Sheik Al Amoudi-PHOTO FILE
Sheik Al Amoudi-PHOTO FILE

“መሐመድ! አጋርነትህን በተግባር የምታሳይበት ወሳኝ ጊዜ ላይ ነህ”

ዋዜማ ራዲዮ-ባለፈው ሳምንት ወደ ሜድሮክ ሊቀመንበር ሼክ ሞሐመድ አላሙዲ የስልክ ጥሪ እንዳደረጉ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በአዲስ አበባ የሚገኙ ጅምር የሜድሮክ ግንባታዎች በጥቅሉ ፖለቲካችንን እያበላሹብን ነው ሲሉ ወቀሳ ማቅረባቸውን የአዲስ አበባ የካቢኔ አባላትና ከፍተኛ የድርጅት አመራሮችን በጽሕፈት ቤታቸው ሰብስበው ባነጋገሩበት ወቅት ገልጸዋል፡፡

የከተማ ነዋሪዎች በመንግሥት ላይ እምነት እንዲያጡ ከሚያደርጉ ነገሮች አንዱ ታጥረው ያለግንባታ ለዓመታት የተቀመጡ የከተማዋ ቦታዎች ናቸው ሲሉ ለሜድሮክ ሊቀመንበር እንዳብራሩላቸው፤ ይህም በኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ ሁሉ የተነሳ ጉዳይ እንደሆነ እንዳነሱላቸ

ው አውስተዋል፡፡ “እሱ እኛ ብለነው ሳይሆን ቀድሞም አገሩን የሚወድ ሰው ነው፤ እዉነት እንነጋገር ከተባለ እንደሱ መዋዕለ ነዋዩን ሳይሰስት በዚች አገር ኢንቨስት ያደረገ ሰው የለም” ካሉ በኋላ፤ “በሜድሮክ ፕሮጀክቶች እዛም እዚም መንተፋተፍ ሕዝብ አሉታዊ ትርጉም እየሰጠን ነው፤ ይህ መቀየር አለበት” ብለዋል፡፡ አጋርነትህን በተግባር የምታሳይበት ወሳኝ ጊዜ ላይ ነህ ብዬ ቃል በቃል በስልክ ነግሬዋለሁ፡፡” ሲሉም ለተሰብሳቢዎቹ ተናግረዋል፡፡

የሜድሮክ ሊቀመንበር በበኩላቸው የመዘግየቱ ጉዳይ የመጣው ይበልጥ አገራዊ ፋይዳ ባላቸው ፕሮጀክቶች ላይ በመጠመዳቸው እንደሆነና በአስተዳደሩ በኩልም ችግር እንደነበረ ጠቅሰው አሁን በአጭር ጊዜ ዉስጥ የሁሉም ግንባታዎች መጀመር በግላቸው በቅርቡ እንደሚያበስሩ ቃል ገብተዉልኛል ብለዋል፡፡ “ሂደቱንም መሐመድ ራሱ ወደ አገር ቤት ተመልሶ እንደሚከታተለው አረጋግጠልኛል፡፡” ብለዋል፡፡

ችግሩ የማን ነበር የሚለውን ትተን አሁን በቀጥታ ወደ ሥራ መግባት ይኖርብናል፤ ባለፈ ጉዳይ ጊዜ ማጥፋቱ ረብ የለሽ ነው፣ ይህ ጊዜ እናንተ የካቢኔ አባላት፣ ከግል የልማት አጋሮቻችን ጋር እጅና ጓንት በመሆን ዉጤት እንድታሳዩን የምንፈልግበት ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለተሰብሳቢዎቹ፡፡

የሜድሮክ ሊቀመንበር ሼክ ሙሐመድ አላሙዲ የሁሉም ግንባታ የሚጀመርበት ቀን በሸራተን በልዩ ዝግጅት በቀጥታ ለሕዝብ በቴሌቪዥን እንዲተላለፍ ከዉይይቱ በኋላ ረዳቶቻቸውን አዘው እንደነበር የታወቀ ሲሆን ይህ ሀሳብ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ተሰርዟል ወይም ወደፊት በተለየ መልክ ሊካሄድ ይችላል ሲሉ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ነግረውናል፡፡

