• ከሰሞኑ በአገሪቱ ያለውን አለመረጋጋት ተከትሎ የሊዝ ገበያ ጥንቡን ጥሏል እየተባለ መወራቱ ያናደዳቸው ኦቦ ድሪባ ሕዝቤን ያዝ እንግዲህ ያሉት ይመስላል፡፡ ይኸው ሜዳውይኸው ፈረሱ!

(ለዋዜማ ራዲዮ)

ጤና ይስጥልኝ ጌታዬ!

ገረመው እባላለሁ፡፡ እሳት የላስኩ የፊንፊኔ ደላላ ነኝ፡፡ ምስጉን ጉዳይ ገዳይ ስለመሆኔ እግዜርም ሰይጣንም ያውቃሉ፡፡ ኪራይ ሰብሳቢ መሆኔን ድሪባም ኩማም ያውቃሉ፡፡ ዉሎ-አዳሬ ብሔራዊ፣ አመሻሼ አብዮታዊ ሃሃ፣

ላየን ባር ቤቴ፣ ቴሌ ባር ግዛቴ

እውነት ነው! ጥሎብኝ አልረጋም፡፡ ካዛንቺስ ነው ሲሉኝ ሳሪስ፣ ቀበና ነው ሲሉኝ ባምቢስ!! ድሮስ ደላላ ምን ቀልብ አለው ብለው ነው፤ጌታው!

24ኛ ሊዝ መውጣቱን ላበስሮት ነው አመጣጤ፡፡ መንገር ያለብኝን ነግሬዎ ልሂድ!! ልብ ብለው ይስሙኝ!! ኋላ እንዳይቀየሙኝ፡፡

ካዛንቺስና ታላቁ አሜሪካን ግቢ ገበያ ወጥተዋል፡፡

መርካቶ መሸጫ ነበር፡፡ አሁን መርካቶ ራሱ እየተሸጠ ነው፡፡ የዘፈን ዳር ዳሩ እስክስታ ነው፡፡ የበርገር ዳር ዳሩ ቺፕስ ነው፡፡ የመርካቶ ዳር ዳሩ አሜሪካን ግቢ ነው፡፡ እሱም ተቆርሶ እየተሸጠ ነው፡፡ አራት ሺ ድሀ ተዛዝሎ የኖረበት፣ ጥቁር ገበያ ለዘመናት የደራበት፣ መቶ ሺ የአረብ አገር ተጓዥ አልጋ የያዘበት፣ የመጀመርያው የአሜሪካን ዲፕሎማት የኖሩበት ስንትና ስንት ታሪክ የተሰራበት አሜሪካን ግቢ አሁን እዳሪ መሬት ሆኗል፡፡ ነዳያን የላስቲክ ቤት ቀልሰው ቦታው ለሀብታም እስቲዛወር ያሸልቡበታል፡፡ ጎረምሶች ቾክ አስምረው ቦታውን ለፓርኪንግ ያከራዩታል፡፡ መርካቶ የሚዘልቅ ሞጃ መኪናውን ቤት በፈረሰባቸው የድሀ ልጆች ያስጠብቃል፡፡ ሲመለስ 50 ሳንቲም ይጥልላቸዋል፡፡ እሱም ለልጆቹ አዝኖ እንዳይመስልዎ! ሳንቲም ኪስ ይቀዳል፡፡ እየተንኮሻኮሰ ያስጨንቃል፡፡ ስለዚህ ለኔ ቢጤ ሰጥቶ ይገላገለዋል፡፡ በዚያውም ለሰማይ ቤት ሌላ ዙር ሀብት ቀብድ ያሲዛል፡፡

እኔ ምለው ጌታዬ! በቃ ለድሀ የሚሆን ቦታ በፊንፊኔ እንዲህ ይጥፋ?

