et parliamentዋዜማ ራዲዮ- በነገው ዕለት (ሀሙስ) ይደረጋል ተብሎ ይጠበቅ የነበረው የተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባና የጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲሱ ካቢኔ ይፋ የሚደረግበት ቀን ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙ ታወቀ፡፡

ይህ እንዲሆን የተደረገው ክልላዊ ምክር ቤቶች የየራሳቸውን ካቢኔ ለማሳወቅ ተጨማሪ ጊዜ በመፈለጋቸው ነው፡፡

ሕወሓት ባለፉት ሳምንታት መቀሌ ላይ ለተከታታይ ቀናት ከፍተኛ ግምገማ ላይ ቆይቶ ባወጣው መግለጫ የከፍተኛ አመራር ሽግሽግ በቅርቡ ይካሄዳል ብሎ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ አዲስ አበባ የተመለሱት የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴና ሥራ አስፈጻሚ አባላት ከትናንት ጀምሮ ወደ መቀሌ እያቀኑ ነው፡፡ ከነገ ከሰዓት ጀምሮም ለሌላ ዙር ግምገማ ይቀመጣሉ፡፡ ምናልባት በዚህ ግምገማ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አባይ ወልዱን ጨምሮ ከፍተኛ ሹም ሽር ሊኖር ይችላል ተብሎ ተገምቷል፡፡

አቶ አባይ ወልዱ በክልሉ ሕዝብ በአመዛኙ ቅቡልነት ሊያገኙ ያልቻሉ መሪ ናቸው፡፡

በተመሳሳይ ብአዴን ከዚህ ቀደም ባወጣው መግለጫ ለከፍተኛ አመራሮች ከፍተኛ ማስጠንቀቂያ ሰጥቻለሁ የሚል ቁንጽል መግለጫ መስጠቱ የሚታወስ ሲሆን የአመራር ሽግሽግ ስለመካሄዱ ግን ምንም የተሰማ ነገር የለም፡፡ ክልሉ አዲስ ካቢኔውን በቅርቡ እንደሚመሰርት ይጠበቃል፡፡ ተመሳሳይ ሂደት በደኢሕዴን አመራሮች ሽግሽግ ከተካሄደ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲሱን ካቢኔያቸውን ሊያሳዉቁ ይችላሉ፡፡ ይህም በሕዳር ወር መጀመርያ ሊደረግ ይችላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