በዚህ ሠነድ ውስጥ የሀገር ደኅንነት፣ የውስጥ ግጭቶች አፈታት፣ የቀጠናዊ ጦርነት ሥጋቶች፣ የጸጥታና የመከላከያ ተቋማት ገለልተኝነት እንዲሁም የኢኮኖሚ እና ሌሎች መጠነ-ሰፊ ሀገራዊ ጉዳዮች በዝርዝር ተካትተዋል፡፡ ሠነዱ የጸጥታ ኃይሎች አካሄድ፣ የጦርነት መንስኤዎችና የሰላማዊ ሽግግር መርሆችን በተመለከተ ማስጠንቀቂያዎችንም አስፍሯል።

ዋዜማ-የፌደራል መንግሥት ከነሐሴ ወር 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለሚኒስትሮች፤ ለመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ ለጋዜጠኞችና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት ‹‹Medemer Grand Strategy: 2025 – 2050›› የሚል ስያሜ በተሰጠውና በእንግሊዝኛ ቋንቋ በተዘጋጀ ሠነድ ዙሪያ ተከታታይ ስልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል። 115 ገጾች ያሉት ይህ ሰነድ፤ የ25 ዓመታት የመንግስት የሥራ አቅጣጫዎችን እና መዳረሻ ግቦችን የሚያመላክት መሆኑን ዋዜማ ተመልክታለች።

በዚህ ሠነድ ውስጥ የሀገር ደኅንነት፣ የውስጥ ግጭቶች አፈታት፣ የቀጠናዊ ጦርነት ሥጋቶች፣ የጸጥታና የመከላከያ ተቋማት ገለልተኝነት እንዲሁም የኢኮኖሚ እና ሌሎች መጠነ-ሰፊ ሀገራዊ ጉዳዮች በዝርዝር ተካትተዋል፡፡ ሠነዱ የጸጥታ ኃይሎች አካሄድ፣ የጦርነት መንስኤዎችና የሰላማዊ ሽግግር መርሆችን በተመለከተ ማስጠንቀቂያዎችንም አስፍሯል።

ዋዜማ የተመለከተችው ባለ 115 ገጽ የስትራቴጂ ሠነድ፤ የሀገር አቅምን ከሚወክሉ አሥራ ሁለት የኃይል መስመሮች መካከል አንዱ የሆነውን የጸጥታ ኃይል በሚመለከት ማስጠንቀቂያ የሚያስቀምጥ ሲሆን፤ የደህንነትና የጸጥታ ተቋማት ሕጋዊ ሥርዓትን፣ ድንበርንና ዜጎችን ከመጠበቅ ይልቅ በፖለቲካ ሲከፋፈሉ ወይም በሕግ የበላይነት ሥር ሳይገዙ ሲቀሩ «ጠባቂው ስጋት ይሆናል» ሲል ያገልጻል።  

ከዚህ ጋር ተያይዞ «ደኅንነት ሕጋዊነትና የሕዝብ ተቀባይነት ሳይኖረው ለዘለቄታው ሊቆም አይችልም» የሚል መርህ በሰነዱ ተቀምጧል። በኃይል ብቻ የሚጠበቅ ጸጥታ ጊዜያዊ እንጂ ዘላቂ ሰላም እንደማያመጣ በመጥቀስ፤ የሕግ የበላይነት፣ የፍትሕ ተቋማት ገለልተኝነትና የዜጎች እምነት አብረው ካልተገነቡ አገር ወደ ተደጋጋሚ ቀውስ እንደምትገባ ያመለክታል። በስትራቴጂው መሠረት እስከ 2030 ድረስ ደኅንነታቸው የተጠበቀ መሆኑን የሚያምኑ ዜጎች 60 በመቶ እንዲደርሱና በፖለቲካ ሕጋዊነት መለኪያ ከ65 በመቶ በላይ ለማስመዝገብ ግብ መያዙ ተጠቅሷል፡፡

