Textile industry- Photo FILE
Textile industry- Photo FILE

ዋዜማ ራዲዮ- በኢትዮጵያ የተባባሰውን ህዝባዊ አመፅ ተከትሎ በሀገሪቱ በኢንቨስትመንት የተሰማሩ የውጭ ባለሀብቶችና ኩባንያዎች አጣብቂኝ ውስጥ መውደቃቸውን ለዋዜማ የደረሰ መረጃ አመለከተ። በኢነርጂና በኢንደስትሪ ዘርፍ ከዩናይትድ ስቴትስ ወደ ኢትዮጵያ በመሄድ የሚንቀሳቀሱት ሶስት ትልልቅ ኩባንያዎች ከዓለም አቀፍ የኢንሹራንስ ደንበኞቻቸውና ከአሜሪካ የፀጥታ ተቋማት ጋር መነጋገራቸውን ለመረዳት ችለናል።

“በሀገሪቱ ያለው የፀጥታ ሁኔታ የማይሻሻል ከሆነና መንግስት በሙሉ ሀይሉ አገልግሎት ወደመስጠት ካልተመለስ በሀገሪቱ ውስጥ መቆየት አደገኛ ይመስላል” ይላል ከኩባንያዎቹ አንዱ ስለ ሰሞኑ ሁኔታ በገመገመበት ሰነዱ ላይ።

ዩናይትድ ስቴትስ ከሰላሳ በላይ የኢንቨስትመንት ፕሮጀችቶች በኢትዮጵያ ያላት ሲሆን ቢያንስ አምስቱ ከመሰረተ ልማትና ግንባታ ጋር የተያያዙ ናቸው።

በአማራ ክልል በሆላንድ በጣልያን በህንድና በቤልጂየም ኩባንያዎች ላይ የደረስው ጥቃት ክፉኛ እንዳስደነገጣቸው ኩባንያዎቹ አልሸሸጉም።

“ባለስልጣናቱ አግኝተው ሊያነጋግሩን እንኳን ጊዜ የላቸውም፣የበታች ሰራተኞች ደግሞ የምናውቀው የለም ብለውናል። በአሜሪካ ኤምባሲ በኩል ጠቅላይ ሚንስትሩን ለማነጋገር እየሞከርን ነው” ይላሉ ከከፍተኛ ኢንቨስትመንት ኩባን ያዎች የአንዱ ሀላፊ።

ከኧርነስት ያንግ አማካሪ ድርጅት ሀላፊ ዘመዴነህ ንጋቱ መነጋገራቸውን የገለፁት ሌላው የኢንደስትሪ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ አቶ ዘመዴነህ ሁኔታው በቅርቡ እንደሚረጋጋና ከመንግስት አቅም በላይ እንዳልሆነ ነግሮኛል ብለዋል።
“በዘመዴነህ ፊት ላይ ግን አየው የነበረው ጥርጣሬና ስጋት ነበር፣ ከኔ የባሰ ሁኔታው ሳያሳስበው የቀረ አይመስለኝም”ሲሉ አብራርተዋልለድርጅታቸው ባለድርሻዎች ገለፃ ባደረጉበት የፅሁፍ መልዕክት።

“ምንም እንኳ እኛ ፋይናንስ የማንቀሳቀስ ችግር ባይገጥመንም ሸሪኮቻችን የሆኑ ሌሎች ድርጅቶች ባንክ አካባቢ ምንዛሪ ያለመኖሩና አስራሩም እየተወሳሰበ መምጣቱ ከፀጥታ ችግር ጋር ተዳምሮ ስራችንን እያስተጓጎለው ነው”ሲሉ ያክላሉ ሀላፊው።

“ህዝቡ ኢንቨስተሮችን የመንግስት ደጋፊ አድርጎ ስለሚያይ በእንደዚህ አይነቱ ወቅት ተጥቃት ዒላማ ያደርጋቸዋል”ብለዋል።

ባለፉት ቀናት ከራሳችን ስራተኞችና ከነዋሪዎች እንደሰማነው በመንግስት ላይ ጥላቻው አይሏል፣ መንግስት ሁኔታውን ማለዘብ ካልቻለ የተረጋጋ ሰራ መስራት አይቻልም እንደ ሀላፊው አስተያየት።
በዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሀን በኢትዮጵያ ስላለው ቀውስ ተደጋጋሚ ዘገባ እየቀረበ መሆኑ በምዕራቡ አለም ያሉና ኢትዮጵያን ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ አድርገው ለሚያስቡ አቋማቸውን በድጋሚ እንዲፈትሹ እያደርጋቸው ነው።

በኢትዮጵያ ባለው የኢንቨስትመንት ስራ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው የእስያና የአረብ ሀገራት ሲሆኑ ቻይና ቱርክ ህንድ ሳዑዲ አረቢያና ሱዳን ከቀዳሚዎቹ ይገኙበታል።

የኢትዮጵያ መንግስት የውጭ ሀገር ባለሀብቶችን ለማነጋገር ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ስምተናል።