National Bank from internetዋዜማ ራዲዮ- ብዙ ሰፈሮች ፈርሰው እየተገነቡ ነው፡፡ አንዳንድ ሰፈሮች ግን በጣም ፈርሰው እየተገነቡ ነው፡፡ ሰንጋ ተራን በዚህ ረገድ የሚስተካከለው የለም፡፡

አይበለውና አንድ የሰንጋ ተራ ልጅ የሐረር ሰንጋ ወግቶት ሆስፒታል ገባ እንበል፡፡ “ኮማ” ዉስጥ ቆይቶ ከአምስት ዓመት በኋላ ቢነቃ ነፍሱን እንጂ ሰፈሩን ሊያገኛት አይችልም፡፡ ቢያገኛትም ከማይታመኑ ለውጦች ጋር ነው፡፡ የአዋሽ ባንክና የአዋሽ ኢንሹራንስ መንትያ ሕንጻዎች ይኮሰምኑበታል፡፡ የንጉሡ ዘመን ሰማይ ጠቃሽ “በድሉ ሕንጻ” ጊዜና እድል ጥሎት የሰፈሩ ድንክዬው ሕንጻ ይሆንበታል፡፡

ይህ የተጋነነ ልማታዊ ትንቢት አይደለም፡፡ ይህ ቀስ በቀስ እየሆነ ያለ፣ የሚታይ፣ የሚዳሰስ፣ የኮንክሪት ሥር እየያዘ የመጣ ግንባታዊ ክስተት ነው፡፡ የሸገሯ “ሰንጋተራ” የኒውዮርኩን ዎልስትሪት ለመገዳደር እየተቆረቆረች ያለች የአንድ ድሀ አገር አንድ ትንሽዬ የከተማ ጥግ ናት፡፡

ሰንጋተራ ለምን?

ለመሆኑ ይህ የራስ አበበ አረጋዊ ጎዳና ስለምን ለገንዘብ ተቋማት ዋና መሥሪያ ቤትነት ተመረጠ? ማንስ መረጠው? ለሚሉት ኮርኳሪ ጥያቄዎች እውነተኛው መልስ አጋጣሚ የሚል ብቻ ይሆናል፡፡ ያልጸደቀው አዲሱ መሪ ፕላን አሁን አሁን አካባቢውን የገንዘብ ተቋማት ጥግ አድርጎ ቢረዳውም ነገሩ ከግጥምጥሞሽነት ያለፈ መሠረት የለውም፡፡ የኦሮሚያ ባንክ የቦርድ ሊቀመንበር በአንድ ወቅት ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ባደጉት ቃለ ምልልስ “ለከተማው መስተዳደርለዋና መሥሪያ ቤት መገንቢያ የሚሆነን የመሬት ጥያቄ በሰንጋተራ አካባቢ እንዲሰጠን አመልክተን ምላሽ ተነፈግን” ሲሉ አማረው ነበር፡፡ የአዲስ አበባ መስተዳደር በበኩሉ ለፋይናንስ ተቋም ብዬ የከለልኩት ቦታ የለኝም፣ ባንኮች ሰንጋ ተራ እየሄዱ ያሉት በራሳቸው ምርጫ ነው፤ መሬት ማግኘት የሚቻለው በጨረታ አግባብ ብቻ ነው” ሲል በወቅቱ ምላሽ ሰጥቶ ነበር፡፡

ይህንኑ የሐሳብ ዉልዉል የሚያጠናክር ሌላኛው ክስተት በ20ኛው ዙር የሊዝ ጨረታ ተከስቶ ነበር፡፡ በሜክሲኮና ሰንጋ ተራ መሐል የሚገኝ ስፋቱ 1043 ካሬ የሚሆን ቦታ ለጨረታ ከቀረበ በኋላ ጨረታው የታተመበት አዲስ ልሳን ጋዜጣ ስር አንድ አወዛጋቢ አረፍተ ነገር ተጽፎ ነበር፡፡ ይኸውም “የዚህ ቦታ ተጫራቾች በተለይ የፋይናንስ ተቋማት ቢሆን ይመረጣል” የሚል አሻሚ ሐሳብን ያሰፈረ ሐረግ ነው፡፡ የኋላ ኋላ መስተዳደሩ የተጻፈው ነገር ለራሱም ግራ ገባው መሰል ጨረታውን በከፊል ለመሰረዝ ተገደደ፡፡