የሠነዱ አጠቃላይ ይዘት

ሰነዱ በዋናነት በአምስት ምዕራፎች የተከፋፈለ ነው። እነዚህ ምዕራፎች ‹‹Architecture›› ወይም ‹‹መዋቅር›› በሚል ስያሜ የተገለጹ ሲሆን፤ የግብዓት መዋቅር፣ የመለወጥ መዋቅር፣ የውጤት መዋቅር፣ የአፈጻጸምና ግብረ መልስ መዋቅር እንዲሁም የድንበር መዋቅር በሚል ተቀምጠዋል። በእነዚህ ምዕራፎች “ኢትዮጵያ ምን አላት?” ከሚለው ጥያቄ አንስቶ፤ ከሌሎች ሀገራት ጋር ሊኖራት እስከሚገባ ሁለንተናዊ ድንበር ድረስ በ25 ዓመታት ይከናወናሉ የተባሉ ተግባራት ተካተውባቸዋል።

ኢትዮጵያ በሕዝብ፣ በመሬት፣ በውሃ፣ በኃይልና በአቀማመጥ የበለጸገች ስለመሆኗ የሚጠቁመው ሰነዱ፤ እምቅ አቅም ቢኖራትም ይህንን እምቅ አቅም አደራጅቶና አቀናጅቶ መጠቀም አለመቻሉን ያነሳል። ሰነዱ አቅምን ለመገንባት የተለያዩ ዘዴዎችን የሚጠቁም ሲሆን፤ 15 ሞዴሎች፣ 12 የኃይል ቬክተሮች፣ 9 የአሠራር ሥነ-ምግባሮች እንዳሉት ተመላክቷል።

እነዚህ አቅም የመገንባት ዘዴዎችን በመተግበር በሦስት ምዕራፎች የተከፋፈለ ውጤት ለማምጣት መታቀዱንም ሰነዱ ይጠቁማል። ‹‹መሰረት ማስያዝ›› የሚል ስያሜ የተሰጠውና በአውሮፓዊያኑ ከ2025 እስከ 2030 ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀው ውጤት የመጀመሪያው ምዕራፍ ነው። ሥርዓቶች እርስ በእርስ እንዲተባበሩ ይደረግበታል የተባለውና ከ2031 እስከ 2040 የሚዘልቀው ሁለተኛው ምዕራፍ፣ ‹‹አቅምን ዘላቂ ማድረግ›› የሚል ስያሜ ያለውና ከ2041 እስከ 2050 የሚዘልቀው ምዕራፍ ደግሞ ሦስተኛና የመጨረሻ መሆኑ ሰፍሯል።

ሰነዱ ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር ባላት ግንኙነት ለአንድ ጎራ ዘላቂ ታማኝነትን እንደማትሰጥ አስምሮበታል። ይልቁንም ተለዋዋጭ አጋርነትን በመደገፍ፤ በወሳኝ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ የመወሰን ስልጣንን ማረጋገጥ እንደሚገባ ይጠቁማል።

ከትላልቅ ዓለም አቀፍ ኃይሎች፣ ጥምረቶችና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በጥቅም ላይ ተመሥርቶ አብሮ መሥራት እንደሚገባ የተመላከተ ቢሆንም፤ ወገንተኝነት ወይም አንድ አጋር መዋቅራዊ ተጽዕኖ እንዲያገኝ ማድረግ የማይፈቀድ መሆኑን አስፍሯል።

የእርስ በርስ ጦርነትን ማስቀረት

ሠነዱ የኢትዮጵያን ታሪካዊ የሥልጣን ሽግግር ቀውሶች በመጥቀስ፤ ሥልጣን በኃይልና በጦርነት የሚያዝበትን ባህል መቀየር ዋነኛ ግቡ መሆኑን ይገልጻል። በተቋማትና በሥልጣን ሽግግር ስጋቶች ክፍል ውስጥ የአመራር መቋረጥ፣ የሥልጣንና ሽኩቻ፣ የተቋማዊ ትውስታ (የቀድሞ ማንነት) መጥፋት፣ የተቋማት መጠለፍ እና ደካማ የሥልጣን ርክክብ ሀገርን ወደ ቀውስ የሚመሩ ዋነኛ ስጋቶች ናቸው በማለት ዘርዝሯል። ይህንን ለመቅረፍም እስከ 2050 ድረስ ሰላማዊና ተቋማዊ ቀጣይነት ያለው የፖለቲካ ሽግግር እንዲኖር ማድረግ የጦርነትና አዙሪትን ለመስበር የመጨረሻው መዳረሻ ተደርጎ ተቀምጧል።

