Solomon Alemu, Fana Broadcast editor in Chief ( Photo-SM)

ዋዜማ- ለመንግስት ቅርብ በሆኑና በገዥው ፓርቲ በሚተዳደሩ የመገናኛ ብዙሀን ሲሰሩ የነበሩ አራት ጋዜጠኞች ሀገር ጥለው መኮብለላቸውን ከተለያዩ ምንጮች አረጋግጠናል። 

ባለፉት ስድስት ወራት ቢያንስ አስራ ሶስት የግል መገናኛ ብዙሀንና የብይነመረብ ጋዜጠኞች ከሀገር መሰዳዳቸውን ዋዜማ ያሰባሰበችው መረጃ ያመለክታል። የግል መገናኛ ብዙሀን ጋዜጠኞች ስደት ባለፉት ሶስት አመታት በርከት ብሎ የታየ ቢሆንም ያለፉት ሶስት አስርት ዓመታት የየዕለት ክስተት ነበረ። 

የመንግስታዊ መገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች ኩብለላ ላለፉት ሀያ አመታት ጋብ ብሎ የነበረ ቢሆንም በዚህ ሰሞን አራት የፋና ብሮድካስትና የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ጋዜጠኞች ከሀገር ወጥተው አልተመለሱም።  

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ሀያ ለሚጠጉ አመታት በተለያዩ ደረጃዎች ያገለገለው ሰለሞን አለሙ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በአሜሪካ የጥገኝነት ጥያቄ ማቅረቡን ሰምተናል። ሰለሞን አለሙ ከጥቂት ወራት በፊት ፋና ለስራ አሜሪካ ልኮት ነበረ ።በመሀል ተመልሶ የነበረ ቢሆንም እንደገና ፈቃድ ጠይቆ በቀረው የቪዛ ጊዜ ወደ አሜሪካ በመጓዝ በዚያው የጥገኝነት ጥያቄን አቅርቧል። ሰለሞን አለሙ ፋናን ከሪፖርተርነት አንስቶ እስከ ዘርፍ ዳይሬክተርነት ያገለገለ አርታኢ የነበረ እና ; ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የቴሌቪዥን ስርጭትን ከጀመረ አንስቶ የቴሌቪዥን ዜና ዘርፍን በሀላፊነት የመራ  ነው።

የፋና ዲጂታል ሚድያን በሀላፊነት ሲመራ የነበረው መቆያ ሀይለማርያምም በእንግሊዝ ሀገር ጥገኝነት መጠየቁ ተሰምቷል።መቆያ ሀይለማርያምም በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከ15 አመታት በላይ የሰራ እና ከታችኛው እርከን ጀምሮ እስከ ዲጂታል ዘርፍ ዳይሬክተርነት ያገለገለ ነው።

መቆያ ሀይለማርያም ከዚህ ቀደም በእንግሊዝ ሀገር የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቱን የተከታተለ ሲሆን ከዚያ መልስም ለአመታት ተቋሙን ሲያገለግል ነበር። ሆኖም ከጥቂት ሳምንታት በፊት ወደ እንግሊዝ ተመልሶ ጥገኝነት መጠየቁ ተሰምቷል። 

ተስፋዬ ከበደ በፋና ቴሌቪዥን ውስጥ በአርታኢነት ሲያገለግል የነበረ ጋዜጠኛም እንዲሁ በቅርቡ ለስልጠና በሚል ተቋሙ በሚያውቀው መልኩ ወደ አሜሪካ ሄዶ እንዳልተመለሰ መረዳት ችለናል።

በቅርቡ ፕሬዝዳንት ሰሀለወርቅ ዘውዴ የተገኙበትን በአሜሪካ የተደረገ ከግብርና ጋር የተያያዘ ጉባኤን ልትዘግብ አብራ የተጓዘችው የኢቢሲ ጋዜጠኛ መቅደስ ጥላሁን  በአሜሪካ ከአየር ማረፊያ ተሰውራ ካብልላለች።

ዋዜማ ያነጋገረቻቸው የሁለቱ ጋዜጠኞች የቅርብ ወዳጆች እንደነገሩን ጋዜጠኞቹን ወደ ስደት እንዲያመሩ ያስገደዳቸው በሰራ ቦታቸው ያለ አድሏዊ አሰራርና የተካረረ የብሄር ፖለቲካ ሲሆን በመጠኑም ቢሆን ወደ ውጪ ሀገራት ለመጓዘ ያገኙትን ዕድል ላለማሳለፍ በማሰብ እንደሆነ ነግረውናል። የተሰደዱትን ጋዜጠኞች አስተያየት ለማካተት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።  [ዋዜማ]