በቀጣይ ጨረታ በድጋሚ ያው ይዞታ ሲወጣ ግን ለቦታው መወዳደር የሚችሉት የፋይናንስ ተቋማት ብቻ እንደሆኑ በማያሻማ ቋንቋ ተጠቅሶ ነበር፡፡ ይህ የሚያሳየው መስተዳደሩ አካባቢውን በዋናነት የገንዘብ ተቋማት እንዲሰፍሩበት ዉስጥ ዉስጡን የሚሻ ቢሆንም ይህን የሚደግፍ ሕጋዊ አግባብ ለማግኘት ግን ተቸግሮ መቆየቱን ነው፡፡ ይህን ዉሳኔውን ተከትሎም ቡና ባንክ፣ ፀሐይ ኢንሹራንስ፣ ደቡብ ግሎባል ባንክ እና እናት ባንክ በወቅቱ ለጨረታ የቀረበውን 1043 ካሬ ሜትር ቦታ ለመውሰድ ከፍተኛ ፉክክር አድርገው ቡና ባንክ ለካሬ 66ሺ ብር በማቅረብ ይዞታውን ማስከበር ችሏል፡፡ እንደ ባልንጀሮቹ ሰፈሩን የሚመጥን፣ ሰማይ የሚቧጥጥ ሕንጻን ማቆም መቻሉን ግን ባንኩም ቢሆን እርግጠኛ አይደለም፡፡ ቡና፣ ደቡብ ግሎባልና እናት ባንኮች ጠንቻቸው ገና ያልፈረጠመ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ወደፊት በአንድ የመጠቃለል እጣ እንደሚጠብቃቸው ይገመታል፡፡

የኾኖው ኾኖ የሰንጋ ተራና የገንዘብ ተቋማቱን መስተፋቅር ግጥምጥሞሽ ብቻ እንዳይመስል ያደረጉ ምክንያቶች አልጠፉም፡፡ ለምሳሌ የገንዘብ ተቋማት አለቃ የሆነው የብሔራዊ ባንክ መቀመጫው እዚው ግድም መሆኑ፤ በሥነ ሕንጻ ዉበቱ ወደር የማይገኝለት ወርቃማው ባንክም በዚያው ሰፈር መገኘቱ፣ ለአካባቢው ሌላ አክሊል ሳይደፋለት አልቀረም፡፡ በአገሪቱ በገንዘብና ሥነ ምጣኔ ዘርፍ ባለሞያን የሚያፈራው ቀደምቱ የንግድ ሥራ ኮሌጅ የሚገኘውም በዚሁ የከተማዋ ክልል መሆኑ የገንዘብ ተቋማቱ ወደዚህ ሰፈር ለመሳብ ሌላ ምክንያት፣ ሌላ ጉልበት ሳይሆንላቸው አልቀረም፡፡

የአጋጣሚ ነገር ኾኖ ቀድመው የተቋቋሙትም ሆነ አዲስ የሚገነቡት የገንዘብና የመድን ሰጪ ተቋማት በዚሁ ቀበሌ በቅርብ ርቀት ፈንጠርጠር ብለው የሰፈሩ ናቸው፡፡ የመድን ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት ለገሀር ነው፡፡ ከሰንጋ ተራ በእርምጃ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ወጋገን ባንክ ያስገነባው የናኒ ሕንጻ እኩያ ባለ 23 ወለል ሕንጻ የሚገኘው በራስ መኮንን ጎዳና ስቴዲየም ላሊበላ ሆቴል ጎን ነው፡፡ ለጊዜው የአገሪቱ ረዥም ሕንጻ ለመሆን ችሏል፡፡ ይህ ጽሑፍ ሲዘጋጅ ግንባታው በአመዛኙ ተጠናቆ ዉስጡን የማስዋብ ሂደት ላይ ነበር፡፡ ለወጋገን ገንቢ የቻይናው ጂያንግዚ ኮርፖሬሽን አንድ ቢሊዮን ብር ተከስክሶለታል፡፡ ይህ ግዙፍ ሕንጻ ከሰንጋ ተራ ብዙም ርቆ አይገኝም፡፡ የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና የሎጂስቲክ አገልግሎ ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት ግንባታ እየተጠናቀቀ ያለውም ከመድን ድርጅት ጀርባ ነው፡፡ ሁሉም ከሰንጋ ተራ የ10 ደቂቃ እርምጃ ያህል ቢርቁ ነው፡፡

