ዋዜማ – ከጥቂት ወራት ወዲህ ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት ውስጥ የገቡት የግል ባንኮች ቁጠባቸውን ለማሳደግና በቂ መንቀሳቀሻ ገንዘብ ለማግኘት ከፍተኛ ገንዘብን በጊዜ ገደብ ቁጠባ (Fixed time deposite) ሊያስቀምጡ ለሚችሉ ደንበኞች ከፍተኛ የተባለ ወለድን እያቀረቡ መሆኑን ዋዜማ ካሰባሰበችው መረጃ ተረድታለች።

የጊዜ ገደብ ቁጠባ ወይንም (fixed time deposite) የሚባለው በተለምዶ የባንክ ደንበኞች ከሶስት ወርና ከዚያም በላይ ገንዘባቸውን ላለማንቀሳቀስ ተስማምተው፣ ለዚህ ስምምነታቸው ደግሞ ከባንኮች ከፍተኛ የሆነ ወለድን እንዲያገኙ የሚደረግበት አሰራር ነው። 

እንዲህ አይነት የገንዘብ ቁጠባ ውስጥ የሚሳተፉት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብን ማስቀመጥ የሚችሉ ግለሰቦች ናቸው። ከዚህ በፊት በዚህ መልኩ ለሚቆጥቡ ደንበኞች ባንኮች ከ12 በመቶ አንስቶ ከፍ ካለም የሚቆጥቡት የገንዘብ መጠን ከፍተኛነት ታይቶ እስከ 14 በመቶ ድረስ ወለድ ይታሰብላቸው ነበር። አሁን ግን በጊዜ ገደብ ቁጠባ ገንዘብን ለሚያስቀመጡ ደንበኞች ከ16 በመቶ ጀምሮ እስከ 18.5 በመቶ ድረስ ወለድ መክፈል ጀምረዋል።

ዋዜማ ባሰባሰበችው መረጃ አምስት የሚደርሱ የግል  ባንኮች በከፍተኛ ወለድ ቁጠባን መሰብሰብ ውስጥ ገብተዋል። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ለገንዘብ አስቀማጮች ያወጣው ዝቅተኛ የወለድ ምጣኔ ሰባት በመቶ ነው።

ከዚህ አንጻር በ18 በመቶ የተሰበሰበ ቁጠባ ለብድር የሚቀርብ ከሆነ አሁን ባለው የዋጋ ንረት ላይ ተጨማሪ የኢኮኖሚ ችግር እንሚፈጥር የፋይናንስ ባለሙያዎች ነግረውናል። ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአንድ የግል ባንክ የስራ ሀላፊ እንደሚሉት ከሆነ ፣ ባንኮች አሁን ላይ በከፍተኛ ወለድ ለመሰብሰብ የተገደዱትን ገንዘብ ለማበደር ብቻ ሳይሆን ያደሩ ግዴታዎቻቸውን ሳይቀር ሊፈጽሙበት ነው። 

የተፈጠረው የገንዘብ እጥረት ከአንዱ ግል ባንክ ወደ ሌላ ግል ባንክ ገንዘብን መላክን አስቸጋሪ አድርጎታል። ከአንድ ባንክ ወደ ሌላ ባንክ እንዲዘዋወር ትእዛዝ የተሰጠበት ገንዘብ ዝውውሩን ለመፈጸም ሳምንታት እየወሰደ ነው። ከአንዱ ባንክ ወደ ሌላ ባንክ የሚደረግ የገንዘብ ዝውውር በብሄራዊ ባንክ በኩል የሚፈጸም እንደመሆኑ ባንኮች ይህን ተግባር የሚፈጽሙት ብሄራዊ ባንክ ባላቸው ሂሳብ (settlement account) አማካይነት ነው። 

ሆኖም አንዳንድ ባንኮች የባንክ ለባንክ የገንዘብ ዝውውራቸውን ለመፈጸም የሚያስችል ገንዘብን በዚህ ሂሳባቸው ውስጥ ማስቀመጥ የማይችሉበት ደረጃ መድረሳቸው የችግሩ ማሳያ መሆኑን የባንክ የስራ ሀላፊው ነግረውናል። 

ይፋ ባልሆነ መንገድ የባንክ ለባንክ ገንዘብ መላላክ የቀረውም በዚህ ሳቢያ ነው። ይህም ብቻ ሳይሆን በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ያሉ የክፍያ ማሽኖች (ATM) ባዶ ሆነው በተደጋጋሚ የሚስተዋሉትም በዚህ ምክንያት መሆኑንም ገልጸውልናል። 

መጋቢት ወር ላይ የተፈቀዱ ብድሮችን በገንዘብ እጥረት ምክንያት ብዙ የግል ባንኮች እስካሁን አለመልቀቃቸውን ዋዜማ ከተለያዩ የባንክ ሀላፊዎች እና ብድር ተፈቅዶላቸው ነገር ግን ካልተለቀቀላቸው ባለሀብቶች ሰምታለች። 

ያነጋገርናቸው የባንክ ሀላፊም የጊዜ ገደብ ተቀማጭን ባንኮች እንደ አማራጭ የወሰዱትም አሁን የገቡበትን ወቅታዊ ችግር እንደመወጪያ እንጂ ዘላቂ መፍትሄ አይሆንም።

አሁን ከፍተኛ ገንዘብን በጊዜ ገደብ ለሚያስቀምጡ አስቀማጮች ይሰጣል እየተባለ ያለው 18.5 በመቶ አካባቢ ወለድ እስከ አሁን ድረስ ብድር የሚሰጥበት ከፍተኛው የወለድ ምጣኔ ነበር። የኢትዮጵያ ባንኮች በተለይም የግል ባንኮች ለረጅም ወራት ተመሳሳይ በሆነ የገንዘብ እጥረት መውደቃቸው ያልተለመደ ነው። 

ከጥቂት ወራት ወዲህ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብም ከባንኮቹ ሲወጣ እንዲሁም ሲዘዋወር ነበር። 

ይህንን በርካቶች ከወቅቱ የዋጋ ንረት ጋር በተያያዘ ንብረት ለመያዝ ከባድ ፍላጎት መኖሩን ገንዘቡ ለመውጣቱ እንደ አንድ ምክንያት የሚያቀርቡት አሉ። 

ብሄራዊ ባንክ ባንኮች በእንዲህ አይነት ተመሳሳይ የገንዘብ ችግር ውስጥ ሲወድቁ በገበያው ውስጥ ያለውን ወለድ በማወዳደር ያበድራቸው ነበር። ሆኖም ባንኮች ለወራት የገንዘብ ችግር ውስጥ ቢሆኑም ብሄራዊ ባንክ እስካሁን ብድር አላቀረበላቸውም። [ዋዜማ]