Fincha Sugar Factory

ዋዜማ – ከጥቂት ዓመታት በፊት ሀገሪቱ በቢሊየን የሚቆጠር ብድር አፈላልጋ በሀገሪቱ አስር የስኳር ፋብሪካዎችን ለመገንባትና ያሉትን ለማዘመን ስራ ጀምራ ነበር። የብዙዎቹ ግንባታ ተካሂዷል። የኦሞ ኩራዝ አካባቢ አራት ፋብሪካዎች 35 ቢሊየን ብር ወጥቶባቸው ተገንብተዋል። መንግስት እነዚህ ፋብሪካዎች አዋጭ አይደሉም በሚል ወደ ግል ይዞታ እንዲዛወሩ ያለፉትን ሶስት አመታት ዝግጅት ሲያደርግ ነበር። 

ፋብሪካዎቹ አሁንም ጉዳያቸው በእንጥልጥል እንዳለ ነው። ከተመሰረተ 45 አመታትን ያስቆጠረው ነባሩ  የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ በመስከረም ወር ስራ እንደሚጀምር ቢጠበቅም አልተሳካለትም። በተጨማሪም በመንግስትና ኦነግ ሸኔ መካከል በሚፈጠረው ተደጋጋሚ ግጭት መደበኛ ተግባሩን ማከናወን አልቻለም።ዋዜማ ጉዳዩን ከድርጅቱ ሰራተኞች ጠይቃ ለመረዳት ሞክራለች።

በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን የሚገኘው ፊንጫ ስኳር ፋብሪካ፣ በወቅቱ የሚያስፈልገው ጥገና ሊደረግለት ባለመቻሉ እና ፋብሪካው በዋናነት ጥቅም ላይ የሚያውላቸው፣ ፋይቭራዘር እና ሸራውድ የተሰኙት ማሽኖች ከአገልግሎት ውጪ በመሆናቸው ምክንያት ሙሉ ለሙሉ ስራ ማቆሙን የፋብሪካው ሰራተኞች ለዋዜማ ተናግረዋል። 

ፋብሪካው ከዚኽ ቀደም ባለው ልምድ መሠረት፣ ክረምት ላይ ጥገና ተደርጎለት መስከረም ወር ላይ ወደ ሥራ ይገባ እንደነበር የገለፁት ምንጮች፣ አኹን ላይ ግን አስፈላጊ የሚባሉት የማምረቻ ቁሳቁሶች ጭምር ባለመሟላታቸው ስራ ማቆሙን ገልፀዋል። 

ፋብሪካው ስራ ያቆመው በቀደመው ዓመት ሚያዚያ ወር ላይ እንደሆነ የጠቀሱት የፋብሪካው ሰራተኞች፣ አስፈላጊዎቹ ማሽኖች ተሟልተው፣ ፋብሪካው ወደ ስራ እንዲገባ በተደጋጋሚ ጥያቄያቸውን ለፋብሪካው አስተዳደር ቢያቀርቡም፣ ማሽኖቹ ከውጭ እንደሚገቡ እና እስከዛሬ የዘገየቱም በውጭ ምንዛሬ ዕጥረት እንደሆነ ሲነገራቸው ከመሰንበቱ ውጪ በተግባር የተደረገ ነገር እንደሌለም ጠቁመዋል።

በፋብሪካው ከ2 ሺ 700 በላይ ቋሚ እና ከ 8 ሺ በላይ ጊዜያዊ ሰራተኞች እንዳሉ የተገለፀ ሲሆን፣ ፋብሪካው አስፈላጊው ጥገና ተደርጎለት በቅርቡ ስራ የማይጀምር ከሆነ ደሞዛችን ሊቆም ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንዳሉ ለዋዜማ ተናግረዋል። 

በአካባቢው የሚኖሩ ከ70 ሺ በላይ ሰዎችም ህልውናቸው ከዚሁ ፋብሪካ ጋር የተገናኝ እንደመሆኑ፣ ወደ ስራ የማይገባ ከሆነ የእነዚህ ነዋሪዎች ሕይወትም አደጋ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ዋዜማ ለመረዳት ችላለች። 