ከባሕር ትራንስርፖት ሕንጻ ፊት ለፊት አቢሲኒያ ባንክ የአያት እህት ኩባንያ ከሆነው ሳካ አክሲዮን ማኅበር በ400 ሚሊዮን ብር ዋጋ የገዛው ባለ 15 ወለል መንታ ፎቅ ይገኛል፡፡ 3ሺ ካሬ ላይ ያረፈ ሕንጻ ቢሆንም ቅድመ ዲዛይኑ ለአፓርትመንት ታስቦ የተደዘነ ስለነበር ሕንጻው ለባንኩ ብዙም ምቾት የሰጠው አይመስልም፡፡ ለዚህም ይመስላል ግዡው ከተፈጸመ ዓመታት ቢቆጠርም ሕንጻው አናት ላይ የባንኩን ስም ከማጻፍ የዘለለ ሥራ ያልተሠራው፡፡ ዉስጥ አዋቂዎች እንደሚሉት አቢሲኒያ ባንክ ጊዜ ወስዶም ቢሆን ወደፊት በለስ ቀንቶት ቦታ ካገኘ ወደ ሰንጋ ተራ የመምጣት ጥልቅ ፍላጎት አለው፡፡ አሁን የአቢሲኒያ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በኪራይ የተገኘ ነው፡፡

መድን ሰጪዎቹ

አሁን በአገሪቱ 17 መድን ሰጪ ተቋማት በብሔራዊ ባንክ እውቅና አግኝተው በሥራ ላይ ሲሆኑ ከነዚህ ዉስጥ ሲሶ የሚሆኑት የዋና መሥሪያ ቤት ግንባታን አቅደዋል፡፡ በጣት የሚቆጠሩት ግንባታቸውን አገባደዋል፡፡ ከፊሎቹ የቁፋሮ ሥራ ላይ ናቸው፡፡

ለምሳሌ ናይል ኢንሹራንስ “ጅዳው ኮንሰልት”ን በአማካሪነት፣ ወሰን አርክቴክትን በደዛኝነት፣ ራማ ኮንትራክተርስን ደግሞ በገንቢነት አሰማርቶ ባለ 22 ወለል ዋና መስሪያ ቤቱን ግንባታ እያቀላጠፈው ሲሆን ይህ ጽሑፍ ሲዘጋጅ 5ኛ ፎቅ የ”ስላብ” ሙሊት እየተካሄደ ነበር፡፡ ናይል ኢንሹራንስ የሚገኘውም ከወርቃማው ባንክ በቅርብ ርቀት ነው፡፡

ከናይል ኢንሹራንስ የሚጎራበተው የአቶ ከተማ ከበደ (ኬኬ ኢንተርናሽናል) በጅምር የቀረ የ22 ፎቅ አጽመ ሕንጸ ነው፡፡ በ5ሺ ካሬ የወለል ስፋት የሚገኘው ይህ ሕንጻ የወለሎች ሙሊት ሙሉ በሙሉ ከተጠናቀቀ ዘመን የለውም፡፡ ከ12 ዓመታት በፊት በድርድር ሊዝ በካሬ 3600 ብር ስሌት ብቻ በ7 ሚሊዮን ብር ክፍያ ቦታውን ከመስተዳደሩ የተረከቡት አቶ ከተማ ሕንጻውን ለአገለልግሎት ሳያበቁት በሙስና ተጠርጥረ ማረሚያ ወርደዋል፡፡

