “ቀለሙን ጨምሮ አንድ ነገር ሳይቀር ከዉጭ ነው የገባው፡፡ ታርጋ ብቻ ነው ከአገር ዉስጥ” በራሱ ቀልድ ዘለግ ያለ ሳቅ ሳቀ፡፡

“እኮ ያው ስሪታቸው ቻይና ነው፡፡”

ቴዲ ከቻይና መሆናቸውን ቢያውቅም እንዲነሳበት አይፈልግም፡፡ የገቡት ከዉጭ ነው፣ በቃ፡፡ ከብዙ መተከዝ በኋላ ጀርመን አደባባይን እንዳለፍን፣ ዋናውን የጀሞን መንገድ እንደያዝን ሊፋን በመግዛቱ እንደሚጸጸት ተናዘዘ፡፡

“ሊፋን የቻይና መኪና ነው፡፡ ጥሎበት ቶሎ ይገረጅፋል፡፡ ይኸው አይገር ባስ የአሮጊት መስሎ አታየውም? ቢሾፍቱ ባስ እንዴት ማስጠሎ እንደሆነ አታይም? ቻይና እድሜዋ አጭር ነው፡፡መሪዉን በቡጢ ነረተው፡፡”

“ማርያምን ተገነተርኩ፡፡ መባነን ነበረብኝ”

ላጽናናው አልፈለኩም፡፡ ይዉጣለት፡፡

***

ሊፋን ከቤቱ 365ሺ ብር ነው፡፡ መንግሥት ቀረጥ አነሳለቸውና ዋጋውን ወደ 220ሺ ብር አወረደላቸው፡፡እስከነ ኢንሹራንሱ 98 ሺህ ብር ከፍለዋል፡፡ ኾኖም የባንክ ወለድ አለባቸው፡፡ 80 ሺ ብር ወለድና የመኪናው ቀሪ ብር 130ሺ በድምሩ 210 ሺ ብር በ2 ዓመት ገቢ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለዚያ ነው እነ ቴዲ አብዝተው የሚጨነቁት፡፡

ምናልባትም እነ ቴዲ የሊፋንን እዳ ከፍለው በሚጨርሱበት ወቅት ሊፋኗ ራሱ አብራ ከእዳው እኩል ታልቅ ይሆናል፡፡ በዚህ እርግጠኛ መሆን ይቻላል፡፡ የሆላንድ ካር አባይን፣ የመስነፍን ኢንጂነሪንግ ጂሊን የገዙ ወዳጆቼ መኪኖቻቸው እንደ ጭስ ተነውባቸዋል፡፡ ለቴዲሻ በድጋሚ አዘንኩለት፡፡

እስከነአባባሉ ልፋ ያለው ሊፋን ይገዛል ነው የሚባል፡፡

የጀሞን አደባባይ ለመሻገር አንድ 25 ደቂቃ ቆምን፡፡ መንገዱ ተቆላልፏል፡፡ ቴዲ የሊፋንን ግለ ታሪክ ጨርሶ ወደ አቫንዛ ታሪክ ገባ፡፡

ቢጫዎቹ ታክሲዎች ሁሉም ደም ግባታቸው ልዩ ነው፡፡ በተለይ ሽንጣሞቹ አቫንዛ ቶዮታዎች ከዉብም ዉብ ናቸው፡፡ 460ሺ ብር ከቀረጥ ነጻ እንደወጣባቸው ቴዲ አጫወተኝ፡፡