እርቅ

ሠነዱ የውስጥ ግጭቶችንና ጦርነቶችን በወታደራዊ መንገድ ብቻ ሳይሆን በፖለቲካዊ መግባባት፣ በውይይትና በተቋማዊ እርቅ መፍታት እንደሚገባ ያስቀምጣል። ለዚህም በሰነዱ የአፈጻጸም ኢላማዎች ውስጥ እስከ 2028 ድረስ ተቋማዊ የእርቅ ሥርዓት ተግባራዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ግብ ተቀምጧል።

በተጨማሪም «ፍትሐዊ የአቅም ግንባታ» በሚለው የአሠራር መርህ ሥር በግጭት የተጎዱ አካባቢዎች፣ ገጠራማ፣ አርብቶ አደርና ጠረፋማ አካባቢዎች ልዩ ትኩረት ካላገኙ የግጭት አዙሪት እንደማይቆም ተጠቅሷል፡፡ የሀገር ልማትና አቅም ግንባታ በተወሰኑ አካባቢዎች ላይ ብቻ የተከማቸ መሆኑን ጠቅሶ፤ ይህም ያልተሟላ ሥርአትን እንደሚፈጥር አመልክቷል፡፡

የባህር በር እና የውክልና ጦርነት

በስትራቴጂ ሠነዱ የውጭ ግንኙነትና በድንበር አስተዳደር ክፍል፣ ሰነዱ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና የውጭ ኃይሎች የውክልና ጦርነት መድረክ እንዳይሆን መከላከል የኢትዮጵያ ቀዳሚ ስትራቴጂካዊ ጉዳይ መሆኑን ያትታል። ጎረቤት አገራት ሲታመሱ ወይም ውጫዊ ኃይሎች ቀጣናውን ለፍልሚያ ሲጠቀሙበት ኢትዮጵያ ቀጥተኛ ተጎጂ እንደምትሆን በመጥቀስ፣ በዲፕሎማሲ፣ በጋራ ደኅንነት ትብብር፣ በንግድና በመሠረተ ልማት ትስስር ቀጣናዊ መረጋጋትን መፍጠር ወሳኝ መሆኑን ይገልጻል።

ከላይ በተጠቀሱት ትብብሮች መሠረት አስተማማኝ የባሕርና የኮሪደር መዳረሻ ማበጀት እንደሚገባ በመጥቀስ፤ እነዚህ መዳረሻዎች በአንድ መስመር ተጋላጭነት ላይ እንዳይመሰረቱ በርካታ አዋጭ መንገዶችን መለየት እንደሚገባም ተሰምሮበታል። ይሁንና ሰነዱ ከባሕር በርና ከሌሎች ሀገራት ግንኙነት ጋር የተገናኙ ጉዳዮችን በመርህ ደረጃ ከመግለጽ ባለፈ፤ በጉዳዩ ዙሪያ ከሀገራት ጋር ስለሚደረግ ድርድርና ቀነ ገደብ ያስቀመጠው ነገር የለም።

ከአባይ ወንዝ ጋር በተገናኘው ቀጣናዊ ጉዳይም፤ ሉዓላዊ የልማት ጥቅምን ማረጋገጥና መብቶችን ማስጠበቅ ከሚሉ የመርህ አገላለጾች  በተረፈ ከግድቡ ጋር በተያያዘ ስለሚደረጉ ድርድሮች ያስቀመጠው የተለየ አቅጣጫ የለም።