ሰሞኑን በማዘጋጃ ቤት ከምክትል ከንቲባ አባተ ስጦታው ጋር የተወያዩት የሜድሮክ ባለቤት ወኪል፣ ሥራ አስፈጻሚና የሼክ ሙሐመድ የግል ወዳጅ አቶ አብነት ገብረመስቀል ሁሉም ፕሮጀክቶች የሚጀመሩት ቀን እንዲቆረጥና ይህም በሕዝብ መገናኛ ብዙኃን እንዲገለጽ የሊቀመንበራቸው ፍላጎት መሆኑን ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ በዚህም መሠረት ጥቅምት 19 የሜድሮክ የልማት ቀን ተብሎ እንዲሰየም ከመግባባት ደርሰዋል፡፡ የዲዛይን ለውጥ፣ የፍሳሽና ኤሌክትሪክ መስመሮች በጊዜው አለመነሳት፣ የሜድሮክ የዉስጥ ችግሮች አዘግይተውናል፣ ከዚህ በኋላ ዋስትና የሚሆነው ሥራውን ሠርቶ ማሳየት ብቻ ነው ሲሉ መናገራቸው ተሰምቷል፡፡

ይህንንም ተከትሎ የቀድሞው የዉሃና ኢነርጂ ሚኒስትር የነበሩት አቶ አለማየሁ ተገኑ ከጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ፣ አቶ አባተ ስጦታው ከመስተዳደሩ ጋር በመሆን የጉብኝት ፕሮግራም ያወጡ ሲሆን ጉብኝቱ የሚዲያ ሽፋን እንዲያገኝ፣ ከግንባታ ፍቃድ ጋር በተያያዘ ያልተፈታ ችግር ካለም አስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጠው መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ ለዚህም ይመስላል ለሁሉም ክፍለከተሞች የሜድሮክ ፕሮጀክቶችን በተመለከተ በሚል ርዕስ የተሰጠው ደብዳቤ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ለግንባታ ፍቃድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች የተላከው፡፡ ይህ ደብዳቤ እንደሚያብራራው የሜድሮክ ፕሮጀክቶች ላይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መስተዳደሩና የጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ በቅንጅት መፍትሄ መስጠት በማስፈለጉ በማንኛውም ሁኔታ የመከኑ የሜድሮክ ካርታዎች እንዲመለሱ፣ የግንባታ ፍቃድ ማራዘሚያ እንዲደረግላቸው፣ በቢሯችሁ በኩል የግንባታ መጓተትን የሚያስከትል ማንኛውም ጉዳይ በአስቸኳይ እንዲፈታ እንዲሁም የግንባታ አረጋጋጭ ባለሞያ በየጊዜው ወደ ሜድሮክ ሳይቶች እንዲላክና ይህም ሂደት በየጊዜው ለቢሯቸው ሪፖርት እንዲደረግላቸው አቶ አባተ የጻፉት ደብዳቤ ተብራርቷል፡፡

ሜድሮክ ወሎ ሰፈር የሚገኘው አፓርትመንት ምድር ቤቱን የዳሽን ባንክ ፕሪምየም ደምበኞች አገልግሎት መስጫ አድርጎ በቅርቡ የከፈተው ሲሆን በዚሁ ሕንጻ መግቢያ ላይ የሜድሮክ ፕሮጀክቶች መጀመርያ ቀን ጥቅምት 19፣ ሜድሮክ የልማት አጋር የሚል ተለቅ ያለ ፖስተር ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ተለጥፏል፡፡ ይህ አፓርትመንት ላለፉት 8 ዓመታት ግንባታው ሲጓተት የቆየና ከተጠናቀቀ በኋላም ቢሆን ለአገልግሎት ክፍት ሳይሆን የኖረ ነው፡፡ በተመሳሳይ በሳርቤት ገብሬል አካባቢ የሚገኘው ሎሊ ሕንጻ የዉጭ ገጽታ ንጣፍ እየተጠናቀቀለት ይገኛል፡፡