“ነገሩን የቆሰቆሱት እኮ የቦሌ ታክሲዎች ናቸው፡፡ በተለይም አዲስ ሜትር ታክሲ የሚባል ማኅበር አለ፡፡ የፖለቲካ ማኅበር በለው፡፡ መሪዎቹ መሬ* ናቸው፡፡ ከለታት አንድ ቀን መንግሥት ጋ ሄዱና “ይሄ እኛ የምንነዳው ከርካሳ ታክሲ የአገር ገጽታ እያበላሸ ነው፡፡” የቱሪዝም መዳከም ዋናው መንስኤ የቦሌ ታክሲዎች ሞተር መድከም ነው ብለው ተቀደዱ፡፡ ወዲያውኑ ተፈቀደላቸው፡፡ ምን አይነት መኪና እናስመጣ በሚለው ብዙ ክርክር ካካሄዱ በኋላ የ2016 አቫንዛ ቶዮታ ይሁንልን ብለው ወሰኑ፡፡ ይሄ ሙድ ያለው መኪና የሀብታም መኪና እንደሆነ ነው የሚታወቀው፡፡ ለታክሲነት በጭራሽ የሚታሰብ አይደለም፡፡ ማኅበሩ እንዴት እንደመረጠው አላውቅም፡”

“ከሊፋን መቼስ የትናየት ይሻላል” አልኩኝ፡፡ ሳላስበው የከረመ ቁስል ቀሰቀስኩ፡፡

“ፍሬንድ! ምን ነካሽ!? ባጃጅና ሊሙዚን ታወዳድሪያለሽ እንዴ?” አቫንዛ እኮ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ነው ከቤቱ የሚገዛው፤ ዜሮ ዜሮ፣ ያለጠፈ፡፡” በዉስጥ ስፖኪዮ አፈጠጠብኝ፡፡

“ታዲያ አንተ ከሊፋን እሱ አይሻልህም ነበር?”

“ቀላል ይሻላል እንዴ! ያኔ አልባነንማ፡፡ ቅድመ ክፍያው 120 ሺ ብር ነው ሲሉኝ ደንግጬ ይብራብኝ አልኳቸው፡፡ለሊፋን በከፈልኩት ብር 22ሺ ብጨምርበት ዛሬ የአቫንዛ ጌታ ነበርኩ፤ ማርያምን!”

ቴዲ እውነቱን ነው፡፡ አቫንዛ ቶዮታ የተቀናጣ የሀብታም መኪና ነው፡፡ እንዲያውም ሀብታሞች እንዴት የኛ መኪና እንደ መናኛ ለታክሲነት ይፈቀዳል ብለው መንግሥት ላይ አቂመዋል አሉ፡፡ እጃቸው ላይ ያለ አቫንዛን ባገኙት ዋጋ መሸጥ ጀምረዋል ይባላል፡፡ በዚህ ምክንያት የለጠፈ አቫንዛ ዋጋው ዘጭ ብሏል ይባላል፡፡ ከባለጸጋነት ወደ ታክሲ ሾፌርነት ያወረዳቸው መንግሥት ደጋፊዎቹን ሳያስቀይም አልቀረም፡፡

እነዚህ 2016 አቫንዛ ቶዮታ አውቶሞብሎችን በግል ወደ አገር ቤት ለማስገባት አንድ ሚሊዮን ሁለት መቶ ሺ ብር ይፈጃል፡፡ ኾኖም በመንግሥት ቸርነት ማኅበሩ በ460ሺህ ብር ነው አጠናቆ ወደ አገር ቤት ያስገባቸው፡፡

በዚያ ላይ ቴዲ እንደሚለው አቫንዛ በአንድ ጊዜ 7 ቀጠን ያሉ ሰዎችን መያዝ ይችላል፡፡ ሻንጣ ያለው ሰው ከመጣ የኋላው ወንበር ይታጠፍና ሰፊ የሻንጣ ቦታ ይፈጠራል፡፡

“ወፍራም አረቦች በድሮ ላዳ ታክሲ ሲገቡ የተወሰነ ቦርጫቸው ዉጭ ይቀራል፡፡ ስለዚህ አቫንዛን ነው የሚመርጡት፡፡” አለኝ ቴዲዮ እየሳቀ፡፡

ጀሞ ደረስኩ፡፡ የቴዲ ሳቅ ዘላቂ አልመስልህ አለኝ፡፡ እዳው ሲያልቅ ሊፋኑም አብራ የምታልቅ መሰለኝ፡፡