girisho posterዋዜማ ራዲዮ- በአዲስ አበባ አነጋጋሪ ሆኖ የሰነበተውና በኢትዮጵያ የትያትር ታሪክ በአንድ ሰው በመተወን(Monologue) የመጀመሪያ የሆነው ፌስታሌን (እያዩ ፈንገስ) የመድረክ ትዕይንት በዩናይትድ ስቴትስ በዚህ ሳምንት መታየት ይጀምራል። ዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው የመጀመሪያው የትዕይንቱ ቦታ ነው -November 6። በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች በቀጣይ ሳምንታት ይቀርባል። ደራሲው በረከት በላይነህና ተዋናይ ግሩም ዘነበ ለትዕይንቱ አሜሪካ ይገኛሉ። በተለያዩ ውቅታዊና ማህበረሰባዊ ጉድለቶቻችን ዙሪያ የሚታዩ ተቃርኖዎችን በመንቀስ በሽሙጥ የሚተቸው ይህ ተውኔት በአዲስ አበባ በ10 ወራት ጊዜ ውስጥ ሰባ ሺ ታዳሚ ተመልክቶታል።

ፌስታሌን ሀገራዊ ችግሮችን ያነሳል፣ ፈጣሪውን ይሞግታል፣ ማህበረስቡን ይጠይቃል።
ከሀያ ስምንት በላይ ክፍሎች ያሉት “ፌስታሌን” ተውኔት በውጪ ሀገሮች ያሉ ኢትዮጵያውያንን ሊያስደስቱ የሚችሉ ግን ደግሞ መቸታቸውን ሀገር ቤት ያደረጉ ገቢሮች የተካተቱበት ይህ ትዕይንት በአትላንታ በዳላስ በሂዩስተን በሲያትልበሜኒሶታ በሎስ አንጀለስና በሌሎችም የአሜሪካ ግዛቶች በተከታታይ ሳምንታት ለመታየት መርሀ ግብር ወጥቷል።

የተውኔቱ ማጀቢያ ሙዚቃ በአበጋዝ ክብረወርቅ፣ በግሩም መዝሙር ፣በጆርጋ መስፍን የተቀናበረ ሲሆን ድምፃዊ በዛወርቅ አስፋውና ግዛቸው ተሾመ የራሱ የሆነ ዜማ ያንጎራጉሩለታል።

“ለዚህ ጉዞ ከዚህ ቀደም ያልቀረቡ አዳዲስ ገቢሮችን አካተናል” ሲል ግሩም ስለ ዝግጅቱ አዲስነት ይናገራል።
“ሁልጊዜ ከትናንቱ የተሻለ ሰራ ይዘን ለመቅረብ እንሞክራለን፣ እስካሁን ተሳክቶልናል። የሚደርሱን አስተያየቶች ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ተመልካቾች ተደስተው መውጣታቸውን ነው። ለዛም ይመስለኛል ስባት ጊዜ ድረስ ስዎች እየተመላለሱ ደጋግመው የተመለከቱት (በአዲስ አበባ)”

ይህ የቁም የኮሜዲ ስራ አይደለም። የሙሉ ሰዓት ተውኔት ነው። ታሪክ አለው ገፀባህሪው “እያዩ ፈንገስ” የጠፋበትን የላስቲክ ኮሮጆ (ፌስታል) መነሻ አድርጎ ወደየ አንዳንዶቻችን የህሊና ጓዳ ጠልቆ መዝባሪውን፣ ግለኛውን፣ አስመሳዩን ይጠይቃል።
የዚህ ተውኔት አብይ መልዕክት የታዳሚውን ስሜት ስቅዞ በመያዝ ያቆይና ደግሞ መልሶ ይበትነዋል፣ አዳራሹ በሳቅና በጭብጨባ ይናጣል።

“ለዚህ ትውኔት ተዋናዩ ግሩም ዘነበ ነፍስ ዘርቶበታል” ይላል ደራሲው በረከት በላይነህ።
ግሩም ዘነበ በርካታ የመድረክ ተውኔቶችን በመጫወት ላቅ ያለ ዝና ያተረፈ ባለሙያ ነው። “ዘ ፋዘር” የተሰኘ አለማቀፍ ፊልም በመተወን የትወና ችሎታውን ለህዝብ ያሳየው ግሩም “ፍቅር የተራበ” “አንቲገን” “ንጉስ አርማህ” የተሰኙ የሙሉ ሰዓት የመድረክ ተውኔቶችን ተጫውቷል። Girisho 2

“በሀገሪቱ የመናገር ነፃነት በተገደበበትና ብልሹ አሰራር በተንሰራፋበት ወቅት እንዲህ አይነቱ ተውኔት አማራጭ የመተንፈሻ መንገድ ነው” ይላል ተውኔቱን አራት ጊዜ ያህል የተመለከተው ብሩክ ካሳ ከአዲስ አበባ።
“ዋጋው ከሌሎች ትያትሮች ከፍ ይላል፣ ትኬቱን ለመግዛት ሶስት ሰዓት ያህል ቀድሞ መሰለፍ ግድ ይላል። ግሩም ሲጫወተው ማየት ግን ይክስሀል” ብሩክ ያክልበታል።
“የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች አድር ባይ በሆኑበት በዚህ ወቅት ይህን መሰሉ ህሊና ኮርኳሪና ሸንቆጥ የሚያደርግ ተውኔት መኖሩ ትልቅ አክብሮት የምሰጠው ነው” ይላል የፊልም ባለሙያው ፍፁም ዘመንፈስ።

ትዕይንቱን ሊንኬጅ አርት ይሳቃል ኢንተርቴመንትና ጣይቱ የባህል ማዕከል በጋራ ያዘጋጁት ነው።

አርጋው አሽኔ ዝርዝር አለው- በድምፅ