እኔ እንኳ ድሀና ድህነትን ጥሎብኝ እፈራለሁ፡፡ ለዚያም ነው ዉሎዬ ከሞጃ የሚሆነው፡፡ ግን ግን የፈረሱት የአሜሪካን ግቢ ሰዎች የት ተወሰዱ ብሎ መጠየቅ የወገን ነው፡፡ ካራቆሬ፣ ቡልቡላ የአገር ቂጥ፣ የአለም ዳርቻ ተጥለዋል፡፡ እንደነገሩ የቆመ ኮንዶሚንየም ታድለዋል፡፡ ከመሐል አገር ወደ ካራቆሬ መጣል ቆሻሻ ከመሆን በምን ይለያል ጎበዝ! ቆሻሻ ራሱ ካራቆሬ ድረስ አይሄድም እኮ፣ አየር ጤና ነው ቆሼ ያለው፡፡

ሳላስበው ፖለቲካ ተናገርኩ እንዴ ጌታዬ? ደላላ ዋጋ እንጂ ፖለቲካ አያምርበትም ይሉኝ ነበር አቶ ገብረዋሕድ!!

ለማንኛውም መሬት እንደ ወርቅ ክምችት በሚታይባት ፊንፊኔ ባለሐብት ሊያጋድሉ የሚችሉ ቦታዎችን ለገበያ ቀርበዋል፡፡ ይፍጠኑ ሰነድ ይግዙ፡፡ ሁለት መቶ ብር ሰነድ ለመግዛት ያለውን ወረፋ እኔ አልነግርዎትም፡፡ እርስዎ ራስዎ አራዳ ድሪባ ቢሮ ሄደው በአይንዎ ካላረጋገጡ አያምኑኝም፡፡

ከሰሞኑ በአገሪቱ ያለውን አለመረጋጋት ተከትሎ የሊዝ ገበያ ጥንቡን ጥሏል እየተባለ መወራቱ ያናደዳቸው ኦቦ ድሪባ ሕዝቤን ያዝ እንግዲህ ያሉት ይመስላል፡፡ ይኸው ሜዳውይኸው ፈረሱ!

ካዛንቺስ ነው አንዱ ሞጃ የሚጋደልበት አውድማ እንዲሆን በድሪባ ካቢኔ የተመረጠ፡፡

ካዛንቺስ ግን ምን አለ? ካዛንቺስ ባለ 5 ኮከቡ ራዲሰን ብሎ አለ፣ ካዛንቺስባለ 5 ኮከቡ ኢሊሌ አለ፣ ካዛንቺስ ባለ 4 ኮከቡ ጂፒተር አለ፣ ካዛንቺስ ባለ 4 ኮከቡ ኢንተርኮንቲነንታል አለ፡፡ ካዛንቺስ ሌላም ብዙ ነገር አለ፡፡ በኮከብ ብዛት የካዛንቺስን ያህል ጋላክሲ የሆነ ሰፈር የለም፡፡ ፊንፊኔ ካሏት ጥቂት ባለ 5 ኮከብ ሆቴሎች 99 በመቶው የከተሙት በካዛንቺስ ነው ብል ማጋነን አይሆንም፡፡

እናም እርስዎ እንደአጋጣሚ ሞል ወይም ሆቴል እስከዛሬ በካዛንቺስ ከሌልዎ፣ ጊዜው አሁን ነው እልዎታለሁ፡፡ ሰነድ ይግዙና እድልዎን ይሞክሩ!

በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 የሚገኙ ሁለት ቦታዎች ብቻ ለቅምሻ ያህል ወጥተዋል፡፡ በኮድ ቁጥር LDR/KIR/MIX/ 00012072 የቀረበው ቦታ የይዞታ ስፋቱ 1354 ካሬ ስፋት ያለው ሲሆን ለቅይጥ አገልግሎት የቀረበ ደረጃ 2 የፊንፊኔ መሬት ነው፡፡ ተጫራቾች ይህ ቦታ ላይ ለመወዳደር 6 ሚሊዮን 318 ሺህ 666 ብር አቅም ማሳያ ባንክ ዉስጥ ሊኖራቸው ይገባል፡፡

ሁለተኛው የካዛንቺስ መሬት በዚሁ ወረዳ 6 የሚገኝ ደረጃ 2 ቦታ ሲሆን የይዞታ ስፋቱ 1238 ካሬ ሜትር ነው፡፡ ይህን መሬት የሚወዳደር 5.7 ሚሊዮን ብር በባንክ ደብተሩ ማሳየት ይጠበቅበታል፡፡ የሁለቱም ቦታዎች የሕንጻ ትንሹ ከፍታ 9 ወለል ሲሆን አቅም አለኝ የሚል እስከ 19 ወለል ወደላይ መገንባት ተፈቅዶለታል፡፡ ሰማዩን ጨርቅ ያርግለት፡፡

