Fire on Kilinto prison/PHOTO Reporter
Fire on Kilinto prison/PHOTO Reporter

ዋዜማ ራዲዮ-ተቃዋሚ የፓለቲካ አመራሮችን እና ጋዜጠኞችን ጨምሮ ከሶስት ሺህ በላይ እስረኞችን የሚይዘው የአዲስ አበባ ቅሊንጦ ማረሚያ ቤት በእሳት ጋየ።

በፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ስር የሚገኘው የቂሊንጦ ጊዜያዊ የእስረኞች ማቆያ ዛሬ ጠዋቱን በግቢው በተነሳ የእሳት አደጋ ቃጠሎ የደረሰበት ሲሆን ቁጥራቸው ያልታወቁ ታራሚዎች መጎዳታቸውን የዓይን እማኞች ገልፀዋል፡፡

የእሳት አደጋው የተነሳው ጠዋት ሶስት ሰዓት ገደማ እንደነበር እና ቃጠሎውን ተከትሎም የተኩስ ድምፅ በተከታታይ መሰማት መቀጠሉን በአካባቢው የነበሩ እማኞች ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡ እሳቱ የተቀሰቀሰው የቂሊንጦ እስር ቤትን ከሚጎራበተው የአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ አቅጣጫ እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡ ጥቂት ቆይቶ የአስተዳደር ቢሮዎች እና አዳራሽ ወደሚገኙበት ቦታ እንደተዛመተም ያብራራሉ፡፡

ለዩኒቨርስቲው የሚቀርበው የእስረኞች ቦታ በእስር ቤቱ አጠራር ዞን አንድ ተብሎ የሚታወቀው ቦታ ነው፡፡ በተለምዶ ወደ ሶስት ሺህ ገደማ እስረኞችን በውስጡ የሚይዘው የቂሊንጦ እስር ቤት በሶስት ትልልቅ ዞኖች የተከፋፈለ ነው፡፡ ምርጫ 2007ን ተከትሎ አነስተኛ የሆነ እና በቆርቆሮ የተሰሩ ማረፊያ ቤቶችን የያዘ አራተኛ ዞን የተገነባ ሲሆን በፖለቲካ ሰበብ ለእስር የተዳረጉ እሰረኞችን ከሌሎች ለመለየት በሚል አንድ አነስተኛ ዞን በቅርቡ ተጨምሯል፡፡

ቃጠሎው በየቦታው መስፋፋቱን ተከትሎ የእስር ቤቱ ፖሊሶች ዙሪያውን ከበው መተኮስ መጀመራቸውን እና የእስረኞች የጩኸት ድምጽ ከርቀት ሁሉ ጎልቶ ይሰማ እንደነበር በቦታው የነበረ የዋዜማ ምንጭ ይናገራል፡፡ ተኩሱ ለ40 ደቂቃ ያህል ግድም መቆየቱንም ይገልጻል፡፡ የተኩሱን ድምጽ የሰሙ በአቅራቢያው የሚገኙ የፌደራል የፖሊስ ኃይሎች ከጥቂት ጊዜ በኋላ መድረሳቸውንም ያስረዳል፡፡

በአንድ ኤፍ ኤስ አር ሙሉ የተጫኑ ፖሊሶች ወደ ግቢው ሲገቡ ተመልክቻለሁ የሚለው የዋዜማ ምንጭ በትንሹ በአምስት ፒክ አፕ መኪኖች የተጫኑ ተጨማሪ ፖሊሶችም ወደ ቦታው ሲያመሩ ማየቱን ይገልጻል፡፡

የተኩስ ድምጽ መሰማት ሲጀመር ከእስር ቤቱ አጠገብ በመሆን ለእስረኞች የሚፈቀዱ ሸቀጣ ሸቀጦችን የሚሸጡ የመንገድ ዳር ነጋዴዎች በፍጥነት መበታተናቸውን ሌላ የዓይን እማኝ ትናገራለች፡፡ የእስረኛ ጠያቂዎች ጉዳዩን ለማጣራት ወደ ቦታው ሲጠጉ ፖሊሶች ይመልሷቸው እንደነበርም ታስረዳለች፡፡

