(ለዋዜማ ራዲዮ)

ጤና ይስጥልኝ ጌታዬ!

ገረመው እባላለሁ፡፡ እሳት የላስኩ የፊንፊኔ ደላላ ነኝ፡፡ ምስጉን ጉዳይ ገዳይ ስለመሆኔ እግዜርም ሰይጣንም ያውቃሉ፡፡ ኪራይ ሰብሳቢ መሆኔን ድሪባም ኩማም ያውቃሉ፡፡ ዉሎ-አዳሬ ብሔራዊ፣ አመሻሼ አብዮታዊ ሃሃ፣ ላየን ባር ቤቴ፣ ቴሌ ባር ግዛቴ፡፡

እውነት ነው! ጥሎብኝ አልረጋም፡፡ ካዛንቺስ ነው ሲሉኝ ሳሪስ፣ ቀበና ነው ሲሉኝ ባምቢስ ደላላ ምን ቀልብ አለው ብለው ነው፤ጌታው!

እንዴት ነዎት ግን እርስዎ?

አይጠይቁኝ፡፡ ይኸው ይህን ሳምንት እንድቺው፡፡ ለምወዳት ዱለት እንኳ ጊዜ ልጣ!

ምንላርግ ብለው ነው….ከጥቃቅን ሚኒስትር እስከ ከፍተኛ ነጋዴ “ንብረቴን ሽጥልኝ” ብሎ ሰንጎ ይዞኝ…፡፡ ላይ ብወጣ ገረመው ነው፣ ታች ብወርድ ገረመው ነው፡፡ መካኒሳ “ሽጥልኝ ነው” ሰሚት ብወርድ “ሽጥልኝ” ነው፡፡ አጋዛኝ የሚል እኮ ጠፋ፡፡ ሻጭና ገዢ እንዲህ ያልተመጣጠነበት ዘመን በድለላ ዘመኔ ገጥሞኝም አያውቅ፡፡

እንደገባኝ ከሆነ በፊንፊኔ ሰማይ ፍርሃት የነገሰ ይመስላል፡፡ ሞጃው ሁሉ ነቅሎ አገር ለመልቀቅ ዳርዳርታ ላይ ያለ ይመስላል፡፡ ፊንፊኔ የወጨጫ ተራራ የከበዳት ይመስላል፡፡ ወትሮ ንብረት ለመግዛት ዐይናቸውን የማያሹት ኦህዴዶች እንኳ ዛሬ ተገልብጠው ቁጭ፡፡ ስልካቸውን ማንሳት ሁሉ ፈራሁኝ እኮ፡፡ ሱሉልታ ብወጣ “ሽጥልን ነው…” ሰበታ ብወርድ “ሽጥልን ነው” ፡፡ አሃ…ምንድነው ይሄን ያህል መንቦቅቦቅ! አገር እንደሁ ባንድ ቀን አትፈርስ!

በሚሽቱና በቅምጡ ስም ዐይኑን ጨፍኖ ያለ የሌለ ንብረት ሲገዛኝ፣ ቪላ ከአፓርታማ ሲያግበሰብስ የከረመ ኦህዴድ ሁላ የጭንቅ ቀን ሲመጣ እኔ ገረመው መረገም አለበኝ እንዴ፣ ሰዎቹ ከኔ ራስ አልወርድ ያሉትስ ስለምንድነው? ንብረት አጋዛሁት ማለት በሥልጣን አብሬው ወሰለትኩ ማለት ነው እንዴ? መዘንጋት የሌለበት ነገርኮ…እኔ ደለላ ነኝ፡፡ አራት ነጥብ፡፡ ሥራዬ ገዥና ሻጭን ማዳራት ነው፡፡ አራት ነጥብ፡፡ የገዢና የሻጭ የገንዘብ አመጣጥ ጤንነትን መመርመር ያለበት ፓስተር እንጂ ገረመው አይደለም፡፡ ምን ይላል ይሄ!

