ዋዜማ- እንደ ነዳጅ ሁሉ የመንግስት ከፍተኛ ድጎማ ተደርጎበታል የተባለው ማዳበሪያ በህብረት ስራ ዩኒየኖች እና በገበሬ ማህበራት በኩል ለአርሶ አደሩ ከመድረስ ይልቅ ግልጽ ባልሆነ መንገድ በነጋዴዎች እጅ እንደተከማቸ ዋዜማ ከተለያዩ ምንጮች ተረድታለች።

በሀገር አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የአቅርቦት መስተጓጎል ለመኸር እርሻ የሚሆን ማዳበሪያ ከፍተኛ የሆነ እዕጥረት እንዲከሰት ምክንያት መሆኑን ተገንዝበናል። ለወትሮ አርሶ አደሮች ማዳበርያን በየወረዳዎቻቸው ባሉ የገበሬ ማህበራትና ዩኒየኖች በኩል በእኩል ዋጋ ነበር የሚቀርበው። በዚህ አመት ግን ባልተለመደ መልኩ ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ የሚከፋፈለባቸው ዩኒየኖች እና የገበሬ ማህበራት መጋዘኖች አንዳንዶቹ ባዶ ሲሆኑ አንዳንዶቹ ደግሞ እጅግ አነስተኛ ማዳበሪያ ብቻ እያቀረቡ ነው።

በኦሮምያ ክልል ስንዴ በስፋት ከሚመረትባቸው ዋነኛ በሆነው የአርሲ ዞን ለአብዛኛ ወረዳዎች ዳፕ የተሰኘው ማዳበርያ እንዳልደረሰም ዋዜማ ሰምታለች። ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ አንድ የሂጦሳ ወረዳ አርሶ አደር እንደነገረን ስንዴ ለሚመረትበት ለዚህ አካባቢ በተለምዶ ከሰኔ ወር በፊት ማዳበርያ ተጠቃሎ ለአርሶ አደሩ መድረስ ቢኖርበትም እርሱን ጨምሮ በርካታ አርሶአደሮች ከዩኒየኖችና ገበሬ ማህበራት ማዳበርያ እንዳልደረሳቸው ይናገራል። 

“በርካታ መጠን ያለው ማዳበርያ በግለሰብ ነጋዴዎች መጋዘኖች እንደሚገኝ ግን እኔም በአካል ተገኝቼ አረጋግጫለሁ” ብሎናል። 

“መንግስት ደጉሞታል የተባለ ማዳበሪያ የተለመዱ መጋዘኖች ውስጥ ሳይገኝ በሶስት አራት የጭነት መኪና የግለሰብ መጋዘን ውስጥ ግልጽ ባልሆነ መንገድ ወርዶ ተከማችቷል” ሲልም ነግሮናል። 

ማዳበሪያው በግለሰብ ነጋዴዎች እጅ መገኘቱ ብቻ ሳይሆን የመሸጫ ዋጋው በእጅጉ የተጋነነ መሆኑንም አርሶ አደሩ ይገልጻል። አንድ ኩንታል ከ6,500 ብር እስከ 7 ሺህ ብር ዋጋ በነጋዴዎች እንደተሸጠ መሆኑን ገልፆ “እኔም በኩንታል በ7 ሺህ ብር ዋጋ 10 ኩንታል ማዳበሪያ ገዝቻለሁ” ብሎናል።

የዋጋ ጭማሬው ባለፈው የምርት ዘመን የማዳበርያ ዋጋ ተወደደ ተብሎ ይሸጥበት ከነበረው ከ4500 እስከ 5 ሺህ ብርም ከፍተኛ ጭማሬን አሳይቷል። በአርሲ ዞን አብዛኛ ወረዳዎች ስንዴ የሚዘራው በሰኔ ወር የመጨረሻ ሳምንታት እንደመሆኑ የማዳበርያ አቅርቦት በዚህ የሚቀጥል ከሆነ የእርሻ መስተጓጎል ሊከሰት እንደሚችል ፣ እንዲሁም በውድ ዋጋ የሚቀርብበት ሁኔታ ከቀጠለም በስንዴ ላይ በዚህ አመት የታየው ከፍተኛ የገበያ መረበሽ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።

አስተያየታቸውን የሰጡን በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን የሀሙሲት አቅራቢያ አርሶ አደሮች ደግሞ ማዳበሪያን ከገበሬ ማህበራት እና ከዩኒየኖች ብቻም ሳይሆን ከነጋዴዎች ላይም ማግኘት ከባድ እንደሆነባቸው ነግረውናል። የማዳበሪያ ጉዳይ በተለይ በአማራ ክልል አርሶ አደሮችን ለተቃውሞ አደባባይ እንዳስወጣ ይታወሳል።