ይህን ተከትሎም ሕንጻው ባለበት ሁኔታ ለሽያጭ ቀርቦ ነበር፡፡ ስምንት መቶ ሚሊዮን ብር ዋጋ ተቆርጦለት የነበረ ሲሆን ለረዥም ጊዜ ገዢ ባለማግኘቱ እንደቆመ ቀርቷል፡፡ ከዓመታት በፊት የአሮሚያ ኢንሹራንስ ይህን ሕንጻ ለመግዛት ድርድር ጀምሮ የነበረ ሲሆን በዋጋው መናር ምክንያት የቦሌውን ጋራድ ሕንጻ በ220 ሚሊዮን ብር በእጁ አስገብቷል፡፡

በኢትዮጵያ የመጀመርያው የኢንሹራንስ ኩባንያ ናይስ ዋና መሥሪያ ቤት ሕንጻ ለመገንባት ለብዙ ዓመታት ሞክሮ አልተሳካለትም፡፡ ናይስ ኢንሹራንስ በአንድ ወቅት እንዲያውም በብስጭት የኩማ ደመቅሳን አስተዳደር ፍርድ ቤት ለመክሰስ ተቃርቦ ነበር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ቴዎድሮስ አደባባይ ለዋና መሥሪያ ቤት ግንባታ ለወሰድኩት 1800 ካሬ ቦታ መስተዳደሩ የግንባታ ፍቃድ ሰጥቶ ሊያሰራኝ አልቻለም በሚል ነበር፡፡ ከብዙ አመታት እሰጥ አገባ በኋላ ናይስ ስመጥሩን የሕንጻ ተቋራጭ ቫርኔሮን ባለ 12 ወለል ሕንጻ በ140 ሚሊዮን ብር ገንባልኝ ብሎ ተዋውሎት የሕንጻው ምስል በቴዎድሮስ አደባባይ ለመስቀል በቅቶ ነበር፡፡ መጠነኛ ቁፋሮ ከተጀመረ በኋላ ግን አሁንም ግንባታው ባልታወቀ ምክንያት ቆሟል፡፡ የተቆፈረው ቦታ ኩሬ ሰርቶ በቅርቡ ለሦስት ሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት ሆኗል፡፡ ሕይወት በመድን ሽፋን አትመለስ ነገር፡፡

ከናይስ የግንባታ ስፍራ በቅርብ ርቀት በቸርችል ጎዳና ሐሮን ሕንጻ ማዶ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ የሚመሩት ሕብረት ኢንሹራንስ 15 ፎቅ ሕንጻን በዛምራ ተቋራጭነት አስገንብቶ አጠናቋል፡፡ ጌረታ ኮንሰልቲንግ ንድፉን በመሥራትና በሕንጻ ግንባታ ቁጥጥር ሥራ ተሳትፏል፡፡ ዛምራ ከሰሞኑ ሌላ ሁለት መቶ ሚሊዮን ብር ተጨምሮለት የማጠናቀቂያ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡

Awash Bank HQ
Awash Bank HQ

የሰንጋ ተራ የባንክ ክምችቶች

ሰንጋ ተራ የኦሮሚያው የልማት ድርጅት የሚቆጣጠረው የቢፍቱ ሕንጻ በመሐል መሰንቀር ካልሆነ በስተቀር ከብሔራዊ ጫፍ እስከ ሜክሲኮ አደባባይ የሚገኙ መሬቶች በፋይናንስ ተቋማት የተያዙ ናቸው፡፡ ከናይል ኢንሹራንስ ይዞታ በተከታይ የሚገኙት የንብ ባንክ ባለ 37 ወለል ሕንጻ፣ የዘመን ባንክ ባለ 31 ወለል ሕንጻና የሕብረት ባንክ ባለ 33 ወለል የዋና መሥሪያ ቤት ጅምር ሕንጻዎች ናቸው፡፡