ኦቦ አባዱላ ለምሳሌ ወዳጄ ነበር፡፡ አሁንም ነው፡፡ እጅግ አድርጌ የማከብረው ሰው ነው፡፡ እንደርሱ ቸርና ለጋስ ሰው ከአርሲ ምድር እንዳልተፈጠረ እኔ ብቻ ሳልሆን ጠላቶቹም የሚመሰክሩት ነው፡፡ ለምሳሌ የሰበታው ጌታ ኦቦ ሽመልስ ሀሰኖ ከእስር ከተፈታ በኋላ አንድ ሁለት ጊዜ አግኝቼው ነበር፡፡ ታዲያ መለኪያ ይዘን ስንጨዋወት “ስማ ገረመው!….ኦሮሚያ ሰፊ መሆኗን ያወቅኩት በጂኦግራፊ ትምህርት ሳይሆን ባባዱላ ነው፡፡” አለኝ፡፡ እንዴት አልኩት፡፡ “ምን እንዴት አለው…የኦሮሚያ መሬት ታድሎ ቢያልቅ ኖሮ ባባዱላ ዘመን ያልቅ ነበራ፡፡” ብሎ አሳቀኝ፡፡ ዉነቱን ሳይሆን አይቀርም፡፡ ባባዱላ ትዛዝና በሽሜ አስፈጻሚነት የተቸበቸበው የሰበታና የፉሪ መሬት እንኳ ገና መቼ ተጋመሰና፡፡

እና ምን ለማለት ፈልጌ ነው…መጀመርያዉኑ የኦቦ አባዱላን ቸርነት ማንም ጥያቄ ዉስጥ የሚከተው ጉዳይ አይደለም፡፡ ለምሳሌ እርሳቸው ቢሮ ገብቶ 200 ካሬ ሳይሸለም የወጣ የኦሮሞ ልጅ አላውቅም፡፡ መገርሳ የሚባል ለአጭር ጊዜ ልዩ ረዳታቸው ሆኖ የሠራ ወጣት ያጫወተኝን መቼም አልዘነጋውም፡፡

ባንድ ወቅት ኦቦ አባዱላ የኦሮሚያ ፕሬዝዳንት ሳሉ አንድ የአቤቱታ ደብዳቤ ይቀርብላቸውና ዘለግ ላለ ጊዜ መልስ ሳይሰጡበት ይቆያሉ፡፡ ሥራ በዝቶባቸው ይሆናል ብላ ፀሐፊያቸው ማመልከቻውን ፈልጋ ጠረጴዛቸው ላይ ከፊት ለፊት አድርጋ አስቀመጠችላቸው፡፡ በነገታው ከወጪ ደብዳቤዎች ጋር ተቀላቅሎ ተገኘ፡፡ በደንብ ሲታይ ለካንስ ደብዳቤው ጀርባ ላይ የማመልከቻ ወረቀቱን ጫፍ አጥፈው የጻፉት ነገር ነበር፡፡ እንዲህ ይላል፤ “ከልዩ ዞኖች ክፍት ቦታ ተፈልጎ መመሪያው በሚፈቅደው መጠን ካርታ እንዲዘጋጅላቸው ቢደረግ” ይላል፡፡ ያቺ ከተክለሰውነታቸው ጋር በፍጹም የማትመጣጠን ፊርማቸው ከትእዛዙ ስር ሁሌም አብራ አለች፡፡

አባዱላ ደብዳቤው ላይ የጻፉት ነገር በዋና ፀሐፊያቸው ግራ መጋባትን ፈጠረ፡፡ ሲጀመር የደብዳቤው ጭብጥ የመሬት ጥያቄ አልነበረም፡፡ የአንድ “ለልዩ ስራ”ጅ ማ የተመደበ የክልሉ መንግስት ሰራተኛ በጤና ምክንያት ወደ ፊንፊኔ የሥራ ዝውውር ማድረግ እንዲችል ትብብር እንዲያደርጉለት ነበር የጠየቀው፡፡ ለዚያውም አስም አሳቃይቶት ነው የጠየቀው እንጂ ጨርሶውኑ የመሬት ጉዳይ አልነበረም፡፡ ለካንስ ኦቦ አባዱላ መሬት ማደል ለምዶባቸው ከርሱ በፊት በነበሩ ተከታታይ ደብዳቤዎች ላይ የጻፉትን እዚህም ላይ ጽፈውት ኖሯል፡፡ የደብዳቤውን ጭብጥ እንኳ በቅጡ ሳይረዱ ገና ለገና የመሬት ጥያቄ ይሆናል በሚል የመሩት ደብዳቤ ነው፡፡ ብቻ ታሪኩ ብዙ ነው፡፡

