Lidetu Ayalew Mansion at Debre Zeit
Lidetu Ayalew Mansion at Debre Zeit PHOTO-Wazema Radio

ሙሴ ሐዘን ጨርቆስ (ለዋዜማ ሬዲዮ)

አሉታዊ ትርጓሜውን ወዲያ ጥለን…አንድ ሰው “ላሊበላ ነው” ሲባል በፍካሪያዊ ትርጉም “ተናጋሪ ነው፣ አፈቀላጤ ነው”እንደማለት መሰለኝ፡፡ አቶ ልደቱ ይህን ቃል የሚወክሉ ሰብአዊ ሀውልት ናቸው ብልስ? በትውልድም በግብርም ማለቴ ነው፡፡ በቅርብ ጊዜ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ እንደ አቶ ልደቱ አንደበቱ የተፍታታ፣ ግንዛቤው የጠለቀ፣ አወዛጋቢ ተክለሰብ ማን አለ?

እርሳቸው ገና ላሊበላ 2ኛ ደረጃ ተማሪ ሳሉ ኢህአዴግ ሰፈራቸው ዉስጥ ከፍተኛ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ያደርግ ነበር፡፡ በኢህአዴጎች የተመሰጡት ገና ያኔ ነበር ብል ስም ማጥፋት እንዳይሆንብኝ፡፡ ኾኖም ለፖለቲካ ጆሮ መስጠት የጀመሩት ኢህአዴጎችን አይተው ስለመሆኑ ከአንድ ብዙ ሰው ከማያነበው መጽሔት ጋር በአንድ ወቀት ባደረጉት ቃለ መጠይቅ መናገራቸውን አስታውሳለሁ፡፡

ደግሞ ሰነፍ ተማሪ ነበሩ፡፡ ዘጠነኛ ክፍል ሲደርሱ ግን የሕይወት ማርሽ ቀየሩ፡፡ ጎበዝ ተማሪ ለመሆን፡፡ የሚገርመው እርሳቸው ጎበዝ ተማሪ ለመሆን ሲወስኑ በላሊበላ ዲግሪ የያዙ ሰዎች ቁጥር ከ5 አይበልጥም ነበር፡፡ አርአያ ፍለጋ ብዙ ተንከራተዋል፡፡

የአቶ ልደቱ የልጅነት ዋንኛ የሕይወት ግብ ግን ፖለቲካን መቆመር አልነበረም፡፡ ልጅ ሳሉ ሕልማቸው አንድና አንድ ነበር፡፡ ሙልጭልጭ የሚል፣ ለተከላካይ ራስ ምታት የሚሆን፣ አሁንም አሁንም ጎል የሚያስቆጥር አጥቂ መሆን፡፡ እንደ ማራዶና! እርግጥ ነው በእግር ኳስ ሜዳ ያሰቡትን ያህል ባያሳኩም በጠባቡ የፖለቲካ ሜዳ ግን ሙልጭልጭ እንዳሉ ነው ይሏቸዋል አብረዋቸው የፓርቲ ፖለቲካን ያቦኩ፡፡ ይሄ ነገር ስም ማጥፋት ይመስልብኝ ይሆን? ግን እኮ የተቃዋሚ ፓርቲው ራሱ መረሬ አፈር ማለት ነው፡፡ በአሉባልታ ሲቦካ የኖረ! እርሳቸውም ከዚያው አፈር ነው የወጡት፡፡

እስቲ ሾርኔያችንን ገታ አድርገን ስለ አቶ ልደቱ የልጅነት ሕልም በጥልቀት እናውራ፡፡ በልጅነታቸው የምር ጎበዝ ተጫዋች እንደነበሩ ማንም አብሯደግ የሚመሰክረው ነው፡፡ አሁን ራሱ ኳስ የማንቀርቀብ ክህሎታቸው አስገራሚ ነው፡፡ ፖለቲካውን እንደሚያንቀረቅቡት ኳሱን ያንቀረቅቡታል፡፡ ኳስ ድብልቡል ናት፡፡ እርሳቸውም በፖለቲካዊ ሰብእናቸው እንዲያ ሳይሆኑ አይቀሩም፡፡ የአቶ ልደቱን ፖለቲካው ቅርጽ መናገር ለማንም ፈታኝ የሚሆነውም ለዚሁ ነው፡፡ እኔ ለምሳሌ ይሄን ሦስተኛ መንገድ እስከዛሬ እየፈለኩት አለሁ፡፡ 3ኛ ፖሊስ ጣቢያ እንጂ 3ኛ የሚባል መንገድ አላገኘሁም፡፡