ንብ ባንክ ከወለል በታች 4፣ ከወለል በላይ 37 ፎቅ ለማስገንባት ዉል ያሰረው ከቻይናው ጂያንግሱ ኢንተርናሽናል ጋር ነው፡፡ በ4 ዓመታት ዉስጥ ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃል የተባለው ይህ ሕንጻ ስንት ገንዘብ ፈለገ የሚለው እስከዛሬም በሚስጢር የተያዘ ጉዳይ ነው፡፡ ዉስጥ አዋቂዎች ወጪውን 1.8 ቢሊየን ያደርሱታል፡፡

ጂያንግሱ ኢንተርናሽናል ከንብ ባንክ ጋር ለመፈራረም ያስቻለውን ዋጋ ያቀረበው አጠገቡ የሕብረት ባንክን እየገነባ ስለሚገኝ የሎጂስቲክ ወጪን ስለሚቀንስለት ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል፡፡ የቁፋሮ ሥራውን በ40 ሚሊዮን ብር ቀደም ብሎ ካጣቀቀ በኋላ ከቻይናው ጂያንግሱ ኢንተርናሽናል በ1.5 ቢሊዮን ብር 30 ፎቅ ሕንጻ ለማስገንባት የተዋዋለው ሕብረት ባንክ ከቡና ባንክ የወደፊት ዋና መሥሪያ ቤቱን ይጎራበታል፡፡

በአንድ ጊዜ ሁለት መቶ መኪኖችን የሚያሳርፍ 4 ወለል ወደታች የሚዘልቅ ምድር ቤት የሚኖረው ይህ ሕንጻ በ3 ዓመት ተኩል ግንባታው ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡ በስፍራው ገዘፍ ያለ ኮንክሪት ማሟሻ (Batching Plant) በመትከል ግንባታውን ያለ እረፍት እያከናወነ የሚገኘው ጂያንግሱ በአካባቢው የዉኃ ምንጭ መኖሩ በስራው ላይ መጠነኛ መጓተት ቢያስከትልበትም አያያዙ ፈጣን ይመስላል፡፡ የሼክ አላሙዲንን ደርባ ሲሚንቶ የፋብሪካ ግንባታና ተከላ ያከናወነው ይኸው የቻይና ኩባንያ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ከሕብረት ባንክ ቀጥሎ የ3ሺ 3መቶ ካሬ ቦታን የሚጎራበተው ዘመን ባንክ ነው፡፡ ካወዳደራቸው ዲዛይኖች ጅዳው ኮንሰልት በተባለ ኩባንያ የቀረበን ንድፍ አጽድቆ 31 ወለሎችን የሚይዝ ዋና መሥሪያ ቤት ይገነባል፡፡ ይህ የዘመን ባንክ ኪነ ሕንጻ የባንኩን ዘመናዊነት እንደ ስሙ ለማንጸባረቅ የመስታወት ሕንጻ ዘዬን (Curtain Wall) እንደዋንኛ አማራጭ እንደወሰደ አይቶ መፍረድ ይቻላል፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት ይህ ዲዛይን ሲጸድቅ ግንባታው 450 ሚሊዮን ብር እንደሚፈጅ ተገምቶ ነበር፡፡ በቅርቡ ከገንቢው ጋር ዉል ሲፈጣጠም ግን ይህ ወጪ ወደ አንድ ቢሊዮን ተመንድጓል፡፡

ኦሮሚያ ኢንሹራንስና ኦሮሚያ ባንኮች ሜክሲኮ አደባባይ አቅራቢያ የቡናና ሻይ ሕንጻን በሚጎራበት መሬት ሰፊ ይዞታን ከሰሞኑ አስከብረዋል፡፡ ቦታው በምን አግባብ ለባንኮቹ እንደተሰጠ ግልጽ ባይሆንም አገሪቱ በተቃውሞ እየተናጠች በነበረበት የወዲያኛው ሳምንት ለዋና መሥሪያ ቤት ሕንጻ የመሠረት ድንጋይ በስፍራው እንዲቀመጥ ተደርጓል፡፡

