ዋዜማ ራዲዮ -The Life and Times of Menelik II በሚል ርዕስ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1961 ተጀምሮ በ1975 የተጠናቀቀውና በአሜሪካዊው ሀሮልድ ጂ ማርከስ ተጽፎ የነበረው መጽሐፍ በዚህ ሳምንት መግቢያ ላይ ወደ አማርኛ ተመልሶ ለአንባቢዎች ቀርቧል፡፡
ስድስት መቶ ገጾችን ሊሞላ ጥቂት የቀረው ይህ ባለ ወፍራም ጥራዝ መጽሐፍ ወደ አማርኛ የተመለሰው “የዐጼ ምኒልክ የሕይወት ታሪክ እና የሥልጣን ዘመን” በሚል ርዕስ በአቶ ቢኒያም ዓለማየሁ አማካኝነት ነው፡፡
የእንግዝኛ ደራሲው ዶክተር ሀሮልድ ጂ ማርከስ የተወለዱት እንደ ጎርጎሳዊያኑ አቆጣጠር በ1936 በአሜሪካ ማሳቹሴትስ ሲኾን የሞቱት በ66 ዓመታቸው የዛሬ አስራ አራት ዓመት ገደማ ከልብ ሕመም ጋር በተያያዘ ነው፡፡ የፒኤች ዲ ዲግሪያቸውን ያገኙት እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1964 ከቦስተን ዩኒቨርስቲ ሲኾን ከዚያ ጥቂት ቀደም ብሎ ለዲግሪያቸው ማሟያ ጥናት ለማድረግ ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ ወዲህ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ልዩ ፍላጎት እንዳደረባቸው ይናገራሉ፡፡ የመመረቂያ ወረቀታቸውን የሠሩትም በኢትዮጵያና በእንግሊዝ ዲፖሎማሲያዊ ግንኙነት ላይ ነው፡፡
በኢትዮጰያ ዙርያ የሚያጠነጥኑ በርካታ የጥናት ጽሑፎችን ያቀረቡትም ከዚህ ጊዜ ወዲህ እንደኾነ ይነገራል፡፡ዶክተር ሀሮልድ የንጉሥ ምንሊክን ታሪክ በስፋት ከመጻፋቸው ባሻገር የአጼ ኃይለሥላሴን የሥልጣንና ዘመንና ግለ ታሪክ HaileSellasie፡ The formative Years፡ 1892-1936 በሚል ርዕስ እ.አ.አ በ1987 በመጽሐፍ መልክ አቅርበዋል፡፡
በሚቺጋን ስቴት ዩኒቨርስቲ የታሪክና የአፍሪካ ጥናት ፕሮፌሰር የነበሩት ዶክተር ሀሮልድ የዘመናዊት ኢትዮጵያንና የአፍሪካ ቀንድን ታሪክ በስፋት በማጥናትና መጽሐፍ በማሳተምም ይታወቃሉ፡፡ በአካባቢው ጉዳዮች ዙርያም እውቅ ጋዜጠኞችም ኾኑ የምዕራብ መንግሥታት እርሳቸውን የማማከር ዝንባሌ እንደነበራቸውም ይወሳል፡፡ ይበልጥ የሚታወቁትም The Politics of Empire: Ethiopia, Great Britain and The United States በሚለው መጽሐፋቸው ነው፡፡
ዶክተር ሀሮልድ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርስቲ (የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ)፣ በካርቱም ዩኒቨርስቲ፣ በኦሳካ ዩኒቨርስቲና በሀዋርድ ዩኒቨርስቲዎች ለተወሰኑ ጊዜያትም ቢኾን ታሪክን አስተምረዋል፡፡ ረዥም የመምህርነት ዘመናቸውን ያሳለፉት ግን በሚቺጋን ዩኒቨርስቲ ነው፡፡ በዚያ ለ35 ዓመታት የታሪክ ፕሮፌሰር ኾነው አገልግለዋል፡፡
አሁን ወደ አማርኛ የተመለሰው የአጼ ምኒሊክ የሕይወት ታሪክና እና የሥልጣን ዘመን የአማርኛ ቅጂ በ200 ብር ዋጋ እየተሸጠ ይገኛል፡፡ ኾኖም መጽሐፉ የትኛው የአገር ቤት ማተሚያ ቤት ዉስጥ እንደታተመ የሚገልጽ ጽሑፍ በሽፋኑ ላይ አልሰፈረበትም፡፡ ይህም የኾነው ምናልባት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ አታሚዎች ካልተጠበቀ ተጠያቂነት ራሳቸውን ለመጠበቅ ከሚያደርጉት ሙከራ ጋር የተያያዘ እንደኾነ ይገመታል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸውና አገራዊ አጀንዳን የሚተነትኑ መጽሐፍት በሚያሳትሙ፣ በሚያከፋፍሉና አዙረው በሚሸጡ ዜጎች ላይ ወከባው እየበረታ መምጣቱ ይታወሳል፡፡