አቶ ልደቱ ገና በ14 ዓመታቸው አውራጃቸውን ወክለው 10 ቁጥር ማሊያ ለብሰው አጥቅተዋል፡፡ ጎል ማስቆጠራቸውን የሚያስተውስ ግን የለም፡፡ እርሳቸውም ትዝ አይላቸውም፡፡ ትዝ የሚላቸው አራጋቢው ደጋግሞ ኦፍሳይድ ነዎት ሲላቸው ነው፡፡ አንድ የዋንጫ ጫወታ ላይ አራጋቢው አውለበለበ፡፡ አልተበሳጩም፡፡ እንዲያውም በክርክር ኦፍሳይድ አለመሆናቸውን ለማሳመን ወደ አራጋቢው ሄዱ፡፡ እርሳቸው ከአራጋቢው ጋር እየተከራከሩ የተቃራኒ ቡድን ጎል አስቆጠረ፡፡ ተበሳጭተው ኳስ አቆሙ፡፡ ለነገሩ አሁንም ድረስ ሰውየው ከጨወታ ዉጭ መሆንን ያበዛሉ!! ወደ ጨዋታ የሚመለሱት ወሳኝ ጊዜያቶች ላይ ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ ኢህአዴግ ከሰሞኑ ነፍስ ዉጭ ነፍስ ግቢ ላይ ሲሆን ሸራተን ድረስ ሄደው የጥናት ወረቀት ይዘው ጠይቀውታል፡፡ አሁን ፓርቲው ከጽኑ ማገገሚያ ማዕከል (ICU) እየወጣ ይመስላል፡፡

Lidetu Ayalew-Photo credit Addis Fortune
Lidetu Ayalew-Photo credit Addis Fortune

የምር ግን አቶ ልደቱ የት ጠፍተው ሰነበቱ?

ይልቅ ስለ ወላጅ አባታቸው እናውራ፡፡ የአቶ ልደቱ አባት የሚመስጡ ሰው ናቸው፡፡ አልተማሩም፡፡ ግን ትንታግ ተናጋሪ፣ በገጠር የማኅበራዊ ጉዳዮች ተንታኝ፣ አወዛጋቢ የአካባቢ ሽማግሌና ፈጣሪ-ነጋዴ ናቸው፡፡ በዚህ ዘመን ቢኖሩ ዶናልድ ትራምፕን ሊሆኑ ይችሉ ነበር ብዬ አስባለሁ፡፡ ለምን ማለት ጥሩ ነው፡፡

በላሊበላ ማን የመጀመርያውን ወፍጮ ቤት ከፈተ? አቶ አያሌው ምሕረቱ፡፡ በላሊበላ ማን የመጀመርያውን ዘመናዊ ቡቲክ ከፈተ? አቶ አያሌው ምህረቱ፡፡ በላሊበላ ማን የመጀመርያውን ቤት ገንብቶ መሸጥ ወይም ማን የገጠር ሪልስቴት ቢዝነስ ጀመረ? አቶ አያሌው ምሕረቱ፡፡ አቶ ልደቱ “በኔ ሕይወት ትልቅ አሻራ ጥሎ ያለፈው ሰው ወላጅ አባቴ አቶ አያሌው ነው” የሚሉት እውነታቸውን ሳይሆን አይቀርም፡፡

ለማንኛዉም አቶ ልደቱ እግር ኳስ ተጫዋች እንደማይሆኑ ሲረዱ ደራሲ ለመሆን ወስነው ነበር፤ድሮ፡፡ የፖለቲካ ዉክቢያ ዉስጥ ሲገቡ ግን ለልቦለድ ጊዜ አጡ፡፡ ለነገሩ በወከባ ዉስጥ ሆነውም ሦስት መጽሐፍ ማበርከታቸው ለደራሲነት እምቅ አቅም እንደነበራቸው የሚጠቁም ነው እላለሁ፡፡ የአረም እርሻ፣ መድሎትና ሦስተኛው መንገድ፡፡

አቶ ልደቱን ብዙዎች በአንደበተ ርቱእነታቸው ያውቋቸዋል፡፡ ጋዜጠኞች ደግሞ በጎበዝ ጸሐፊነታቸው ይረዷቸዋል፡፡ ለምሳሌ በአንድ ጉዳይ የጋዜጣ ጽሑፍ እንዲያቀርቡ ከተጠየቁ ብዙዎቹ የአገራችን ፖለቲከኞች ማቃሰት ይጀምራሉ፡፡ ያምጣሉ፡፡ ይታመማሉ፡፡ ጉንፋን ይይዛቸዋል፤ ስልክ ያጠፋሉ፡፡ ዛሬ ነገ እያሉ ጋዜጠኛን ያመላልሳሉ፡፡ በመጨረሻም “ለመጻፍ ጊዜ የለንም፤ በድምጽ ቅዱንና ወደ ጽሑፍ ቀይሩልን” ይላሉ፡፡ አቶ ልደቱስ?

አቶ ልደቱማ ጻፍ የሚላቸውን ሰው መጀመርያ አንቀው ይስሙታል፡፡ ከዚያ 3 ገጽ በጽሑፍ አቅርብ ከተባሉ 7 ገጽ ጽፈው በነገታው ከች ነው፡፡ ደግሞ ሲችሉበት፡፡ ሐሳባቸውን በጥሩ ቋንቋ ከሽነው ማቅረቡ የትኛውም ፖለቲከኛ የሌለው የግል ተሰጧቸው ነው፡፡ በቅርብ ጊዜ እንኳን ሪፖርተር ላይ ስለ መልካም አስተዳደር ፍልስፍናና የኃይለማርያም ይህን ፍልስፍና አለመረዳት የጻፉት ትችት ሲያምር፡፡ እኔ 3 ጊዜ ደጋግሜ አንብቤዋለሁ፡፡ አዲስ ዕይታ ነው፡፡ እንዲህ አይነት መረዳት ያለው ፖለቲከኛ እንዳለመታደል ሆኖ ብዙ የለንም፡፡ አቶ ልደቱ እድሜ ይስጥህ አቦ!

ልደቱ ከሥነጽሑፍ ጋር የተዋወቁት ድሮ ነው፡፡ “እርስዎም ይሞክሩት” የሚባል ፕሮግራም ላይ “ልደቱ ነኝ ከልደታ” እያሉ ተሳትፎ ያደርጉ ነበር፡፡ ያኔ እጅግ አይናፋር ስለነበሩ ሐሳባቸውን መግለጽ የሚቀናቸውም በጽሑፍ ብቻ ነበር፡፡ አሁን ይሄን ማን ያምናል? አቶ ልደቱ አይናፋር መሆናቸውን፡፡

ከለታት ባንዱ ቀን ፕሮፌሰር አስራት “ልደቱ ነኝ ከልደታ” እያሉ በጋዜጣው በሬዲዮኑ የሚሳተፉትን ሰው አምጡልኝ አሉ፡፡ አመጡላቸው፡፡ የላሊበላ ሰው ነው፡፡ ገረማቸው፡፡ “በል ወደ መአሐድ የወጣት ክንፍ ገብተህ አገልግል” አሏቸው፡፡ አቶ ልደቱ ደንግጠው ጠፉ፡፡ በስንትና ስንት ጉትጎታ የወጣት ክንፉ አስተባባሪ ሆኑ፡፡ በ1988 አድዋ 100ኛ ዓመት ሲከበር ፓርቲውን ወክሎ አንድ ሰው ንግግር እንዲያደርግ ተፈለገ፡፡ ማን ደፍሮ ይናገር? አቶ ልደቱ በድፍረት ገቡበት፡፡ ማይክራፎን ከያዙ ራሳቸውን ይስታሉ፡፡ አንበለበሉት፡፡ ድሮስ የላሊበላ ሰው አይደሉ! ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አቶ ልደቱ ለሚዲያ እጅግ ተመራጩ ሰው ኾኑ፡፡

የምር ግን አቶ ልደቱ የት ጠፍተው ነበር?