የንግድ ባንክ አዲስ የግንባታ ምዕራፍ

ንግድ ባንክ ገዘፍ ላሉ ሕንጻዎች ግንባታ አዲስ አይደለም፡፡ በመገናኛ ግሩም ሕንጻ አስገንብቶ ለአገልግሎት አብቅቷል፡፡ በልደታ ተክለብርሃን አምባዬ እየገነባው የሚገኝ ሌላ ሕንጻ ይገኛል፡፡ በቅርቡ ኢትዮጵያ ሆቴል ጀርባ እየተገነባ ያለው የንግድ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት ግን የምሥራቅ አፍሪካ ረዥሙ ፎቅ እንደሚሆን የሚጠበቅ ነው፡፡

በ11ሺ ካሬ ላይ ያረፈውና 198 ሜትር የሚረዝመው ይህ ግንባታ 46 ወለሎች ይኖሩታል፡፡ ገንቢው በ20 አገራት ግዙፍ ግንባታዎችን ያካሄደ፣ ከ80 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ የግንባታ ዉል የፈጸመ እውቅ አህጉር ዘለል ተቋራጭ ሲሆን በቻይና መንግሥት ወጪው የተሸፈነውን አዲሱን የአፍሪካ ሕብረት ዋና ጽሕፈት ቤት የገነባው ይኸው በቻይና መንግሥት የሚተዳደር ተቋራጭ ነው፡፡

“የቻይና መንግሥት ኢንጂነሪንግ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን” የሚል አቻ ስያሜ ያለው “ሲኤሲኢሲ” ለንግድ ባንክ አራት የምድር ወለሎችንና የመሬት ቁፋሮ ሥራን አጠናቆ ከሰሞኑ ቀና ማለት ጀምሯል፡፡ ከጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል አቅጣጫ ሲታይ ከሰሞኑ የቆሙ የኮንክሪት ምሊቶች ለግንባታ ይዞታው ማስከበርያ ከተገነባው የግንብ አጥር በልጠው መታየት ጀምረዋል፡፡

አዲስ የግንባታ ታሪክ ለመስራት ያሰበውም ከዚህ በኋላ ነው፡፡

የግንባታ መቶ ሜትር

ግንባታ በኢትዮጵያ ዉስጥ ማራቶን እንጂ መቶ ሜትር ሆኖ አያውቅም፡፡ ይህ እየተቀየረ ይመስላል፡፡ ለምሳሌ ቦሌ ጃፓን ማዶ ዎርቤክ ሕንጻ ጎን ተክለብርሃን አምባዬ እየገነባው የሚገኘው ቀጠን ረዘም ያለ የአፍሪካ ኢንሹራንስ ባለ 13 ወለል ሕንጻ አጽመ ግንባታው የፈጀው ጊዜ አንድ የአራስ ልጅ ጡት ለመጣል ከሚፈጅበት ትንሹ ጊዜ ያነሰ ነው፡፡ በአራት ወራት ብቻ ሙሉ ወለል ተሞልቶ ማለቁ በዚያ ጎዳና ለሚመላለሱ ሁሉ መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል፡፡ አሁን የብሎኬት ድርደራና የልስን ሥራዎች በመገባደድ ላይ ናቸው፡፡ ተክለ ብርሃን አምባዬ በመገናኛ ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች የሚገነባቸው አፓርትመንቶች፣ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ግቢ የገነባው ቤተ መጽሐፍትና የተማሪ መኖርያ፣ በተመሳሳይ ሁኔታ በአነጋጋሪ ፍጥነት ለመጠናቀቅ ተቃርበዋል፡፡ ሁለቱም ቦታዎች ግንባታቸው ከዓመት ተኩል የበለጠ ጊዜን አልወሰደም፡፡