የስትራቴጂ ሠነዱ የወደፊት ግጭትና ፉክክር በባህላዊ የጦር ሜዳ ብቻ ሳይሆን በቴክኖሎጂ፣ በሳይበር ደኅንነት፣ በመረጃ ቁጥጥርና በሠው ሰራሽ አስተውሎት መስክ እየተካሄደ መሆኑን ያስገነዝባል። አንዲት ሀገር ወሳኝ የደኅንነትና የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማቶቿን በውጭ አካላት ቁጥጥር ሥር ካደረገች በቀውስ ወቅት ሉዓላዊነቷ አደጋ ላይ እንደሚወድቅ በመጥቀስ፤ ራስን የመከላከልና የቴክኖሎጂ አቅም መገንባት የህልውና ጉዳይ መሆኑን ያስረዳል። ለዚህም በ2040 በሳይበር ደኅንነት ዝግጁነት ከአፍሪካ አምስት ቀዳሚ አገራት መካከል የመሆን ግብ ተቀምጧል።

በተቃራኒው ሊዞሩ ይችላሉ የተባሉት አቅሞች  

ሰነዱ የአገር አቅምን ይወክላሉ ያላቸውን 12 የኃይል መስመሮች ሲተነትን፤ ጥንካሬዎች በአግባቡ ካልተመሩ ወይም በአንድ ወገን ከተጠለፉ ሀገርን የሚያናጉ ሥጋቶች እንደሚሆኑ ያትታል። ለአነዚህ መካከል አንዱ የሆነው የደኅንነት ኃይል ከፖለቲካ ወይም ከሕግ ውጭ ሲሆን ዜጎችን ከመጠበቅ ይልቅ «ጠባቂው ስጋት ይሆናል» በሚል ገልጾታል። በተመሳሳይ የዲጂታልና የሠው ሰራሽ አስተውሎት ሥርዓቶች በውጭ መሠረተ ልማትና መረጃ ላይ ብቻ ከተመሠረቱ የአእምሮ ጥገኝነት ሊፈጥሩ እንደሚችሉ እንዲሁም ዳያስፖራው ማህበረሰብ በአግባቡ ካልታቀፈና ከተገለለ አቅም ከመፍጠር ይልቅ ወደ ውጭ የተላከ ‹‹ቅሬታ›› ሊሆን እንደሚችል ሰነዱ ያስጠነቅቃል።

የ2030 እስከ 2050 ዋነኛ ግቦች

ሠነዱ በአምስት ስትራቴጂክ ዘርፎች በቁጥር ሊደረስባቸው ይገባል ያላቸውን ግቦች አስቀምጧል። ይሁንና እነዚህ አኃዞች በዝርዝር የድርጊት መርሐ ግብሮችና በአፈጻጸም ማዕቀፍ ተረጋግጠው የሚሻሻሉ የስትራቴጂክ ዕቅድ መለኪያዎች መሆናቸውን ሠነዱ በግልጽ አመላክቷል።

ኢኮኖሚና ምርት ፡-  ሰነዱ እስከ 2040 ድረስ ዓመታዊ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ዕድገት ከስምንት በመቶ በላይ እንዲሆን ግብ አስቀምጧል። ከ2040 እስከ 2050 ባሉት ዓመታት ደግሞ ዕድገቱ ከሰባት በመቶ በላይ ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ ሌላኛው ግብ ሆኖ ተጠቅሷል።

‹‹የከፋ ድህነት›› ውስጥ የሚገኙ ዜጎች በ2030 ከ15 በመቶ በታች፣ በ2040 ከ10 በመቶ በታች፣ በ2050 ከ5 በመቶ በታች እንዲሆኑ ማድረግ ሌላኛው ግብ ቢሆንም፤ የከፋ ድህነት በሚል የተገለጸው የድህነት ሁኔታ ግን መለኪያዎች አልተቀመጡለትም።

ከ18 እስከ 30 ዓመት ድረስ የሚገኙ ወጣቶችን ሥራ አጥነት አስመልክቶም፤ በ2030 ከ15 በመቶ በታች፣ በ2050 ደግሞ ከስምንት በመቶ በታች ማድረግ እንደሚገባ ሰነዱ አስቀምጧል።

በ2040 የማምረቻና የግብርና ኢንዱስትሪዎች ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ የ15 በመቶ ድርሻ ሊኖራቸው እንደሚገባ፤ በ2050 የ5 ሚሊዮን ሔክታር የመስኖ እርሻ እንዲለማ ማስቻልም ተጨማሪ ግቦች ሆነው ተገልጸዋል።