አቶ ልደቱ በሕይወታቸው ሁለት ትልልቅ ብስጭቶችን ተበሳጭተዋል፡፡ የመጀመርያው ማትሪክ ሳይመጣላቸው ሲቀር፡፡ ሁለተኛው የቅንጅት ምስረታ ላይ በፈጠሩት እክል ምክንያት ሕዝብ ሳይረዳቸው ሲቀር፡፡ እርሳቸው ግን ላመኑበት ሟች ናቸው፡፡ አሁንም እንዲያ ናቸው፡፡ ይህ ባሕሪያቸው “3ኛው መንገድ” የሚል የፖለቲካ ፍልስፍና ወለደ፡፡ ችግሩ ይህ መንገድ ብዙ ሕዝብ የሚተምበት መንገድ አይደለም፡፡ ለዚህም ነው “3ኛው መንገድ” የተባለው፡፡ ለዚህም ነው ይህ ጽሑፍ እርሳቸው ላይ የሚዘምተው፡፡

ይልቅ ሰውየው የት ጠፍተው ነበር?

ያኔ ማትሪክ ሳይመጣላቸው ሲቀር በአይሱዙ ተንጠላጥለው ደሴ ገቡ፡፡ መንጃ ፍቃድ አውጥተው ታክሲ ገዙ፡፡ ይሄን ሕዝብ ያሳፍሩት ጀመር፡፡ አንዳንድ ጊዜ መንገድ እየሳቱ…መንገድ እያሳቱ…ሌላ ሰፈር ዉስጥ ይገቡና….ሃሃሃ…(3ኛው መንገድ ይሆን?)

ተሳፋሪ ጋር መጨቃጨቅ ሰለቻቸው፡፡ መልስ ሰጥቼሃለሁ…አልሰጠከኝም…ወራጅ አለ የለም…ትርፍ ጫን አትጫን…ጋቢና ግባ አትግባ….ጭቅጭቅ…

ታክሲ ሥራን እርግፍ አድርገው ተዉት፡፡ ንግድ ፍቃድ አውጥተው ከደሴ አዲሳባ፡፡ ከአዲሳባ ዱባይ…ከዱባይ መኪና አስመጥቶ መሸጥን ተካኑበት፡፡ ልደቱ አስመጪና ላኪ ተባሉ፡፡ ቤት ገዙ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን እድሜያቸው 25 እንኳን አልደፈነም እኮ፡፡ የአሁን ጊዜ ወጣት ቢሆን ይህን ብር ዙርባ ጫት ይቅምበት ነበር፡፡ ልደቱ ግን ራሳቸው የነደፉትን ቤት ገነቡበት፡፡ ከአፓርታማ ኑሮ ተላቀቁበት፡፡

ገንዘብ ሰገደላቸው፡፡ ገንዘብ ሲያገኙ እርካታ እየራቃቸው ሄደ፡፡ በገንዘባቸው ሌላውን መርዳት ፈለጉ፡፡ አንድ ሰው ከምረዳ ብዙ ሰው ላይ ተጽእኖ የሚፈጥር ነገርን ብረዳ የተሻለ ነው ብለው ስላሰቡ መአሐድ የሚባል የፖለቲካ ድርጅትን በገንዘብ መርዳት ጀመሩ፡፡ ያን ጊዜ ሕይወታቸው አዲስ መንገድ ያዘ፡፡

የምር ግን አቶ ልደቱ የት ጠፍተው ሰነበቱ?

የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በታሪክ ዘርፍ በማታ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በዓለማቀፍ ግንኙነት ይዘዋል፡፡ ዐለማቀፍ ግንኙነት ሲማሩ ክፍል ዉስጥ ዝምታቸው ተማሪውን ረበሸ፡፡ ትምህርት ለረዥም ጊዜ ስለተራቡ ነው መሰል አድፍጠው በብዙ ጥሞና መማርን፣ ጥርሳቸውን ነክሰው “አሳይመንት” መሥራትን ያዘወትሩ ነበር፡፡ የፓርላማ ተመራጭ ቢኾኑም አንድም ቀን ክላስ ቀጥተው አያውቁም፡፡ ክፍል ዉስጥ አስገዳጅ የጥናት ወረቀት ለማቅረብ ካልሆነ ድምጻቸውን ሰማሁ የሚል ተማሪም አስተማሪም ጠፋ፡፡ ልደቱ ግን እንዴት ዝም ሊሉ ቻሉ?