ዞሮ ዞሮ ያ ደብዳቤ ለኦሮሚያ መሬት አስተዳደር መሩት፡፡ አመልካቹ በግርግር 200 ካሬ አፈሰ፡፡ የዝውውር ጥያቄውንም እርግፍ አድርጎ ተወው፡፡ አስሙም በዚያው ተሻለው መሰለኝ፡፡ መገርሳ ራሱ ነው ይሄን ታሪክ የነገረኝ፡፡ መገርሳ ደግሞ አይዋሽም፡፡ ለምሳሌ ኦቦ ለማና ኦቦ ወርቅነህ ሰሞኑን ሙክታርና አስቴርን ሲተኩ በስብሰባው ላይ ከፍተኛ ድምጽ ያገኘው ግን ኦቦ አባዱላ እንደነበር ነግሮኛል፡፡ ይሄን ከሌላም ሰው አጣርቻለሁ፡፡ እውነት ነው፡፡ ኦቦ አባዱላ ግን ከንግዲህ የኦሮሚያ ሥልጣን በቃኝ! በኔ ይሄን ያህል እምነት ስላሳደራችሁ ግን ገለቶማ! ብለው ምርጫውን ዉድቅ አደረጉ፡፡ ከርሱ ቀጥሎ ተከታታይ ድምጽ ያገኙት ለማና ወርቅነህ ወዲያውኑ ሥልጣን ላይ ፊጥ አሉ፡፡ ሰሞኑን ጨፌው ያጸድቅላቸዋል፡፡ ሹመት ያዳብር ብዬ ወዲያው ሜሴጅ ልኪያለሁ፡፡ መገርሳ እንደነገረኝ ግን በድምጽ ቆጠራ ታሪክ በኦሮሚያ እስከ ዛሬ ትልቁን ድምጽ ያገኘውም አባዱላ ነው፡፡ ደግነቱ ለማ መገርሳም ሆነ ወርቅነህ የርሱ ግርፎች ናቸው፡፡ ገና አባዱላ ደኅንነት ቤት ተለማማጅ ሳለ ነው ሁለቱንም ኮትኩቶ ለዚህ ያበቃቸው፡፡ ከርሱ ቃል ፍንክች የማይሉትም ለዚህ ነው፡፡

ብቻ ያባዱላ ታሪኩ ብዙ ነው፡፡

ከኦህዴድ በሀብት የሚበልጠው የለም፡፡ ከሁለቱ የራሱ ሾፌሮቹ በስተቀር፡፡ የሁለቱ ሾፌሮቹ ታሪክ ተወርቶ እንዲሁ በዋዛ የሚያበቃ አይደለም፡፡ ስለዚህ አላነሳውም፡፡ “ሌላ በሐብት አባዱላን የሚገዳደረው የኦፒዲኦ ሰው ማን አለ?”ብዬ አብዝቼ አሰብኩ፤ አወጣሁ አወረድኩ፡፡ አንድም የለም፡፡ ምናልባት የገቢዎችና ጉምሩኩ ወንድሙ ቢራቱ፡፡ ምናልባት ነው እሱም!

ኦቦ አባዱላ በጽኑ የሚያምነው የኦሮሞ ልጅ አሁን ያለውን መረጋጋት ተጠቅሞ በኢኮኖሚ በብዙ መጠቀም እንዳለበት ነው፡፡ ኦሮሞ ተጨቁኛለሁ እያለ ማለቃቀሱን ትቶ አሁን ጊዜውና አቅሙ በፈቀደለት ሁሉ የቻለው መዝገን ነው ያለበት ብሎ በጽኑ ያምናል፡፡ ኦቦ አባዱላ መቼም ሁሌም ለኦሮሞ ልጆች ማድላቱም ለዚሁ ነው፡፡ ኦሮሞ ሙሰኞችን አይቶ እንዳላየ የሚሆነውም ለዚሁ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ለኦሮሞ ሕዝብ እንዲህ ብዙ ሐብት ለመዛቅ የተመቻቸ ጊዜ አይኖርም ብሎም ያምናል፡፡ እንደ አባዱላ አስተሳሰብ የኢኮኖሚ ጉልበት ሲኖር ነው የመብት ጥያቄ አንስቶ ዳር ማድረስ የሚቻለው፡፡ ለኦሮሞ ልጅ አብዝቶ ደግ የሚሆነውም ከዚህ አሰትሳሰቡ በመነሳት ነው ብለውኛል፡፡