ለዚህም ይመስላል ባሳለፍን ወር ግንባታውን ለቻይናውያን አሳልፎ የሰጠውን ንብ ባንክን ፍርድ ቤት ለመገተር የደፈረው፡፡ ንብ ባንክ ለአገር ዉስጥ ተቋራጮች የሚሰጠውን የ7 በመቶ የዋጋ ቅናሽ ልዩነት ቸል ብሎ ዋና መሥሪያ ቤቱን እንዲሠራለት የመረጠው የቻይናውን ጂያንግሱ ኢንተርናሽናል ኩባንያን መሆኑ ከፍ ብሎ የተጠቀሰ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ በውድድሩ ሁለተኛ ለወጡት አቶ ተክለብርሃን አምባዬ የሚዋጥላቸው አልሆነም፡፡ ቻይናዎች የንብ ባንክን ባለ 37 ወለል ሕንጻ በ4 ዓመት ነው ለመጨረስ የተፈራረሙት፡፡ “እኛ በ3 ዓመት ለማጠናቀቅ እንፈራረም ብለናቸው እምቢ ብለዉናል” ይላሉ የተክለብርሃን አምባዬ ኃላፊዎች በቅርቡ በሰጡት ቃለ ምልልስ፡፡

በርግጥ በግንባታ ፍጥነት ከቻይናዊያን ግዙፍ ኩባንያዎች እበልጣለሁ ማለት በራሱ ትልቅ አቅምን የሚጠይቅ ይመስላል፡፡ ተክለብርሃን አምባዬ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተግባር እያሳዩ ያሉት ግን የቻይኖቹን ፍጥነት ለመገዳደር ክፍለ ዘመን መጠበቅ እንደማያስፈልጋቸው ነው፡፡

በአንድ ሳምንት አንድ ፎቅ

የኾነው ኾኖ እስካሁን ከተዘረዘሩ የባንክና ፋይናንስ ተቋማት ሁሉ የሚረዝመው ፎቅ የሚጠናቀቀው ከሁሉም ሕንጻዎች ቀድሞ ነው፡፡ 46 ወለል ወደላይ የሚመዘዘው የንግድ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት ሕንጻ በቁመት የሚያንሱትንም ሆነ ቀድመው የተጀመሩትን ሕንጻዎች ሁሉ ቀድሞ 46ኛ ፎቅ ላይ ይሰየማል፡፡ ሚስጥር የገንቢውና የአስገንቢው አቅም መጎልበት ነው፡፡

ከንግድ ባንክ ኢትዮጵያዊ መሐንዲሶች ዋዜማ ያገኘችው መረጃ እንደሚያስረዳው ከሚቀጥለው ወር በኋላ ተቋራጩ የቻይና መንግሥት ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ ኩባንያ በአንድ ሳምንት አንድ ፎቅ ይጨርሳል፡፡ ይህም ማለት በአንድ ወር 4 ፎቆችን ገንብቶ ያጠናቅቃል ማለት ነው፡፡ በዚህ ሂደት ተቋራጩ ሁሉንም 46 ወለሎች ጨርሶ ለመገንባት ከ12 ወራት በላይ በምንም ተዓምር አይወስድብኝም እያለ ነው፡፡ ይህ በኢትዮጵያ የግንባታ ታሪክ ክብረወሰን ኾኖ ሊመዘገብ የሚገባው ነው፡፡ ምንም እንኳ የክብረ ወሰኑ ባለቤት ቻይናዉያን ቢሆኑም፡፡

በሁለት ጥልፍልፍ ክሬኖች የተዋቀረው የንግድ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት ግንባታ ከሰሞኑ አጥሩን አልፎ ማቆጥቆጥ ከመጀመሩ በፊት የዋዜማ ዘጋቢ ቦታውን የመጎብኝኘት እድል አግኝቶ ነበር፡፡ ለመሠረት የተሞላ ኮንክሪት ዉሀ አምቆ እንድይዝ በመቶ የሚቆጠሩ የደብረብርሃን ብርድልብሶች በዉሀ ተዘፍዝፈው ተነክረው መመልከቱ ግርምትን ፈጥሮበታል፡፡ ባለ አራት ክዳን ኮንክሪት ማማሰያ (Batching Plant) ተተክሎ ቀን ተሌት ይሠራሉ፡፡ ለቻይኖቹ ማደርያ ከብሔራዊ ቴአትር ማዶ በአቶ አብነት ገብረመስቀል ባለቤትነት የተያዘውና “ኦዳ ታወር” እንደሚገናበበት ይጠበቅ የነበረውን ባዶ ቦታ በኪራይ ተበርክቶላቸዋል፡፡ እነርሱም በብረት የተዋቀረ ባለ 2 ፎቅ ማደርያ ቤቶችን ገንብተው በማረፊያነት ይጠቀሙበታል፡፡ እነዚህን ማደርያ ቤቶች ለመሥራት ከአንድ ወር በላይ አልወሰደባቸውም፡፡

ባንኮቻችን ለምን ሕንጻ ይገነባሉ?