አንዱ መላምት ከሌላው ተማሪ በተለየ የእርሳቸው የመጀመርያ ዲግሪ በታሪክ ዘርፍ ስለነበረ በማያውቁት ነገር ላለመዘባረቅ ሲሉ ነው ጥሞናን የመረጡት የሚል ሲሆን፣ ሌላው መላምት ደግሞ በአሉባልታ የሚነዳው የያኔው ፖለቲካ አኮስምኗቸው ነው የሚል ነው፡፡ ታዲያ አንድ ኮርስ የሰጧቸው ዶክተር መረራ ነበሩ አሉ፡፡ አንድ ቀን ልደቱ “ጥያቄ አለኝ” እያሉ ዶክተሩን እጅ አበዙባቸው አሉ…ይሄኔ ዶክተር መረራ መረራቸው አሉ፡፡

“ማነህ ልደቱ! እንግዲህ ይሄ ፓርላማ አደለም… በእጅ ብልጫ የሚወሰን ነገርም የለም፡፡ እዚህ ሳይንስ ነው የምናወራ…እጅ ብትቀንስ ለማለት ነው..ታንኪው.” ክፍሉ በሳቅ! አቶ ልደቱ አብረው በሳቅ! (ይቺ የታሪክ ቅንጣት “ፍተላ” በሚል ትያዝልኝ)

በነገራችሁ ላይ መረራ አውቆትም ይሁን ሳያውቀው ለኢህአዴግ ባለሥልጣናት መጠናከር የራሱን አስተዋጽኦ ሳያደርግ አልቀረም፡፡ ከልደቱ በፊት ወርቅነህ ገበየሁን የዐለም አቀፍ ግንኙነት ሀሁን አስቆጥሮታል፡፡ መረራና ዩኒሳ ተባብረው ነው ወርቅነህን ለዶክተርነት ማዕረግ ያበቁት፡፡

እና የነወርቅነህ ባቾች ሲያወሩ እንደሰማሁት በዶክተር መረራ ክላስ ብዙ ቀልዶችን ይፈበርኩ ነበር አሉ፡፡ አንዱ የሚከተለው ይመስላል፡፡

መረራ ለወርቅነህ ገበየሁ C ግሬድ ሰጠውና ወርቅነህ ተናዶ ዲፓርትመንት ሄዶ ከሰሰ አሉ፡፡ መረራ መልስ ስጥ ተባለ፡፡

“Mr. Workineh…As far as I know…Letter C የቱንም ያህል በፌዴራል ፖሊስ ብትገረፍ Letter A የምትሆን አይመስለኝም!!

ወርቅነህ ለመጀመርያ ጊዜ ተርገፍግፎ ሲስቅ የታየው ያን ቀን ነው ይባላል፡፡

***

የሆነስ ሆነና አቶ ልደቱ የት ጠፍተው ከረሙ?

የመረራን ኮርስ ጨርሰው መመረቂያ ጽሑፋቸውን “የምዕራባዊያን ሚና በ2005 ምርጫ” በሚል ርዕስ ከጻፉ በኋላ አቶ ልደቱ ወደ እንግሊዝ በረሩ፡፡ ብሪቲሽ ካውንስል ነው እድሉን የሰጣቸው፡፡ “ስኩል ኦፍ ኦሪየንታል ስተዲስ” የሚባል ትምህርት ቤት ሙሉ ወጪያቸውን ችሎ “ዴቨሎፕመንታል ስተዲስ” የሚባል ትምህርት አስተማራቸው፡፡ ሌላ ማስተርስ!

የሚገርመው ታዲያ ትምህርት ቤቱን እንግሊዞች “ልማታዊ ዩኒቨርስቲ” እያሉ የሚስቁበት አይነት መሆኑ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ግራ ዘመምነት ስለሚያጠቃው ነው ይባላል፡፡ እንደ ኢህአዴግ ኒዮ ሊበራሎችን የማይወድ፣ ኒዮ ሊበራሊዝምን የሚያወግዝ ትምህርት ቤት ነው የገቡት፡፡ ይሄ ትምህርት ቤት አቶ ልደቱን ወደ ኢህአዴግ አስተሳሰብ አስጠግቷቸው ይሆን? ስል እሰጋለሁ፡፡ “መጀመርያዉኑስ ከኢህአዴግ መቼ ርቀው ያውቁና ነው” እንደምትሉኝ እገምታለሁ፡፡ እኔ ግን አንድም ጊዜ የሰውየውን ነጻ አስተሳሰብ ጥያቄ ዉስጥ ከትቼ አላውቅም፡፡ ምንም እንኳ የአሉባልታው ፖለቲካ ደጋግሞ ጠልፎ ሊጥለኝ ቢሞክርም ማለቴ ነው፡፡

የምር ግን ሰውየው የት ጠፍተው ከረሙ?