ኦቦ አባዱላ አባ መስጠት ነው ብያለሁ፡፡ አዲስ ተጋቢ ሙሽሮችን የጆሮ ጉትቻም ሆነ የአንገት ሐብል ሸልሞ አያውቅም፡፡ የመሬት ካርታ እንጂ፡፡ አራስ ሲጠይቅ እንኳ የልጅ አልጋ ይዞ ሄዶ አያውቅም፤ የቁራሽ መሬት ካርታ እንጂ፡፡

አባዱላ ከባህሪው ሁሉ የሚደንቀኝ ግን ቢሞቱ ጥሬ ገንዘብ አለመስጠቱ ነው፡፡ ባንድ ወቅት መሬት ለግሶት ቤት መሥሪያ ለጠየቀው ቀዥቃዣ የኦፒዲኦ የወጣት አመራር “ኢጆሌ…ኦሮሞ ብልህ ነው! አንተ ግን ሰነፍ ነህ፡፡ ገንዘብ ከምትጠይቅ እጅህ ላይ ያለውን መሬት ግማሹን ሸጠህ በግማሹ አትሠራም?” እያለ በንቀት ሲመለከተው ባይኔ በብረቱ አይቻለሁ፡፡ ያኔ ለአንድ ጉዳይ ፈልጎኝ ሳርቤት እሱ ቢሮው ዉስጥ ተቀምጬ ነበር፡፡ ሁሌም እንደሚያደርገው የይርጋጨፌ ደረጃ አንድ ቡና ጋብዞኝ እርሱ ወዲያ ወዲህ ሲንጎማለል ግርማ ሞገሱ አይረሳኝም፡፡

እውነት ይነገር ከተባለ ሙልጭልጩ ጁነዲንም ሆነ ዉሽልሽሉ ኩማ፣ ቆፍጣናው ዓለማየሁ አቶምሳም(ነፍሱን ይማረው) ሆነ ግትሩ ሙክታር የኦቦ አባዱላን ሩብ ያህል እንኳ ለኦሮሚያ አልሰሩላትም፡፡ በኦሮሚያ መሬት አሁን ከሚታየው ኢንቨስትመንት 95 በመቶው በአባዱላ የግል ጥረት የተጀመረ ነው፡፡ ደግሞ ባለሀብቶቹን ለምኖ ነው ሥራ የሚያስጀምራቸው፡፡ እግራቸው ስር ወድቆ፡፡ ቱርኮች ኦሮሚያን የሚያውቋት ያባዱላ አገር እያሉ ነው፡፡ ሲበዛ ይወዱት ነበር፡፡ የኦሮሞ ወጣት እንዲጠቀም፣ የኦሮሚያ ምድር እንድትለማ ቀንተሌት ለፍቷል፡፡ ዩኒቨርስቲዎችን አስፋፍቷል፡፡ ሆስፒታሎችን አስገንብቷል፡፡ መንገድ ከፌዴራል መንግስት ጋር እየተናነቀ አሰርቷል፡፡ ሕዝቡ ይሄን አሳምሮ ያውቃል፡፡ በቀደም የሳይገን ዲማ ፋብሪካ መቃጠል ሲሰማ ስቅስቅ ብሎ ያለቀሰውም ለዚሁ ነው፡፡ ብዙ ሰው ሳይገን ዲማ ቱርኮች ካባዱላ ጋር በሼር የከፈቱት ፋብሪካ ይመስለዋል፡፡ አይደለም፡፡ እውነታው ሌላ ነው፡፡ ቱርኮች በኦሮሚያ ኢንደስትሪ መንደር እንዲከፍቱ አባዱላ አንካራ ድረስ ሄዶ ለምኖ፣ በኔ ይሁንባችሁ ብሎ ካስመጣቸው ዉስጥ ሳይገን ዲማዎች የመጀመርያዎቹ ስለነበሩ ነው፡፡ ፋብሪካው ሲቃጠል መጀመርያ የደወሉት ፖሊስ ጋር አልነበረም፡፡ እርሱ ጋር እንጂ፡፡

በኦሮሚያ ብዙዉን መንገድ፣ ጤና ጣቢያና ፋብሪካ ያስገነባው በጉልበቱ ነው፡፡ በሱ ዘመን ከበጀት ስባሪ ሳንቲም ወደ ፌዴራል አትመለስም፡፡ ከምትመለስ የኦሮሞ ልጅ በሙስና ቢበላት ይመርጣል፡፡ ዛሬ የሚገነቡት ግዙፍ ስቴዲየሞች ሁሉም የርሱ ዉሳኔዎች ናቸው፡፡ አይበለውና እዚች አገር የከፋ ቀውስ ቢፈጠር የኦሮሞ ሕዝብ ኦህዴዶችን ቀቅሎ ሊበላቸው ይችል ይሆናል፡፡ አባዱላን ግን ጫፉን የሚነካው የሚኖር አይመስለኝም፡፡ ቢከፋ የቁም እስረኛ ቢያደርጉት ነው፡፡