እኩለቀን ሊሆን ግማሽ ስዓት እስኪቀረው ድረስ በእስር ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ከፍተኛ ተኩስ ይሰማ የነበረ ሲሆን ወደ እስር ቤቱ የሚያስኬዱ መንገዶች ሁሉ በፀጥታ ሃይሎች ተዘግተዋል።

ቅሊንጦ ከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ በኦሮሚያ ክልል የተነሳውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የሽብር ክስ የተመሰረተባቸው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ በርካታ የፓለቲካ አመራሮች ፣ የኢትዮጵያ የሙስሊሞች ጉዳይ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ከፊል አባላት እንዲሁም ጋዜጠኞች ለአመታት የፍርድ ሂደታቸውን ታጉረው የሚከታተሉበት ስፍራ ነው።

በእስር ቤቱ ደንብ መሰረት የቅዳሜ እና እሁድ የእስረኞች መጠየቂያ ሰዓት ለግማሽ ቀን የተገደበ ነው፡፡ ጠያቂዎች ሁለት ሰዓት ተኩል አከባቢ ስማቸው እና የሚጠይቁትን ሰው አስመዝግበው ወደ ግቢው እንዲገቡ ይፈቀድላቸው ነበር፡፡ ቀናቱ የዕረፍት ቀን እንደመሆናቸው መጠን እና በርካታ ጠያቂዎች የሚስተናግዱበት በመሆኑ ብዙዎች በእስር ቤቱ አካባቢ የሚገኙት ማልደው ነው፡፡

በጠያቂዎች በኩል በዛሬው ዕለትም ተመሳሳይ ሁኔታ እንደነበር የዓይን እማኞች ይናገራሉ፡፡ በፖሊሶች አማካኝነት ከቦታው እንዲርቁ የተደረጉት ጠያቂዎች እና የአካባቢው ሰዎች በአንድ በኩል ከጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል እንዳያልፉ መደረጉን እና በሌላኛው አቅጣጫ ደግሞ ሄንከን ቢራ ፋብሪካ ጋር መንገድ መዘጋቱን ያብራራሉ፡፡

ከእስር ቤቱ የሚትጎለጎለውን ጭስ በርቀት ሆነው የሚያስተውሉት ጠያቂዎች እና የአካባቢው ነዋሪዎች አምቡላንሶች ወደ ቂሊንጦ እየተመላለሱ የተጉዱ ሰዎችን ጭነው በፍጥነት ወደ ህክምና መስጫ ቦታዎች ሲሄዱ መመልከታቸውን ያስረዳሉ፡፡ አምቡላንሶቹ መጀመሪያ ላይ በቂሊንጦ አቅራቢያ ወደሚገኘው ጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል ሲገቡ ይታዩ የነበረ ሲሆን በስተኋላ ላይ ግን ሞልቷል በማባሉ ተጎጂዎችን ይዘው ወደ ቃሊቲ አቅጣጫ ሲሄዱ እንደነበር ይገልጻሉ፡፡

እስካሁን ድረስ ቁጥራቸው ያልታወቀ ታራሚዎች መጎዳታቸው ቢነገርም ትክክለኛ መረጃ ማግኘት ግን አዳጋች ሆኗል፡፡ አደጋው መከሰቱን ያመነው የአዲስ አበባ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከል እና መቆጣጠር መስሪያ ቤትም ሶስት የአደጋ ጊዜ ሰራተኞቹ ላይ ጉዳት መድረሱን ከመናገር ውጭ በእሰረኞች ላይ ስለደረሰው አደጋ ከመናገር ተቆጥቧል፡፡

በእስር ቤቶች ላይ የሚደርስ የእሳት ቃጠሎ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተደጋጋሚ ሲከሰት የሚስተዋል ጉዳይ ሆኗል፡፡ በዚህ ዓመት ብቻ በርካታ ሰዎች የተጎዱባቸው ተመሳሳይ አደጋዎች በጎንደር እና በደብረ ታቦር እስር ቤቶች ተከስቶ ነበር፡፡