አንዳንድ ጊዜ አቶ ልደቱን ሳስብ በግማሽ ሐዘኔታ ሆኜ “ምናለ ከአንድ ትውልድ በኋላ ተወልደው ቢሆን?” እላለሁ፡፡ በነ አየለ ጫሚሶ ዘመን ተወልደው ነው የፖለቲካ ቅርቃር ዉስጥ የገቡት፡፡ ደግሞም የሚቀጥለው ትውልድ ሐሳብን የሚመዝን፣ አሉባልታን አንጥሮ አጥልሎ የሚያላምጥ ይመስለኛል፡፡ ያለጊዜያቸው መጥተው ይሆን? የምለውም ለዚሁ ነው፡፡

አቶ ልደቱ አሁንም በገዢው ፓርቲ ላይ የሰላ ሂስ የሚሰነዝሩ፣ ንግግራቸው ጠብ የማይል “የማኪያቶ ታጋይ” ናቸው፡፡ የትዊተር ታጋይ ከመሆን የማኪያቶ ታጋይ መሆን በስንት ጣዕሙ፡፡ ከአትላንቲክ ማዶ የሚታገሉትን አምርረው ነው የሚወግዙት፡፡

“እጅግ የሚያስደስተኝ ነገር ቢኖር ከጓደኞቼ ጋር ማኪያቶ እየጠጡ ማውጋት ነው” ብለዋል ለድሬቲዩብ መጽሔት በሰጡት የቅርብ ጊዜ ቃለ ምልልስ፡፡ ከዉትፍትፉ የአገር ቤት ፖለቲካ መታረቅ፣ አሉባልታን ከሚያምነው ሕዝብ መግባባት አልሆንላቸው ሲል ነው መሰል አሁን አሁን አምጠው የወለዱትን ኢዴፓን እንኳ ቸል እያሉት ነው፡፡ ለወጉ የማዕከላዊ ምክር ቤት አባል ቢሆኑም ብቅ የሚሉት አልፎ አልፎ “20 ፊት ኮንቴይነራቸው” የጉምሩክ ክሊራን ሲጨርስ ብቻ ነው፡፡ የተሳካላቸው ነጋዴ ሆነዋል፤ በጥረታቸው፡፡

“በኔ እምነት አንድ ሰው በፖለቲካ ለውጥ ለማምጣት በኢኮኖሚ ረገድ ራሱን መቻል አለበት” የሚሉት አቶ ልደቱ በአመዛኙ የራሳቸው ንድፍ ነው የሚባል ከእንጨት የተፈለፈለ ዉብ መኖርያ ቢሾፍቱ ላይ ገንብተው ወደ ሐይቅ እያዩ ዘርጋ ያለ ኑሮን ይኖራሉ፡፡ ከዚያ ሆነው ብዙ ያነባሉ፣ እጅግ በጣም ብዙ ነው የሚያነቡት፡፡ ጊዜ ሲተርፋቸው ደግሞ ፕሪምየር ሊግ ያያሉ፤ ከባድ የቼልሲ ደጋፊ ናቸው፡፡ 48 ዓመታቸው ቢሆንም አላገቡም፡፡ ስድስት ኪሎ ተማሪ የነበረች አንዲት ቆንጆ ወደው ነበር፤ ሰርግ ቢጤም አቅደውነበር፤ ሳይሳካ ቀረ፡፡ ልጅቱ አሁን ከአትላንቲክ ማዶ ናት፡፡

አቶ ልደቱ ለስሜት እንጂ ለሐሳብ ሙግት እምብዛምም የሆነውን ሕዝባቸውን ሳያሳምኑ ትዳርን የሚሞክሩት አይመስሉም፡፡ “3 መጻሕፍትን” ያበረከቱት አቶ ልደቱ ለጊዜው “3ኛውን መንገድ” እንጂ “3 ጉልቻን” ማሰብ የጀመሩ አይመስሉም ፡፡

ሙሴ ሐዘን ጨርቆስ (ለዋዜማ ሬዲዮ)