ዋዜማ ራዲዮ-የ”ሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ” አባላት የነበሩ እና ከኮሚቴው ጋር በተያያዘ በሽብር ተከስሰው ከተፈረደባቸው ሙስሊሞች መካከል ዘጠኙ ከአራት አመት እስር በኋላ ዛሬ በምህረት ተለቀቁ፡፡
ከኮሚቴው አባላት መካከል ዛሬ የተፈቱት እስረኞች ኡስታዝ አቡበከር አህመድ፣ ሼህ መከተ ሙሄ እና ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ ስድስት እስረኞች በአቡበከር አህመድ መዝገብ ስም ተከፍቶ በነበረው የሽብር ክስ ከሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ጋር ግንኙነት አላችሁ በሚል ተፈርዶባቸው የነበሩ ሲሆኑ እነርሱም ኢንጅነር በድሩ ሁሴን፣ ሙባረክ አደም፣ ሰይድ አሊ፣ ጋዜጠኛ ዩሱፍ ጌታቸው፣ ኑሩ ቱርኪ እና ሙራድ ሽኩር ናቸው፡፡
ዘጠኙ ሙስሊም እስረኞች የኢትዮጵያ መንግስት አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ ምህረት ካደረገላቸው 707 እስረኞች ውስጥ የተካተቱ ናቸው፡፡ በዝዋይ እና ቃሊቲ ይገኙ የነበሩት እነዚህ እስረኞች ከሐሙስ ዕለት ጀምሮ ወደ ሰንዳፋ ፖሊስ ኮሌጅ ተወስደው በመንግስት በኩል ይሰጥ በነበረው ገለጻ ላይ ሲሳተፉ እንደቆዩ ምንጮች ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡
የተፈቺ ቤተሰቦች ቅዳሜ ጠዋት 2፡30 ላይ በቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንዲገኙ በተነገራቸው መሰረት ወደዚያው ማምራታቸውን የሚናገሩት ምንጮች ሶስት ሰዓት ገደማ ላይ የቤተሰብ አባላትን እየጠሩ ወደ ማረሚያ ቤቱ ቅጽር ግቢ እንዳስገቧቸው ይናገራሉ፡፡ ከጥቂት ቆይታ በኋላ የተፈቺ ቤተሰቦች በመኪና ተጭነው ወደ ሰንዳፋ እንደተወሰዱ ያብራራሉ፡፡
ከቀትር በኋላም እስረኞቹ ተፈትተው ከቤተሰብ ጋር መቀላቀላቸውን ምንጮች አስረድተዋል፡፡ ከሙስሊም መሪዎቹ ጋር ከሰንዳፋ የተለቀቁት እስረኞች ብዛት 175 እንደሆነ ምንጮች ለዋዜማ አስረድተዋል፡፡ከዛሬዎቹ ተፈቺዎች መካከል 20 ያህል የሚሆኑት ከማዕከላዊ የተለቀቁ ናቸው። በማዕከላዊ መርማሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ጭንቀት እንደሚነበብ የገለጹት ምንጮች ለተፈቺዎቹ “ሀገሪቱ በአደጋ ላይ ነች” ሲሉ መናገራቸውን ያስረዳሉ። መርማሪዎቹ “አሁን የሁሉም ርብርብ የሚያስፈልግበት አስቸጋሪ ጊዜ ነው” በማለት የተፈቺዎችን እገዛ እንደጠየቁም ታውቋል።
የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ላነሷቸው ከሃይማኖት ነጻነት ጋር ለተያያዙ ጥያቄዎች መፍትሄ እንዲያፈላልግ እና ከሚመለከታቸው የመንግስት ባለስልጣናት ጋር እንዲነጋገር ከአምስት አመት በፊት በህዝብ ተመርጦ የተቋቋመው ኮሚቴ 17 አባላት የነበሩበት ነበር፡፡ እየተጠናከረ የመጣው የሙስሊሞች እንቅስቃሴ ያሰጋው የኢትዮጵያ መንግስት ከኮሚቴው አባላት ውስጥ የተወሰኑትን እና በህዝበ ሙስሊሙ ዘንድ ተደማጭነት የነበራቸውን ግለሰቦች በሐምሌ 2004 ዓ.ም ለእስር ዳርጓል፡፡
ከአራት ወራት ቆይታ በኋላ በጥቅምት 2005 ዓ.ም 28 ሙስሊሞች እና ሁለት ድርጅቶች የተካተቱበት የሽብር ክስ በአቡበከር አህመድ ስም ተከፍቶ ጉዳዩ ለሶስት ዓመታት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲታይ ቆይቷል፡፡ ከፍተኛ ትኩረት ስበው ከነበሩ ፖለቲካ ቀመስ የፍርድ ሂደቶች አንዱ በነበረው በዚህ ክስ ከነበሩ መከላከል በጣት የሚቆጠሩት ቀደም ብለው በነጻ ተለቅቀው ነበር፡፡
የፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ሐምሌ 26 ቀን 2007 ከ22 ዓመት እስከ ሰባት ዓመት የሚደርሱ ቅጣቶች በቀሪዎቹ እስረኞች ላይ አስተላልፎ ነበር፡፡ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ጉዳዩን የሚከታተሉ ወገኖችን አስደንግጦ እና አሳዝኖ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ከፍርዱ ጥቂት ቀናት በኋላ ግን በዚህ መዝገብ የተፈረደባቸው አምስት ሙስሊሞች እንዳሁኑ አዲስ አመትን ምክንያት በማድረግ ምህረት ተደርጎላቸው ከእስር
ተለቅቀዋል፡፡ በወቅቱ የተፈቱት 22 ዓመት ተፈርዶበት የነበረው ኡስታዝ ያሲን ኑሩ ፣ እያንዳንዳቸው 18 ዓመት የተፈረደባቸው ጋዜጠኛ አቡበከር አለሙ፣ ሙኒር ሁሴን እና ሳቢር ይርጉ እንደዚሁም ሰባት ዓመት የተፈረደበት ሼክ ባህሩ ኡመር ነበሩ፡፡
ከዓመት በኋላ በተመሳሳይ ሁኔታ ዛሬ የተፈቱት ኡስታዝ አቡበከር እና ኡስታዝ ካሚል እያንዳንዳቸው 22 ዓመት ተፈርዶባቸው ነበር፡፡ ሼህ መከተ እና ኢንጅነር በድሩ የ18 ዓመት እስራት ተላልፎባቸው የነበረ ሲሆን ሙባረክ እና ሰይድ ደግሞ የ15 ዓመት እስር ተወስኖባቸው ነበር፡፡ ሌሎቹ ተፈቺዎች ጋዜጠኛ ዩሱፍ፣ ኑሩ እና ሙራድ ደግሞ የሰባት ዓመት ፍርደኞች ነበሩ፡፡
በዚህ መዝገብ ውስጥ ተፈርዶባቸው እስር ቤት የቀሩት አራት ናቸው፡፡ በጻፋቸው ታሪክ ቀመስ መጽሀፍቱ ይበልጥ የሚታወቀው እና 22 ዓመት የተፈረደበት አህመዲን ጀበል እንደዚሁም የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ጸሀፊ የነበረው እና 18 ዓመት የተፈረደበት አህመድ ሙስጠፋ እስካሁንም ካልተፈቱት ውስጥ ናቸው፡፡ 18 ዓመት የተፈረደበት ሙሃመድ አባተ እና 15 ዓመት እስራት የተወሰነበት ካሊድ ኢብራሂም አሁንም በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