ሜድሮክ በአዲስ አበባ ብቻ 18 የሚሆኑ የታጠሩ እጅግ ሰፋፊ ይዞታዎች ያሉት ሲሆን ከጥቂቶቹ በስተቀር ሁሉንም ይዞታዎች ያለግንባታ ቸል ብሏቸው ለአመታት ኖሯል፡፡ ከነዚህ አንዱ ለሸራተን ማስፋፊያ የተወሰደ ከሸራተን ሆቴል ማዶ የሚገኝ ቦታ ነው፡፡ ከቤተመንግሥት ወደ ቴዎድሮስ አደባባይ በሚወስደው አዲስ አስፋልት መንገድ በኩል የሚገኘው የሸራተን ማስፋፊያ አጥር በመንገድ ምክንያት በመፍረሱ ከሰሞኑ የአጥር እድሳት እየተደረገለትና የጥበቃ ማማ እየተገነባለት ሲሆን ቦታው ለቁጥጥር አስቸጋሪ በመሆኑና ስፋቱ ከአምባሳደር ቴአትር ፍልዉሃ መስጊድ፣ ፊት በር፣ ፖሊስ ጋራዥና አካሎ እስከ ሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤት አጥር የሚደርስ በመሆኑ ከፍተኛ የወንጀል ድርጊቶች እንዲፈጸሙበት ምክንያት ሳይሆን አልቀረም፡፡

ባለፈው ዓመት አንዲት ቆሎ በማዞር የምትተዳደር ሴት ልጅ በዚህ ስፍራ መደፈሯን ፖሊስ ሪፖርት አድርጎ ነበር፡፡ ይህንንም ተከትሎ በአካባቢው ማኅበረሰብ አቀፍ አነስተኛ የፖሊስ ጣቢያ እንዲሰራ ሐሳብ ቀርቦ ተግባራዊ ሳይደረግ ቆይቷል፡፡ በአካባቢው ተደጋጋሚ ወንጀሎች የሚፈጸሙ ሲሆን በግቢው አደገኛ እጽ የሚያበቅሉ ወጣቶች ተይዘው መታሰራቸው በሚዲያ ተዘግቧል፡፡ በፊት በር በኩል ከእግረኛ ሴቶች ያዘሉትን ቦርሳ በመቀማት አምልጠው የሚጠፉ ወጣት ጥፋተኞች በተደጋጋሚ ዘለው ወደዚህ ሳይት ገብተው የሚሰወሩ ሲሆን ከቦታው አደገኛነት የተነሳ የአዲስ አበባ ፖሊስ ሌቦቹን ገብቶ፣ ተከታትሎና አድኖ ለመያዝ ብዙዉን ጊዜ ፍቃደኛ አይሆንም፡፡ ስፍራው ለወንጀል ድርጊቶች መጠለያ ሆኖ ለረዥም ጊዜ ማገልገሉንና መፍትሄ እንዲሰጠው ባሳለፈውነው አመት መጨረሻ አንድ የፓርላማ አባል በምክር ቤት ጉዳዩን ማንሳታቸው አይዘነጋም፡፡

ከኢንተርኮንቲነንታል ሆቴል ጎን የሚገኘው ሌላው የሜድሮክ ሳይት ክሬን ከቆመ አመታት ቢቆጠርም ጉድጓድ ተቆፍሮ በአካባቢው መለስተኛ ኩሬ ሰርቷል፡፡ ይህም በስተመሰሜን በኩል ማደርያ ክፍል የያዙ የኢንተርኮንቲነንታል ደንበኞች መስኮት ለመከፍተት እንዳይችሉ ሆነዋል፡፡

ሜድሮክ በዚህ አካባቢ የሚገኘውን ይዞታውን ካርታ ስላልታተመልኝ ነው ያልገነባሁት የሚል ምክንያት አቅርቦ የነበረ ሲሆን የቂርቆስ ክፍለከተማ የግንባታ ፍቃድ ባለሞያ ከዚህ ቀደም ካርታ አዘጋጅታችሁ ቤታቸውም ቢሆን ሄዳችሁ ስጧቸው የሚል መመሪያ ከጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ በስልክ ተደውሎ እንደተነገረው ያስታውሳል፡፡ ያመከናቸውን ካርታዎች ወዲያዉኑ በሙሉ መልሰን ሰጥተናቸዋል፡፡ ግንባታ ግን እስከዛሬም ጀምረው አያውቁም፡፡ እኛም ጠይቀናቸው አናውቅም፡፡”ይላል፡፡