በሌላኛው የኦሮምያ ክልል ኢሉ አባቦራ መቱ አቅራቢያ ከአርሶ አደሮች የሰበሰብነው አስተያየት እንደሚጠቁመውም የማዳበርያ አቅርቦቱ ለአርሶ አደሩ ይደርስባቸዋል በተባሉ ነባር ተቋማት ውስጥ “የለም” በሚባል ደረጃ እንደሆነ፣ በተወሰኑ ነጋዴዎች በኩል በኩንታል ከ5 ሺህ ብር በላይ እንደሚሸጥ ነግረውናል። ከከፍተኛ የማዳበሪያ እጥረት ጋር በተያያዘ ከኦሮምያ እና አማራ ክልሎች ባለፈ ደቡብን ጨምሮ በብዙ የሀገሪቱ ክፍሎች ጥያቄዎች እየተነሱ ነው።

መንግስት በአለም አቀፍ ደረጃ ዋጋው የተወደደውን ማዳበሪያ ለመደጎም ብቻ ከ15  ቢሊየን ብር በላይ  ማውጣቱን ቢያስታውቅም ዕጥረቱ አጠቃላይ የሀገሪቱን ግብርና ምርታማነት አስቸጋሪ ቅርቃር ውስጥ ከቶታል። 

የግብርና ሚኒስቴር ከዚህ ጋር በተያያዘ ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሀን በሰጠው መግለጫ ለዚህ አመት የእርሻ ምርት የሚሆን በቂ ማዳበሪያ ግዥ መፈጸሙን ገልጿል።ታህሳስ ወር ላይ ከ12 ሚሊየን ኩንታል በላይ የማዳበርያ ግዥ እንደተፈጸመ ፣ ሀገር ውስጥ ተከማችቶ ከነበረው ጋር ተዳምሮ 15 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ለዚህ አመት የእርሻ ወቅት እንደተዘጋጀ ሚኒስቴሩ አሳውቋል።

ሚኒስትር ዲኤታዋ ሶፍያ ካሳ ባለፈው ሳምንታት በሰጡት መግለጫም ፣ መንግስት እጁ ላይ ካለው 8.4 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ 7.4 ሚሊየን ኩንታሉ ለመሰረታዊ የህብረት ስራ ማህበራት መከፋፈሉን ፣ ከዚህ ውስጥ ደግሞ 5.7 ሚሊየን ኩንታሉ ለአርሶ አደሩ መከፋፈሉን ተናግረዋል። 

እኚሁ ሚኒስትር ዲኤታ ከባለፈው ሳምንት በቀደመ ጊዜ እና ለመንግስት ቅርበት ባለቸው መገናኛ ብዙሀን ስለተፈጠረው የማዳበሪያ እጥረት ተጠይቀው ምላሽ ሲሰጡ : ከውጭ ምንዛሬ አከፋፈል ጋር ግዢ ከተፈጸመው ማዳበሪያ ውስጥ የተወሰነው ካለመግባቱ በስተቀር ለአመቱ የሚያስፈልገው ማዳበሪያ በመንግስት እንደሚቀርብ ፣ እንዲሁም ሀገር ውስጥ ያልገባው ማዳበሪያ እስከ ሰኔ ወር መጨረሻ እያንዳንዳቸው ከ600 ሺህ ኩንታል በላይ በሚጭኑ ሰባት መርከቦች ተጓጉዞ እንደሚገባ አንስተዋል።

ነገር ግን ክልሎች ያላሰራጩት ክምችት እጃቸው ላይ እንዳለ ፣ እንዲሁም በነጋዴዎች እጅ ማዳበሪያው ሊገባ ከቻለም ታች ያሉ የመንግስት መዋቅሮች ጋር ሊፈተሽ እንደሚገባ የሚጠቁም ምላሽ ሰጥተዋል።

በሩሲያና በዩክሬን ጦርነት ሳቢያ ዓለማቀፍ የማዳበሪያ አቅርቦት ከፍተኛ መስተጓጎልና የዋጋ ውድነት የገጠመው ሲሆን ችግሩ ከውጪ ምንዛሩ ዕጥረት ጋር ተያይዞ  ለበርካታ ድሀ ሀገሮች ፈታኝ ሆኗል። [ዋዜማ]