አባዱላ የኦሮሞ ወጣትን አብዝቶ ይወዳል፡፡ ሁሉንም እንደ ልጁ ነው የሚያየው፡፡ ልክ እንደኮሚቲያስ፡፡ ኮሚቲያስ የአባዱላ ልጅ ነበር፡፡ እንደ ብዙዎቹ የባለሥልጣን ልጆች ሱስ አናውዞት ገና በ30 ዓመቱ ተቀጠፈ፡፡ እሱን ለማዳን የባሕል ሕክምና እንኳ አልቀረውም፡፡ ኮሚቲያስ ግን በጄ አላለም፡፡ ወሎ ሰፈር ከዱሪዮች ጋር ሲቅም ሲያጨስ እድሜውን ባጭር ቀጨ፡፡

ኦቦ አባዱላ መጽሐፍ ቢያነብ ይወዳል፡፡ ግን ደግሞ ቶሎ ይደክመዋል፡፡ ከንባብ ይልቅ መሳቅ ነው አመሉ፡፡ እኔን የሚወደኝም ለዚህ ይመስለኛል፡፡ በተለይ የደኢህዴን ሰዎችን ሳማለት እየተርገፈገረ ነው የሚስቀው፡፡ ለምን እንደሆነ አላውቅም ደኢህዴኖች ያስቁታል፡፡ ኦቦ ቀልድ ነፍሱ ነው፡፡ በተለይ የኦሮሚኛ ጆኮችን የሚነግረው ሰው ወዲያውኑ በልቡ ልዩ ሥፍራን ያገኛል፡፡ አባዱላ ከሳቀ ደግሞ የቁራሽ መሬት ሽልማት አለ፡፡ አንድ ቀን በአዳማ ቀኑን ሙሉ ሰብስቧቸው ማታዉኑ ሕዝብ ስለሱ የሚቀልደውን እየነገሩ በሳቅ ሲያርገፈገፉ ላስመሹት የኦሮሚያ ቲቪ 5 ጋዜጠኞች ለሁሉም ሁለት ሁለት መቶ ካሬ መሬት ስጧቸው ብሎ የቃል ትዕዛዝ ሰጠላቸው፡፡ ምንዋጋው ወዲያው ዓለማየሁ አቶምሳ መጥቶ ጉሮሯቸው ላይ ቆመ፡፡

እና ባጠቃላይ ምን ለማለት ፈልጌ ነው፡፡ አባዱላ ጥሩ ሰው ነው፡፡ ሰው ሙሰኛ ነው ይለዋል፡፡ እሱ ግን በልቶ የሚያበላ፣ ሰርቶ የሚያሰራ ደግ ኦሮሞ ነው፡፡ ደግሞስ እስቲ ከሙስና ነጻ ነኝ የሚል እጁን ያውጣ! ኦህዴድ ራሷ ተጠፍጥፋ የተሰራችው ሙስና ከሚባል ጭቃ አይደለምን?

ብቻ ሆድ ይፍጀው!

በምን ነበር ግን ይሄን ሁሉ ወሬ የጀመርነው? በኦህዴዶች!

አው! ኦህዴዶች ደንበኞቼ ነበሩ፡፡ ከሰሞኑ ግን ንብረት ሽያጭ ላይ ትኩረት አድርገው እኔንም አስጨነቁኝ፡፡ በፊት ዉድ ቤት በፊንፊኔ ገዢ ካጣሁለት ኦህዴዶች ጋር ነበር የምወስደው፡፡ አሁን ግን ነገሩ ተገለበጠ፡፡ ሻጭ እንጂ ገዢ ጠፋ፡፡ በፉሪ፣ በአለምገና፣ በሆለታ፣ በሰበታ…ሁሉም ነዋሪ ቤቱን ሽጦ መውጣት ነው ሕልሙ፡፡ እኔ ታዲያ ለዚሁ ሁሉ ሻጭ ገዢ ከየት ላምጣ፡፡

ክፉ ጊዜ! ሻጭ እንጂ ገዢ የጠፋበት!