የቅሬታ አቅራቢ ፓርቲዎች ተወካዮች- Photo Wazema

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት በቅርቡ የሰጠው መግለጫ “አይወክለንም” ያሉ አባል ድርጅቶች ምክር ቤቱ በአምስት ቀናት ይቅርታ ካልጠየቀ ሌላ ምክር ቤት እናቋቁማለን ሲሉ አስጠንቅቀዋል። ምክር ቤቱ በበኩሉ ክሱን አጣጥሎታል። ዝርዝሩን አንብቡት

ዋዜማ- የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ያወጣው መግለጫ በጠቅላላ ጉባኤ  ከስምምነት ላይ ያልደረስንባቸው ርእሰ ጉዳዬች የተነሱበትና በአመዛኙ በጉባኤው የተነሱ ሀሳቦችን ያላካተተ በመሆኑ ተቀባይነት የሌለውና የእኛ 32 ፓርቲዎች አቋም የማይገልጽ ነው ሲሉ ተቃውመዋል ።

የኢትዮጵያ የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በአምስት ቀናት ውስጥ ከምክር ቤቱ አባል ፓርቲዎች ፊት ቀርቦ “ይቅርታ የሚጠይቅ መግለጫ” ማውጣት ካልቻለ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አሳውቀው የ32 ፓለቲካ ፓርቲዎችን የሚወክል የጋራ የፓለቲካ ምክር ቤት እንደሚያቋቁሙ ተናግረዋል።

ተቃውሞ ካስነሱ ጉዳዬችና በኢትዬጵያ የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መግለጫ ከተጠቀሱት  መካከል”በሀይማኖት ጉዳዬች ላይ ምንም አይነት አቋም አንይዝም የሚልና ገና ከስምምነት ላይ ያልተደረሰበት ውሳኔ” ሆኖ ሳለ ነገር ግን በመግለጫው መነሳቱ የፓርቲዎቻችን አቋም አይወክልም የሚል ነው።

ሌላኛው በሸገር ከተማ “ህገ ወጥ” ናቸው በሚል የፈረሱት መስጊዶች በሚመለከት የፓለቲካ ምክር ቤቱ የሰጠው መግለጫ “ያልተወያየንበትና የሁሉም ፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ አቋም የሚወክል“ አለመሆኑ ተቃውሞአቸውን እየገለፁ የሚገኙ ፓርቲዎች   ጠቅሰዋል። 

“ጊዜያዊ ኮሚቴ” በሚል ውክልና አግኝተናል የሚሉትና  ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት ሶስት ፓርቲዎች የአገው ብሔራዊ ሸንጎ ፓርቲ፣ ህዳሴ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ናቸው።

በጊዚያዊ ኮሚቴው በኩል ተቃውሞ ካሰሙት ፓርቲዎች መካከል የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ)፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ፓርቲ ( ኢብፓ)፣ የገዳ ስርአት አራማጅ ፓርቲ፣ የአማራ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ( አዲፓ) እንዲሁም አረና ትግራይ መሆናቸውን ሰምተናል ።

የውዝግብ ምንጭ ሆነዋል የተባሉት ርእስ ጉዳዬች ዙርያ ዋዜማ የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጠይቃ እንደተረዳቺው ከሆነም በቁጥር ደረጃ 32 እንደሆኑ ተደርጎ የተገለፀው ትክክለኛ ቁጥር አለመሆኑ ነው።

የፓለቲካ ምክርቤቱ በወቅታዊ ጉዳዬች ዙርያ ያወጣው የአቋም መግለጫ እየተቃወሙ የሚገኙት የፓለቲካ ፓርቲዎች ከአስር ያልበለጡ መሆናቸውን የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ፀሀፊ የሆኑት ራሔል ባፌ ይናገራሉ ።

ራሔል እንደሚሉት  ፓርቲዎቹ ምክርቤቱ በሰጠው የአቋም መግለጫ ዙርያ ተቃውሞ ቢኖራቸው እንኳን አቤቱታቸውን ማቅረብ የሚችሉት ለጠቅላላ ጉባኤው መሆኑን ነግረውናል ።

