Ethio Engineering Group HQ

ዋዜማ- በቀድሞ አጠራሩ የኢትዮጵያ ብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ይባል የነበረው እና በኢትዮጵያ የፖሊቲካ ለውጥ ከተደረገ በሁዋላ ወታደራዊ ምርቶች በመተው እንደ አዲስ በተዋቀረው ኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ስር ያለው የፓወር ኢኪውፕመንት ማምረቻ ፋብሪካ ስምንት አመራሮች ከብረት ስርቆት ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ዋዜማ ከምንጮቿ አረጋግጣለች።

በቁጥጥር ስር የዋሉት የፋብሪካው አመራሮች አንዱአለም ለገሰ የፓወር ኢኪውፕመንት ማምረቻ ስራ አስኪያጅ፣አልማዝ ብርሀኑ የፋብሪካው የሎጂስቲክስ ሀላፊ ፣ መብርሂት ተስፋዬ የፋብሪካው ንብረት አስተዳደር ፣ አሚኑ መሀመድ የፋብሪካው ጥበቃ ሀላፊ ፣  እንዲሁም ይበልጣል ተረፈ ፣  ብርሀኑ ስዩም እና ፍቃዱ ማሞ የተባሉ አመራሮች ናቸው።

የድርጅቱ ሌሎች ሀላፊዎች  ሁሉም አመራሮች ከብረት ስርቆት  ጋር በተያያዘ ከመታሰራቸው ውጭ ጉዳዩ በፖሊስ ስለተያዘ በሚል ምክንያት ዝርዝሩን ከመጥቀስ ተቆጥበዋል።

ዋዜማ ከሌሎች ምንጮች ለእንዳጣራችው ፣ በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የፓወር ኢኪውፕመንት ማምረቻ ፋብሪካ አመራሮች የታሰሩት ተቋሙ በጨረታ ከሸጠው ቁርጥራጭ ብረት ስርቆት ጋር በተያያዘ ነው። 

የፓወር ኢኪውፕመንት ማምረቻ ፋብሪካው ከዚህ ቀደም በርካታ መጠን ያለውን ቁርጥራጭ ብረቶችን ጨረታ በማውጣት ሸጦ ነበር። ለጨረታ ከቀረበው ቁርጥራጭ ብረት ውስጥ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተመርቶ የነበረና በሁዋላ ለግድቡ አይመጥንም ተብሎ ፣ እንዲሁም  ለግድቡ የብረታ ብረት ስራዎች ተቋራጭ በመቀየሩ ምክንያት ተቆራርጦ እንዲሸጥ የተደረገ የውሀ ማፋሰሻ የተሰራበት ብረትም ይገኝበታል

የፓወር ኢኪውፕመንትስ ማምረቻ ፋብሪካ ሀላፊዎች ከተጠረጠሩበት የብረት ስርቆት ውስጥ በጨረታ የተሸጠ ብረት ውስጥ የጨረታ አሸናፊው ከቦታው ሳያነሳው ከመጠኑ ማጉደል ይገኝበታል ተብሏል። 

ብረቱ ተከማችቶ የነበረውም አዲስ አበባ ጎሮ እየተባለ ከሚጠራው ሰፈር አቅራቢ ያለው ቦሌ ካባ የሚባል አካባቢ ነው። ቁርጥራጭ ብረቱ በጨረታ ሲሸጥ በ10 ሚሊየኖች ብሮች አስገኝቷልም መባሉን ነው ዋዜማ የሰማችው። ተጠርጣሪዎቹ ህዳር 7 2016 አ.ም ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል። [ዋዜማ]