የመንግሥት ገቢና ዲጂታል አገልግሎት፡  ታክስ ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አንጻር ያለውን ምጣኔ በ2031 ከ12 በመቶ በላይ፣ በ2040 ከ15 በመቶ በላይ፣ በ2050 ደግሞ ከ20 በመቶ በላይ ማድረስ ተቀምጧል። በዲጂታል የሚሰጡ የመንግሥት አገልግሎቶችን በ2040 ወደ 95 በመቶ ማሳደግ፣ የ«ፋይዳ» ዲጂታል መታወቂያን በ2032 ከዋና ዋና የሕዝብ አገልግሎቶች ጋር ማቀናጀት፣ በምርምርና ፈጠራ በ2045 ከሦስቱ ቀዳሚ የአፍሪካ አገራት መሠለፍ እንዲሁም በሳይበር ደኅንነት ዝግጁነት በ2040 ከአፍሪካ አምስት ቀዳሚ አገራት መካከል መግባት ተካተዋል።

መረጋጋትና ሕጋዊነት፦ በፖለቲካ ሕጋዊነት መለኪያ በ2030 ከ65 በመቶ በላይ ለማስመዝገብ ግብ ቢቀመጥም የመለኪያው ዝርዝር አልተገለጸም። በተመሳሳይ ዓመት ደኅንነታቸው የተጠበቀ መሆኑን የሚያምኑ ዜጎች 60 በመቶ እንዲደርሱ፣ በ2028 የእርቅ ሥርዓት እንዲጠናቀቅና ዓመታዊ የኃይል ሽያጭ ገቢ ወደ 500 ሚሊዮን ዶላር እንዲያድግ ተመላክቷል።

ማኅበራዊ ግቦች፦ በ2030 50 በመቶ የሚሆኑ የአመራር ቦታዎች በሴቶች እንዲያዙና አገራዊ የሥርዓተ ትምህርት ማሻሻያ በ2030 ተግባራዊ ሆኖ እስከ 2050 እንዲቀጥል ዕቅድ ተይዟል።

ዘላቂነትና የረጅም ጊዜ ግቦች፦ በ2050 ሰላማዊና ተቋማዊ ቀጣይነት ያላቸው የፖለቲካ ሽግግሮች እንዲከናወኑ፣ የደን ሽፋን ከ30 በመቶ በላይ እንዲያድግና በአፍሪካ ከቀዳሚ ሦስት የዲፕሎማሲ አቅም ካላቸው ሀገራት ተርታ መሰለፍ የሚለው ተካትቷል።

እንዲቋቋሙ ምክረ ሐሳብ የቀረበባቸው ተቋማት

ሰነዱ በቀጣዮቹ ዓመታት እንዲቋቋሙ የሚያበረታታቸው ሁለት ተቋማትን ጠቅሷል። የመጀመሪያው «የመደመር ኢንስቲትዩት» ሲሆን፤ የስትራቴጂውን ተቋማዊ ትውስታ ለመጠበቅ፣ የረጅም ጊዜ ስትራቴጂክ ጥናትና ምርምር ለማካሄድና የስትራቴጂውን ቀጣይነት ለመደገፍ እንደሚሠራ ተገልጿል። ሁለተኛው ደግሞ «የኢትዮጵያ የአደራ ጠባቂነት አካዳሚ» ሲሆን «ከተቋቋመ» የሚል ቅድመ ሁኔታ ተቀምጦለታል። ተቋሙ ሲመሠረት መሪዎችን ማብቃት፣ የተቋማትን ጉድለትና ልምድ ማጥናት፣ የሕገ መንግሥት ፍልስፍና ጥናትና የተተኪ መሪዎች ሥልጠና መስጠት ኃላፊነቶቹ እንዲሆኑ ምክረ ሐሳብ ቀርቧል። [ዋዜማ]

የዋዜማን ዘገባዎች በሌላ ሚዲያ ለመጠቀም የዋዜማን ምንጭነት ይግለፁ፣ ዘገባውን ሳያዛቡ በማቅረብ ለተሻለ ጋዜጠኝነት ድጋፍዎን ያሳዩ።