ዋዜማ ራዲዮ- ሀገሪቱ ውስጥ የተነሳበትን ተቃውሞ በሀይል ለማኮላሸት የወሰነው ኢህአዴግ እየወሰደ ካለው መጠነ ሰፊ የአፈና እርምጃ በተጨማሪ የካቢኔ አባላት ሹም ሽር ለማድረግ ተሰናድቷል።
የድርጅት አባል ያልሆኑ አዳዲስ ሚኒስትሮችን ጭምር ወደ ሥልጣን ያመጣሉ ተብለው የሚጠበቁት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ልዩ ኮሚቴ አዋቅረው አዳዲስ አመራሮችን መመልመል ከጀመሩ ሳምንታት ተቆጥረዋል፡፡
ይህ ኮሚቴ ጠርቶ ያነጋገራቸውና በግብረሰናይ ድርጅቶች ዉስጥ በዳይሬክተርነትና በዩኒቨርስቲ ተመራማሪነት ይሠሩ የነበሩ ጥቂት ግለሰቦች ጭምር ባሳለፍነው ሳምንታት ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ እየተጠሩ አገራችን ለማገልገል ምንያህል ፍቃደኛ እንደሆኑ ሲጠየቁ ነበር፡፡ የማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስትር፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር፣ የእንሰሳትና አሳ ሐብት ሚኒስቴር እና ሴቶችና ሕጻናት ሚኒስትር ቦታዎች የፓርቲ አባል ላልሆኑ ባለሞያዎች ሊሰጥ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ የዋዜማ ምንጮች ለነዚህ ቦታዎች የሚሆኑ ግለሰቦች ምልመላ ባሳለፍነው ሳምንት ተካሄዶ እንደተጠናቀቀ ይጠቁማሉ፡፡
የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር የነበሩት አቶ አብይ አሕመድ አሊ በኦሮሚያ አዲሱ ካቢኔ በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የከተማ ልማትና ቤቶች ኃላፊ ተደርገው መሾማቸው የቀድሞው ሥልጣናቸው ስለማጣታቸው አመላካች ነው፡፡ በተመሳሳይ የእንሰሳትና አሳ ሐብት ሚኒስቴር የነበሩት አቶ ስለሺ ጌታሁንም በኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳደር የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ኃላፊ በመሆናቸው ቀድሞ ይመሩት የነበረው ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ከፓርቲ አባል ዉጭ ለሆነ ባለሞያ ይሰጣል የሚል ግምት አለ፡፡
ያልተረጋገጡና ዋዜማ ያገኘቻቸው መረጃዎች አዲሱ ካቢኔ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የኮሚኒኬሽን ሚኒስቴር በአዳዲስ ሰዎች እንዲተካ በመልማዩ ኮሚቴ ሀሳብ መቅረቡን ያሳያሉ፡፡ ይህ ምክረ ሀሳብ ይጽደቅ አይጽደቅ ግን የታወቀ ነገር የለም፡፡ ምናልባት የአቶ ጌታቸው ረዳ ቦታ በሌላ የሕወሓት አባልና የሬድዮ ፋና ስራ አስኪያጅ በአቶ ወልዱ ይመስል ሊወሰድ ይችላል፡፡ ይሁንና እነዚህ መረጃዎች የምልመላ ሂደቱን ብቻ ተመስርተው የተገኙ ሲሆን የመጨረሻ ዉሳኔን አያሳዩም፡፡
አቶ ቴዎድሮስ አድሀኖምንም የመተካት ሀሳብ ሲንሸራሸር እንደነበር ምንጮች ነግረውናል። የአቶ ቴዎድሮስ መተካት በከፊል በራሳቸው ፍላጎትና ለአለም የጤና ድርጅት መንበር ከሚያደርጉት ሙከራ ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል እየተነገረ ነው። በካቢኔ ሹመቱ የብሄር ተዋፃኦ ይፋዊ ባልሆነ መንገድ መስፈርት መሆኑ እንደቀጠለ እየተሰማ ነው። መንግስት የስልጣን ግብዣ ካቀረበላቸው የፓርቲ አባል ያልሆኑ ግለሰቦች ብዙዎቹ ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸውን፣ የተስማሙትም ከብዙ ማግባባት በኋላ ይሁንታ መስጠታቸው የፓርቲው ምንጮች ይናገራሉ።።