“ፓርቲዎቹ የተሰማቸውን ቅሬታ እስካሁን ማቅረብ አልቻሉም። አሁን ላይ እየተሰማ ያለው ጫጫታ ለምክርቤቱም ሆነ አጠቃላይ ለፓለቲካ ምህዳሩ የሚበጅ ተግባር ባለመሆኑ የስምምነት ሰነዱ በሚፈቅደው መልኩ ጥያቄዎቻቸውን ቢያቀርቡ ይሻላል” ብለዋል ወሮ ራሔል።

ቅሬታ አቅራቢ ፓርቲዎቹ በበኩላቸው ጊዜያዊ ኮሚቴ በሚል ሌላ የፓለቲካ ምክርቤት ለማቋቋም እንቅስቃሴዎችን መጀመራቸው እየገለፁ ነው። በተባሉት ቀናቶች ውስጥ የፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ይቅርታ የሚጠይቅ መግለጫ መስጠት ካልቻለና ለአባል ፓርቲዎቹ በግንባር ቀርቦ ካላስተባበለ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አሳውቀው የራሳቸውን የጋራ የፓለቲካ ምክር ቤት እንደሚያቋቁሙ ተናግረዋል።  

ቅሬታ አቅራቢ ፓርቲዎቹ ካነሷቸው ተቃውሞዎች መካከልም የምክር ቤቱ ሰራ አስፈፃሚዎች የሚያራምዱት ራሳቸው የሚወክሏቸው የፓርቲዎች አቋም እንጂ በጠቅላላ ጉባኤ የተነሱና አቋም የተወሰዱባቸው ሀሳቦች አለመሆናቸው ጠቅሰው በዚህ መሠረትም የጋራ ምክር ቤቱ የሚተዳደርበት “መርህ” ተጥሷል ባይ ናቸው።

ዋዜማ ከፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ያሰባሰበችው መረጃ እንደሚያመላክተው ምክርቤቱ  ከጠቅላላ ጉባኤው በተሰጠው ስልጣን መሠረት በወቅታዊ ጉዳዬች ዙርያ የአቋም መግለጫ ማውጣት ለስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የተሰጠ ስልጣን ነው። 

በመግለጫው የተጠቀሱት ሀሳቦችንም በተመለከተ የፓለቲካ ፓርቲዎቹ በጠቅላላ ጉባኤ የተሰማሙበት መሆኑን ፀሀፊዋ ራሔል ባፌ ተናግረዋል።

ፀሀፊዋ ራሔል እንደሚሉት ” በምክርቤቱ የውስጥ አሰራር መሠረት ጠቅላላ ጉባኤ  አብላጫ ጥቁር ያላቸው አባል ፓርቲዎች ተስማምተውበታል ማለት የምክር ቤቱ አቋም ሁኖ የሚፀና ነው”

በዚሁ መሠረት ምክር ቤቱ የአቋም መግለጫ ማውጣት የቆየ አሰራር መሆኑን ራሔል ገልፀውልናል ።

ግንቦት 24 ቀን 2015 ዓ.ም በተደረገው የአባል ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ ከቀረቡት አጀንዳዎች አንዱና ሰፊ ውይይት የተደረገው በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች በተለይም “የሰላምና ፀጥታ” የተመለከተ ነው የሚሉት ተቃውሟቸው እያሰሙ የሚገኙት የፓለቲካ ፓርቲዎች ናቸው። ሆኖም ከስምምነት ላይ ሳይደረስበትና ሳንስማማበት የአቋም መግለጫ መሰጠት አልነበረበትም እያሉ ይገኛሉ።

በዚሁ እለት በነበረው ጉባኤ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተወካዮች በታዛቢነት ተገኝተው ነበር።  

“የትኞውም የፓለቲካ ፓርቲ ያለውን ቅሬታ በቀጥታ ለምክርቤቱ በፅሁፍም አልያም በግንባር ቀርቦ ቅሬታውን ማቅረብ ይችላል እንጂ ማንም ባሻው ጊዜ እየነሳ ምክርቤት ማቋቋም የሚችልበት አካሄድ የለም” ሲሉ ራሔል ባፌ ነግረውናል። [ዋዜማ]