ፋብሪካው ከጊዜ ወደ ጊዜ የማምረት አቅሙ በከፍተኛ መጠን እያሽቆለቆለ መሄዱን የጠቀሱት ምንጮች፣ ከዚህ ቀደም በዓመት ከ1.2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ስኳር ያመርት የነበረ ሲሆን፣ ስራ እስኪያቆም ድረስ በዓመት ከ200 ሺ ኩንታል ያነሰ የስኳር ምርት ብቻ ሲያመርት እንደነበርም አስረድተዋል፡፡ ለዚህም በዋናነት እንደ ምክንያት የተጠቀሰው ለምርት የሚያስፈልጉ ማሽነሪዎች አለመሟላታቸው እና በስራ ላይ ያሉትም ዕድሳት ከተደረገላቸው ብዙ ጊዜ በመቆጠሩ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ 

በሌላ በኩል ፋብሪካው ከ35 ሺ ሄክታር በላይ የሸንኮራ አገዳ ማልሚያ መሬት ቢኖረውም፣ በአካባቢው ባለው ከፍተኛ የፀጥታ ችግር የተነሳ ለስኳር  ምርት ግብአት የሚሆነውን የሸንኮራ አገዳ እንደሚፈለገው ለፋብሪካው ማቅረብ አለመቻሉም ለዚህ መሰሉ የምርት ማሽቆልቆል አንዱ ምክንያት መሆኑም ተጠቅሷል። 

የሸንኮራ አገዳውን ለማምጣት፣ ፋብሪካው ካለበት ቦታ ከ35 እስከ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ያህል መጓዝ እንደሚያስፈልግ የጠቀሱት ሰራተኞቹ፣ በዚያ አካባቢ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና ራሱን የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ብሎ በሚጠራው ታጣቂ ቡድን መካከል ከፍተኛ ውጊያ በመኖሩ የተነሳ፣ ያንን ማድረግ አለመቻሉን ተናግረዋል። 

ይኽም በአካባቢው የሸንኮራ አገዳ ለፋብሪካው በማቅረብ ለሚተዳደሩ አርሶ አደሮች የነበረውን የስራ ዕድል እንዲዘጋ በማድረጉ የተነሳ፣ አርሶ አደሮቹ ችግር ላይ መውደቃቸውንም ጭምረው ነግረውናል፡፡ በተጨማሪም በፋብሪካው ውስጥ ለምርት ስራ የሚውሉ ማሽነሪዎች፣ ተሸከርካሪዎች እንዲኹም የተለያዩ ቁሳቁሶች ላይ በሁለቱ ኃይሎች መካከል በየጊዜው በሚደረጉ ግጭቶች ከፍተኛ ውድመት እንደሚደርስም ተናግረዋል፡፡   

በፋብሪካው ውስጥ ሌላው እንደ ችግር የሚነሳው የደሞዝ ጉዳይ መሆኑን የጠቀሱት ዋዜማ ያነጋገረቻቸው የፋብሪካው ሰራተኞች፣ ደሞዝ ወቅቱን ጠብቆ ሊከፍል አለመቻሉ ሌላኛው ተግዳሮት መሆኑን ጠቅሰዋል። 

በዚኹ ምክንያት ከሦስት ዓመት ወዲኽ ከ1 ሺ በላይ የሚሆኑ የፋብሪካው ቋሚ ሰራተኞች ስራ መልቀቃቸውንና አኹን ላይ 2ሺ 700 የሚሆኑ ሰራተኞች ብቻ ከመኖራቸው ባለፈ፣ ወደ 10 ሺ ይጠጉ ከነበሩት የቀን ሰራተኞች መካከል 8ሺ ያህሉ ብቻ አሁን በስራ ላይ እንዳሉ እኒኹ የዋዜማ ምንጮች ጠቅሰዋል። 

ሰራተኞቹ አክለው እንደተናገሩት፣ ስለ ደሞዝ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች አስተዳደር ክፍሉን በምንጠይቅበት ወቅት፣ “ፋብሪካው ይቀጥል፣ አይቀጥል ባልታወቀበት ሁኔታ ስለ ደሞዝ ለማውራት ያስቸግራል” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸውም ነግረውናል፡፡ 

የፋብሪካውን አመራሮች በስልክ ለማነጋገር ጥረት ብናደርግም መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል። [ዋዜማ]