አዲስ አበባ ፖሊሶቿን አስታጥቃለች፡፡
ወደ ክልል የሚሄዱ መኪኖች የወታደር አጀብ አይለያቸውም፡፡
ጥቅምት 1 (October 11)
ዋዜማ ራዲዮ-በባሕርዳር ለአምስት ቀናት የሚቆይ የሥራ ማቆም አድማ ዛሬ ጀምራለች፡፡ አድማው የንግድን ሱቆችን ከሥራ ዉጭ አድርጓቸዋል፡፡ እያስተማሩ ያሉ በርካታ ትምህርት ቤቶች ቢኖሩም አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ግን ተማሪዎችን ለመቀበል አልፈቀዱም ተብሏል፡፡ የባጃጅና ታክሲ አገልግሎት በከፊል ብቻ የተስተጓጎለ ሲሆን በርከት ያሉ ታክሲዎች ነዋሪዎችን እያመላለሱ እንደሚገኙ ተገልጧል፡፡ ከቀድሞው ጊዜ አንጻር በርካታ ባጃጆችም በዚህኛው አድማ ተሳትፎ አላደረጉም፡፡
ኅብረተሰቡ ዛሬ አድማ እንደተጠራ እንዴት እንደሚያውቅ ከዋዜማ የተጠየቁ የከተማዋ ነዋሪ ሌሊት ላይ ወረቀቶች ይበተናሉ፡፡ አንዱ ለአንዱ እየነገረ ወሬው በአጭር ሰዓት ይዛመታል ሲሉ የተደራጀ አሰራር እንዳለ ጠቁመዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እያለ ከትናንት ጀምሮ አዲስ አበባ በበርካታ ወታደሮች እየተጠበቀች ነው፡፡ ትናንት የሁለቱ ምክር ቤቶች መከፈት ተከትሎ አራት ኪሎ ፓርላማ አካባቢ እንዲሁም ግቢ ገብርኤልና ሸራተን ዙርያ ወታደር በብዙ ቁጥር ፈሶ ታይቷል፡፡ ከከሰዓት አራት ኪሎና አካባቢዋ ከትራፊክ ፍሰት ዉጭ እንዲሆኑ የተደረገ ሲሆን ቀትር ላይ መኪኖች ወደ መደበኛው ፍሰት ተመልሰዋል፡፡ በቤተመንግስት ዋናው በር ሁለት ብረት ለበስ ተሸከርካሪዎች፣ በቤተመንግሥታ ጋራዥ አካባቢ አድማ በታኝ ተሽከርካሪ፣ እንዲሁም ዎኪቶኪ የያዙ እግረኛ ፌዴራል ፖሊሶች በርክተው ታይተዋል፡፡
የወታደሮች ቁጥር ዛሬ ቀነስ ብሎ የታየ ቢሆንም በየአደባባዮች መሳርያ የታጠቁ ፖሊሶች ከወትሮው በርክተው ታይተዋል፡፡ ካዛንቺስ አካባቢ የትራፊክ መጨናነቅ ለተወሰኑ ሰዓታት ተከስቶም ነበር፡፡ ምናልባትም የዛሬው የጸጥታ ኃይሎች መብዛት ከጀርመኗ መርሐይተ መንግሥት አንጌላ መርኬል አዲስ አበባ መግባት ጋር ተያይዞ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል፡፡
የኢሬቻው አደጋ ተከትሎ በአዲስ አበባ መግቢያ በሮች የተነሳው አመጽን ተከትሎ በዋና ከተማዋም ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር ከፍ ያለ ስጋት በመንግሥት በኩል ተፈጥሮ ነበር፡፡ ለዚህም ይመስላል ሞተረኛ የትራፊክ ፖሊሶችና ወትሮ የጎማ ዱላ ብቻ እንዲይዙ ይደረጉ የነበሩ የአዲስ አበባ ፖሊሶች ብዙዎቹ መሳርያ እንዲታጠቁ የተደረገው፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዛሬ ማለዳ ላይ ለሬዲዮ ፋና እንደተናገሩት አመጹ ወደ አዲስ አበባ ለማስገባት የሞከሩ ሰዎች እንደነበሩ አምነው እስካሁን ግን የጎላ የፀጥታ ችግር በከተማዋ እንዳላጋጠመ አውስተዋል፡፡ አውቶቡስ ተራ አካባቢ አንድ ግለሰብ የኦነግን ባንዲራ ይዞ ሲያውለበልብ መታየቱንና በቁጥጥር ስር መዋሉን ጠቅሰዋል፡፡
በሌላ በኩል ከአዲስ አበባ ወደ ክፍለ አገር የሚደረጉ ጉዞዎች በስጋት የተሞሉ እንደሆኑ ተሰምቷል፡፡
ከሆሳእና ዛሬ ጠዋት እንደገባ የተናገረ የዩኒቨርስቲ መምህር በየመንገዱ ከአንድ ትራፊክ ጋር አምስት ወታደሮች ቆመው እንደተመለከተ፣ በመንገደኛ አውቶብሶች ዉስጥ የታጠቀ አንድ ወታደር ከሹፌሩ ጎን እንዲሳፈሩ እንደሚደረግ ተናግሯል፡፡ አዲስ አበባ እስኪደርስ ድረስ አምስት የሚሆኑ ተሸከርካሪዎች በየመንገዱ ተቃጥለው መመልከት እንደቻለም ገልጧል፡፡
ከቦንጋ ወደ አዲስ አበባ ቅዳሜ ዕለት እንደተመለሰ የተናገረ ሌላ የኢንሹራንስ ሠራተኛ በበኩሉ ለዋዜማ እንደተናገረው ከወልቂጤ መልስ ጉዞው ሁሉ በሰቀቀን የተሞላ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ወልቂጤ ከሆቴላችን ስንወጣ ፖሊሶች ከኛ ጋር የነበሩ 20 መኪኖችን ሰብስበው ካሰለፉን በኋላ ከፊት ለፊት አንድ ሙሉ ፒከአፕ መኪና ወታደር እንዲሁም ከኋላ ሌላ የወታደር መኪና አጅቦን ነው የተጓዝነው ሲል ስለሁኔታው አብራርቷል፡፡ ከወሊሶ፣ ዲላላ፣ ቆራ፣ እና ቱሎቦሎ በድንጋይ የተዘጋ ኬላዎችን አልፈናል፣ አስጎሪ ከምትባል ከተማ ቀጥሎ የምትገኝና አዋሽ ቡሌ ከመድረሳችን በፊት ባለች ተጂ በምትባል አነስተኛ ከተማ ላይ ደግሞ ዋናው መንገድ በቆርቆሮ አጥር ታጥሮ ማየቴ አስገርሞኛል ይላል ይኸው የኢንሹራንስ ባለሞያ፡፡
ከአውቶቡስ ተራ በሚነሱና ወደ ኦሮሚያ ክልል የሚደረጉ ጉዞዎች ላይ ስጋት በመኖሩ ኦሮየሚል ታርጋ የለጠፉ የዶልፊን ትራንስፖርት መሽጫ ተሸከርካሪዎች ወደ ስምሪት ለመግባት አልፈቀዱም፡፡ በዚህም የትራንስፖርት እጥረት መኖሩ አረጋግጠናል፡፡ ሁኔታዎች ግን እየተሻሻሉ ነው ተብሏል፡፡
በጅማና በአዳማ ዩኒቨርስቲዎች መጠነኛ ሁከት እንደነበር ተሰምቷል፡፡ ትናንት ከአዳማ ዩኒቨርስቲ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በጸጥታ ችግር የተመለሰች ወጣት ለዋዜማ እንደተናገረችው ማለዳ ወደ መማሪያ ክፍል በሚሄዱ መምህራንና ተማሪዎች ላይ በድንጋይ ጥቃት ለማድረስ የሞከሩ ተማሪዎች ዩኒቨርስቲውን አውከውታል፡፡ ነገሮች መልክ እስኪይዙ በሚል ጥቂት የማይባሉ ተማሪዎች ግቢውን ለቀን ወጥተናል ብላለች፡፡