በዚህ የሰንጋ ተራና አካባቢው የፋይናንስ ተቋማት ለዋና መሥሪያ ቤት ግንባታ እየከሰከሱ ያሉት የብር መጠን አንድ ላይ ቢደመር ሌላ አንድ ግለገል ጊቤ የሚያስጨርስ ነው፡፡ የኤቲኤም ማሽን እንኳ ያልተከሉ ባንኮች ስለምን ለዋና መሥሪያ ቤት ግንባታ ይንሰፈሰፋሉ የሚለው ኮርኳሪ ጥያቄ ነው፡፡ አንዳንድ ባለሞያዎች ገንዘቡን ለባንኪንግ ቴክኖሎጂ ማበልጸጊያ ወይም ለብድር አቅርቦታ ቢያዉሉት አገርም ባንክም ይበልጥ ይጠቀማል ብለው ያስባሉ፡፡ ሌሎች በተቃራኒው የዋና መሥሪያ ቤት ግንባታ በፍጹም የሚኮነን ተግባር አይደም ይላሉ፡፡

እንደነርሱ እምነት ባንኮቻችን ከጥሬ ገንዘብ ይልቅ ቋሚ ንብረት (Fixed Asset) ላይ አንጡራ ሀብታቸውን መከስከሳቸው ፋይዳው በርከት ይላል፡፡ አንዱና ዋንኛው በደንበኞቻቸውና በባለአክሲዮኖቻቸው ላይ የሚፈጥሩት የመተማመን ከፍታ ነው፡፡ ባንኮች ገዘፍ ያለ የሚታይ የሚዳሰስ ንብረት በስማቸው ማቆማቸው የደንበኞችን እምነት ያደረጃል፡፡ ከዚያም ባሻገር የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ በሌለበት አገር ገንዘብን በቋሚ ንብረት እንደማሳረፍ ብልህ ተግባር የለም፡፡

ብሔራዊ ባንክ የግል ባንኮች የቅርንጫፍ ብዜታቸውን በየዓመቱ 30 በመቶ እንዲያዋልዱ ያስገድዳቸዋል፡፡ ይህም ለሕንጻ የሚያወጡትን የኪራይ ወጪ ያንረዋል፡፡ የብዙዎቹ የግል ባንኮች 30 በመቶ ወጪ የሚወጣው ለቦታ ኪራይ ነው፡፡ አሁን ባለው የአገር ዋጋ ለካሬ ሜትር እስከ 700 መቶ ብር እየከፈሉ በኪራይ መዝለቅ ለግል ባንኮች ወርሃዊ ቁንጥጫ ኾኖባቸዋል፡፡ የራሳቸውን ሕንጻዎች ሲገነቡ ግን ወጪያቸውን ሸፍነው ትርፍ ክፍሎቻቸውን አከራይተው ጠቀም ያለ ትርፍን መቋጠር ያስችላቸዋል፡፡

ዳሽን ባንክ በመላ አገሪቱ 31 ሕንጻዎችን ገንብቷል፡፡ ንብ ባንክ የአዲስ አበባውን ጨምሮ በአዋሳና ድሬዳዋ የራሱን ሕንጻዎች በፍጥነት እያስገነባ ነው፡፡ አዋሽ 15 የሚጠጉ ሕንጻዎችን ከዋና ከተማ በተጨማሪ በሐረር፣ በጅማ፣ በበደሳ በባለቤትነት ያስተዳድራል፡፡ አቢሲኒያም በአዲስ አበባ ልዩ ልዩ ቦታዎች ሕንጻ ገዝቶ ቢሮ እያስገነባ ነው፡፡ ለአንድ ባንክ ጤናማው የሕንጻ ቁጥር ግን ስንት ነው?