ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፈው ሳምንት የአመራሮች ምደባን አካሂዷል። የአዲሱ የአመራር ምደባ የባንኩን ደካማ አፈጻጸም ያስተካክላሉ ተብለው ከጥቂት ወራት በፊት ወደ ባንኩ ፕሬዝዳንትነት የመጡት አቶ አቢ ሳኖ ሀላፊ ከሆኑ በሁዋላ የተፈጸመ የመጀመርያው ምደባ ነው።
አቶ አቢ ሳኖ እንደ አዲስ የንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት ከመሆናቸው ከአመታት በፊትም ባንኩን በፕሬዝዳንትነት ማገልገላቸው የሚታወስ ሲሆን ፣ የኦሮምያ ኢንተርናሽናል ባንክን ከመሩ በሁዋላ ነው አቶ ባጫ ጊናን ተክተው ወደ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንትነት የተመለሱት።
ባለፈው ሳምንት የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ተክለወልድ አጥናፉም ባጸደቁት መልኩ አዲሱ ምደባ ተግባራዊ ሆኗል። የምክትል ፕሬዝዳንቶቹ ምደባ ሲካሄድም ከዚህ ቀደም 24 የነበሩትን የባንኩን ምክትል ፕሬዝዳንቶች ቁጥር ወደ 18 ዝቅ በማድረግና በፕሬዝዳንቱ እና በምክትል ፕሬዝዳንቶች መካከል የነበረ የቺፍ ኦፊሰር አደረጃጀት እንዲቀር በማድረግ ነው።
በብዙዎች ዘንድ የአቶ ባጫ ጊናን መነሳት ተከትሎ የሚኖረው አዲስ ምደባ እሳቸው ያመጧቸውና ባንኩን ለችግር የዳረጉት የማኔጅመንት አባላት ላይ ሰፊ ለውጥ ይደረጋል ተብሎ ቢጠበቅም የተደረገ ለውጥ አለመኖሩን ሰምተናል። በአቶ ባጫ የንግድ ባንክ ፕሬዝዳንትነት የነበሩ ምክትል ፕሬዝዳንቶች ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ አሁንም እንዲቀጥሉ ተደርጓል። የአቶ ባጫ አመዳደብ ከችሎታ ይልቅ ማንነት ላይ ያተኮረ እንደነበር መነሳቱ ባንኩን ለችግር እንደዳረገው ሲነሳ ቆይቷል።
ዋዜማ ሬድዮ ባገኘችው መረጃ መሰረትም በአቶ ባጫ ፕሬዝዳንትነት ከኦሮምያ ህብረት ስራ ባንክና አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ ተሹመው የንግድ ባንክ ምክትል ፕሬዝዳንትና ከፍተኛ ሀላፊ የሆኑት ማክዳ ኡመር ፣ ኑሪ ሁሴን የወለድ ነጻ ባንክ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ፣ ደረጄ ፉፋ የደቡብ ምእራብ ሪጅን ም/ ፕሬዝዳንት፣ ሳሙኤል ተስፋሁነኝ የሰሜን ምስራቅ ሪጅን ም/ፕሬዝዳንት፣ ሱሪ ፈቀታ የህግ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት እና አሊ አህመድ የስትራቴጂ ፕላን ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው እንዲቀጥሉ ተደርገዋል።
የምክትል ፕሬዝዳንቶቹ ቁጥር ከ24 ወደ 18 ዝቅ በማለቱ ምክንያት ስድስት አመራሮች እስካሁን ምደባ አላገኙም። በሌላ በኩል አቶ ባጫ ወደ ፕሬዝዳንትነት ከመምጣታቸው በፊት ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩት ፍቅረስላሴ ዘውዱ ፣ ኤፍሬም መኩሪያ ፣ዮናስ ልደቱ ፣ጥሩብርሀን ሀይሉ ፣ ይስሀቅ መንገሻ ፣ ዳዊት ቀኖ ፣ ኪዳኔ መንገሻ እና ዮሀንስ ሚሊዮን አሁንም በተለያዩ ዘርፎች ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው እንዲቀጥሉ ተመድበዋል።
ይህ መሆኑ በባንኩ ውስጥ ስር ነቀል ለውጥ አለመካሄዱን የሚጠቁም ነው ሲሉ የባንኩ ምንጫችን ነግረውናል። ምናልባትም ጠንካራ የአመራሮች የአፈጻጸም ግምገማ ኖሮ ቢሆን ምክትል ፕሬዝዳንቶቹ ባሉበት የሚቀጥሉበት ሁኔታ ላይኖር ይችል ነበር የሚል ግምት እንዳላቸው የባንክ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
ሌላ የባንኩ ምንጫችን እንደነገረን አሁን ያሉት አመራሮች እንዲቀጥሉ የተደረጉት አቶ በቃሉ ዘለቀ ከባንኩ ፕሬዝዳንትነት ከተነሱ በሁዋላ የአቢሲኒያ ባንክ ፕሬዝዳንትነትን ሲይዙ የወሰዷቸው በርካታ የንግድ ባንክ የቀድሞ አመራሮችና ወደ ሌላ ባንኮች ያመሩ ግለሰቦች እንዲመለሱ ጥሪ ተደርጎላቸው ፍቃደኛ ስላልሆኑም ነውም ብለውናል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተለይ በዚህ አመት አይቶት በማያውቀው ሁኔታ ያቀደውን ቁጠባና እና ትርፍ ማሳካት አቅቶት ተቸግሮ ታይቷል ።የሰጠው ብድርና ወጭ ከፍተኛ ስለነበረም ያገኘው ትርፍ ባቀደው ልክ አይደለም።
በ2012 አ.ም የታቀደው ተቀማጭ ብር 100 ቢሊየን ብር ሲሆን የተሳካው 54 ቢሊየን ብር ነው።ይህ ካለፉት ሁለት አመታት አንጻር ዝቅተኛ ነው።የ2011 አ.ም ተቀማጭ ገንዘብ 89 ቢሊየን ብር ነበር።የ2010 አ.ም ደግሞ 87 ቢሊየን ብር ነበር።በተቀማጭ ገንዘብ ከሁለቱም አመታት አንጻር በጣም ቀንሷል። የ2012 አ.ም ትርፍ 14 ቢሊየን ብር ነው።ይህ ከእቅዱ አንጻር 36 በመቶ የቀነሰ ነው።ከ2011 አ.ም አንጻር ደግሞ 10.3 በመቶ ቀንሷል።በ2012 አ.ም 42.5 ቢሊየን ብር ወጭ አደርጋለሁ ቢልም ወጪው ግን 55 ቢሊየን ብር ሆኗል።ይህም 64.3 ቢሊየን ብር ገቢ ለማግኘት አስቦ 69 ቢሊየን ገቢ ቢያገኝም ወጪው ስለናረ ብዙም ውጤታማ አላደረገውም። [ዋዜማ ራዲዮ]