የሁለቱም ቦታዎች መነሻ ዋጋ 809 ብር ብቻ ነው፡፡ ሦስት በስጋ የማይዛመዱ ተጫራቾች ለቦታው ካልቀረቡ ጨረታው ይሰረዛል፡፡ እነዚህ ግሩም ቦታዎች በስንት ብር ያልቁ ይሆን? ብለው ራስዎን ጠይቀዋል? ገረመው! እኛ ምኑን አውቀን፤ አንተው ንገረን ካላችሁኝ ሰፊ ልምዴንና የካበተ እውቀቴን ተጠቅሜ የሚመስለኝን መጠቆም አይገደኝም፡፡ ለካሬ ከመቶ ሺህ ብር በታች አቅርቦ ለማሸነፍ ማለም የዋህነት ነው እላለሁ፡፡

ከካዛንቺስ የባሰ እሳት ቦታ የት አለ ካሉኝ ደግሞ ወደ አሜሪካን ግቢ እመራዎታለሁ፡፡

አንድ መቶ ስድሳ ሺህ ካሬ ያህል ከሚሰፋው አሜሪካን ግቢ ለዚህኛው ዙር ገበያ የቀረበው መሬት ተቆንጥሮ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ጨረታ የወጡት ስድስት ቦታዎች ቢደመሩ እንኳ 10ሺህ ካሬ መሙላታቸውን እጠራጠራለሁ፡፡ ከታላቁ አንዋር መስጊድን ይዞ የሚንደረደረው አስፋልት እስከ ጎርደሜ ወንዝ ድረስ 16 ሄክታር ይሰፋል፡፡ ጃሊያ ትምህርት ቤት ድረስ ግራና ቀኝ የፈረሱ የድሀ ሰፈሮች ናቸው ፈረንካ ያለው ይዉሰዳቸው ተብሎ በዚህ 24ኛ ዙር የተወሰነባቸው፡፡ በድምሩ ስድስት ቦታዎች ሲሆኑ የካሬ ስፋታቸው ከ343 ካሬ እስከ 1380 የሚለያዩ ናቸው፡፡

ስድስቱም ቦታዎች በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ የሚገኙና ለቢዝነስ አገልግሎት ብቻ መዋል የሚችሉ ናቸው፡፡ በዚህ አካባቢ አሸናፊዎች መገንባታ የሚችሉት ትንሹ የወለል ከፍታ 9 ሲሆን አቅም አለኝ ካሉ 19 ፎቅ ያህል ወደ ላይ ከመውጣት የሚያግድዎ ምድራዊ ኃይል የለም፡፡ ሰማዩን ጨርቅ ያርግልዎት ብለዎታል ኦቦ ድሪባ፡፡

ከዚህ ቀደም በነበረ መመሪያ መርካቶና አካባቢው ከአራት ወለል በላይ ከፍታ መገንባት ሕጉ አይፈቅም ነበር፡፡ ያን ሁሉ ግቻ ፎቅ ካበቀሉ በኋላ ደግሞ ከፍታውን ወደ 19 አሳድገውታል፡፡ እንዳሻቸው ነው የሚሆኑት፡፡ ሲላቸው ይፈቅዳሉ፣ ሲላቸው ይገድባሉ፡፡

የአሜሪካን ግቢ ስድስቱም ቦታዎች የድሪባ ቢሮ ደረጃ አንድ ቦታዎች ብሎ የሰየማቸው ሲሆን የመነሻ ዋጋቸውም 1535 ብር ብቻ ነው፡፡ ታዲያ ይሄ መነሻ ዋጋ እንጂ መድረሻ ዋጋ አይደለም፡፡ ጌታዬ በፍጹም እንዳይታለሉ፡፡ ይሆነው ሆኖ እነዚህ የመርካቶ ቦታዎች በስንት ብር ያልቃሉ ብለው ያስባሉ? ገረመው! እኛ ምኑን አውቀን፤ አንተው ንገረን እንጂ ካሉኝ ሰፊ የድለላ ልምዴንና የካበተ እውቀቴን ተጠቅሜ ዋጋ ልሰጥዎ እችላለሁ፡፡

ለካሬ ከ150ሺህ ብር በታች ሰጥተው ካሸነፉ አድለኛ ነዎት!

ገረመው ነኝ፣ ከላየን ባር!