Lamberet Bus Terminal -FILE
Lamberet Bus Terminal -FILE
  • ሾፌሮች ወደ አማራና ኦሮሚያ ክልል መጓዝ አልቻሉም
  • የኦሮሚያ አመፅ የአዲስ አበባን ገበያ አቀዝቅዞታል

ዋዜማ ራዲዮ-በመንግስት ኃይሎች በተለያዩ አካባቢዎች የተገደሉ ዜጎችን በሃዘን አስቦ ለመዋል እና መንግስት የሚወስዳቸውን እርምጃዎች ለመቃወም በማህበራዊ ድረ-ገጾች የተደረገ ጥሪን ተከትሎ በርካታ ወደ አማራ ክልል የሚጓዙ የአውቶቡስ ሾፌሮች ጉዞዎቻቸውን እንደሰረዙ የዋዜማ ምንጮች አረጋገጡ።

ወደ ኦሮሚያ ክልል የሚደረጉ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎቶች ቀደም ብለው መቋረጣቸውን የገለፁት በተለምዶ አውቶቡስ ተራ መናኸሪያ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የጉዞ ተራቸውን እየጠበቁ የሚገኙ ሾፌሮች፣ ከጷጉሜ አንድ ጀምሮ ወደ አማራ ክልል ጉዞ ለማድረግ ዝግጅቶቻቸውን አጠናቀው እንደነበር ይናገራሉ። ሆኖም ” ‘መኪናውን ሳይሆን እናንተን ነው የምንነካው’ የሚል ማስጠንቀቂያ ስለደረሰን ጉዞዎቻችንን ሰርዘናል” ይላሉ።

ማስጠንቀቂያውን ተከትሎ ወደ አማራ ክልል የተለያዩ ክፍሎች ምንም አይነት የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት እየተሰጠ እንዳልሆነ ሾፌሮቹ ተናግረዋል። አዲስ አመትን ተከትሎ የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል መስከረም 2 ቀን 2009 ዓ.ም ስለሚከበር በምትኩ ወደ ደቡብ ክልል የተለያዮ ክፍሎች ተሳፋሪዎችን እያደረሱ እንደሆነ ገልፀዋል።

ከአዲስ አበባ ሆለታ፣ አዲስ አለም፣ ጊንጪ፣ አምቦ፣ ጉደር፣ ጌዶ፣ ባኮ፣ ነቀምት እና ጊምቢ አልፎ አልፎ ካልሆነ በቀር በየከተሞቹ ምንም አይነት የህዝብ ማመላለሻ አገልግሎት ሰጪዎች እንደማይታዮ በአምቦ ከተማ የሚገኙ ምንጮች ለዋዜማ ተናግረዋል። በከተማዋ ውስጥ የባጃጅ ትራንስፖርት አገልግሎት እንኳ እንደማይሰጥ ያስረዳሉ።

በኦሮሚያ በርካታ ከተሞች የሚገኙ አገልግሎት ሰጪዎች ድርጅቶቻቸውን ለቀናት እንደዘጉ ከክልሉ ለሚወጡ ሪፖርቶች ያመለክታሉ። በአምቦም ተመሳሳይ ሁኔታ ቢስተዋልም ትልልቅ ሆቴሎች በመንግስት አካላት በሚደርስባቸው ጫና አገልግሎት ለመስጠት እንደተገደዱ ምንጮች ይናገራሉ።

በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ጀነራል ዊንጌት የቴክኒክ እና ሙያ ማሰልጠኛ ት/ቤት በተለምዶ ዊንጌት አደባባይ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ለወትሮው የአዲስ አመት የበግ ሽያጭ የደራ እንደነበር ያስታወሱት የዋዜማ ምንጭ ደጋግመው ወደ ገበያው የበግ ዋጋ ስንት እንደገባ ለመጠየቅ እንደሄዱ ተናግረው “ቆሞ በጎቹን ለመግዛት ዋጋ የሚጠይቅ የለም ስለዚህ ተመልሻለው” ብለዋል።

ሌላው የዋዜማ ሪፖርተር በአዲስ አበባ የታዘበውን እንደወረደ አቅርበነዋል

ዛሬ ጳጉሜ 4 ነው።በዚህ ቀን የተለያዩ አካባቢዎችን ተዘዋውሬ ተመልክቼ ነበር በተለይም እንስሶች ወደ አዲስ አበባ በሚገቡባቸው አካባቢዎች ያለው እንቅስቃሴ ፍፁም የተቀዛቀዘ ነው።አልፎ አልፎ በተወሰኑ አካባቢዎች ከሚታዩ የችቦ ሽያጮች ውጭ የበአል ሰሜት የሚናገር እንቅስቃሴ ለማየት አይቻልም።
የዚህ ሁሉ ምክንያቱ በሀገሪቱ እየታዬ ያለው የህዝብ ተቃውሞ መሆኑ ይሰማል።
ትላንት ሱሉልታና ቡራዩ አካባቢዎች ሱቆች ዝግ ነበሩ ወደ መሀል ከተማም ለበአል የሚሆኑ እንስሶች እንዳይገቡ በራሳቸው በገበሬዎቹ ማዕቀብ መደረጉን ተረድቻለሁ።
አሁን በአዲስ አበባ የሚታየው ድባብ ሁኔታ እንኩዋንስ የዘመን መለወጫ ይቅርና ወርሃዊ የንግስ በአሎች እንኩዋን ሲከበሩ የሚታየውን ያህል መሆን አልቻለም።የከተማው ህዝብ ጋር ያለው የበአል ስሜት ፍፁም የቀዘቀዘ ነው።በተጨማሪ ለበአል ዝግጅት አስቀድሞ የተያዙ የሙዚቃ ኮንሰርቶችን መሰረዛቸው የበአሉን መንፈስ የበለጠ አደብዝዞታል።


ዛሬ ጳጉሜ 5 ቀን በአዲስ አበባ የተሻለ የበአል ስሜት ይታያል ከትላንቱ አንፃር ። በተለያዩ ገበያዎችም ላይ ተገኝቼ ነበር ሰው ሲሽምት ተመልክቻለሁ።የገበያ ዋጋው ካለፉት ጊዜአት ጋር ሲመሳከር ርካሽ ይመስላል ለዚህም ዋናው ምክንያት እንደ ሌሎች ጊዜያቶች ሽማቹ በብዛት ባለመውጣቱ ነው ሲሉ ነጋዴዎች ነግረውኛል።
የሆነ ሆኖ ግን ከትላንት በተሻለ ዛሬ የበአል ስሜት በአአ ላይ ተመልክቻለሁ።