ሌሎች ግለሰቦች በሊዝ የወሰዷቸውን ቦታዎች በገቡት ዉል መሠረት ካልገነቡ መስተዳደሩ ይዞታቸውን ወዲያዉኑ የሚነጥቃቸው ሲሆን ላለፉት 18 ዓመታት አንድም ግንባታ ሳያካሄድ የቆየው ሜድሮክ ግን አንዳችም የደረሰበት ቅጣት የለም፡፡ ከዚህ ቀደም በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲመክኑበት የተደረጉ ካርታዎችም በአስቸኳይ እንዲመለሱለት ተደርጓል፡፡

ይህ ዜጎችን ለያይቱ የማስተዳደር ጉዳይ በነዋሪዎች ዘንድ ዉስጥ ዉስጡን ሕዝብ በመንግሥት ላይ እምነት እንዲያጣ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ የሜድሮክ ጉዳዮችን ተከታትሎ ለሕዝብ በማሳወቅ ረገድ ሪፖርተር ጋዜጣ ተጠቃሽ ሲሆን ለድርጅቱ የሚደረገውን ያፈጠጠ ኢፍትሀዊ አሰራር ሲቃወም ቆይቷል፡፡ አንዳንዶች ይህ የሆነው ለአገር በመቆርቆር ሳይሆን የጋዜጣው ባለቤት በግል ከሜድሮክ ሰዎች ጥቃት ስለደረሰባቸው ይህንኑ ለመበቀል ያደረጉት ነው ይላሉ፡፡ ያም ሆኖ ችግሮቹን ለሕዝብ በማድረስ ረገድ ጋዜጣው የተጫወተው ሚና በቀላሉ የሚገመት አልሆነም፡፡

ሜድሮክ የእንግሊዝኛ ምህጻረ ቃል ሲሆን “ሞሐመድ ኢንተርናሽናል ዴቨሎፕመንት ሪሰርች ኤንድ ኦርጋናይዜሽን ካምፓኒ” የሚለውን ስም የሚወክል ነው፡፡ በስሩ 60 የሚሆኑ ካምፓኒዎችን ይዟል፡፡ ከነዚህ ዉስጥ ሀያ አራቱ የሚሆኑት ሜድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ በሚል ጥላ ስር የሚገኙ ሲሆን በበላይነት የሼክ ሙሐመድ አብሮ አደግ የሆኑት የወልዲያው ተወላጅ ዶክተር አረጋ ይርጋው ይመሯቸዋል፡፡ ዶክተር አረጋ የሜድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ሥራ አስፈጻሚ ከመሆናቸው ባሻገር የዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንትነትና የሜድሮክ ጎልድን ሥራ አስፈጻሚነትን ደርበው የያዙ ሰው ናቸው፡፡ ሆራይዘን፣ ሞሀ፣ ናሽናል ኦይል፣ ደርባ ሲሚንቶ፣ ሁዳ ሪልስቴት፣ ሜድሮክ ፋውንዴሽን ከሜድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ የሚጠቀሱት ናቸው፡፡ ከነዚህ ባሻገር የአፍሪካ ሕብረት ግራንድ ሆቴልን ገንብቶ እያጠናቀቀ የሚገኘው ሜድሮክ ኢትዮጵያ ፕሮጀክት ለፕሬዘዲንቶች ማረፊያ የሚሆነውን የላክዠሪ ሆቴል ገንብቶ በአሁን ሰዓት ማጠናቀቂያ ሥራን እያከናወነ ነው፡፡ ይህ ላክዠሪ ግራንድ ሆቴል በዚህ ዓመት መጨረሻ ይጠናቀቃል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ በቅርቡ ሁዳ ኮንስትራክሽን ቴክነኖሎጂ ግሩፕ የወልዲያ ስቴዲየምን በ400 ሚሊዮን ብር ግንብቶ ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡

ዶክተር አረጋ በቅርቡ ኢትዮጵያን ቢዝነስ ሪቪው ከሚባልና አገር ቤት ከሚታተም የእንግዝኛ መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ሼክ መሀመድ ስለቢዝነሶቻቸው ዕለታዊ እንቅስቃሴ በምን መልኩ ነው የሚከታተሉት ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ በስድስት ወር አንድ ጊዜ ሪፖርት ይቀርብላቸዋል የሚል አጭር መልስ ሰጥተው ነበር፡፡