ዋዜማ- የግል ንግድ ባንኮች የገጠማቸው የጥሬ ገንዘብ እጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ቀጥሎ ለደንበኞቻቸው መክፈል የማይችሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ዋዜማ ያሰባሰበችው መረጃ ያመለክታል።
የጥሬ ገንዘብ ዕጥረቱን ተከትሎ፣ ባለሀብቶችና ነጋዴዎች ጥሬ ገንዘብ ወደ ባንክ ከማስገባት ይልቅ ሌሎች አማራጮችን ለመጠቀም እንደተገደዱ ነግረውናል
ያነጋገርናቸው ነጋደዎች እና ባለሀብቶች፣ ገንዘባቸውን ቀስ በቀስ ከባንክ እያወጡ በግል ካዝናና ስውር ቦታዎች ማስቀመጥ መምረጣቸውን ይናገራሉ። የባለሀብቶቹ ስጋት በባንክ የተቀመጠ ገንዘባቸውን በፈለጉት ፍጥነት ለማግኘት በመቸገራቸውና የተለያዩ ገደቦች ስለተጣለባቸው ነው።
አንዳንድ ባንኮች ባለፉት ወራት አልፎ አልፎ ለተመረጡ ደንበኞች ሲፈቅዱ የነበረውን ከባንክ ወደ ባንክ የገንዘብ ዝውውር (RTGS) አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ወደማቆም እየመጡ መሆናቸው የባንክ ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡
ዋዜማ ከነጋገረቻቸው የግል ንግድ ባንክ የሥራ ኃላፊዎች አንዱ “ዛሬ አንድ ሚሊየን ብር አስገብቶ ነገ ሲመጣ የሚፈልገውን ያክል ወጪ እንደማልሰጠው እያወቀ እንዴት ይመጣል?” ሲሉ የነጋዴዎች ጥሬ ገንዘብ መከዘን ገንዘባቸውን በፈለጉበት ጊዜ ማንቀሳቀስ አለመቻል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ዋዜማ ያጋገረቻቸው የተለያዩ ባንኮች የቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጆች፣ የሚመሩትን ቅርንጫፍ ከ50 ሺህ ብር ባነሰ አዳሪ ገንዘብ ዕለታዊ ሂሳባቸውን የሚዘጉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ጠቁመዋል፡፡
የባንክ ቀርንጫፎች ለደንበኞቻቸው የሚከፍሉት ገንዘብ ሲያጥራቸው ከዋና መስሪያ ቤት (ትሬዠሪ) ገንዘብ እንዲላክላቸው በስፋት ጥያቄ እያቀረቡ ቢሆንም፣ ዋና መስሪያ ቤት ቋት ላይ እጥረቱ ስለበረታ የጠየቁትን ያክል ማግኘት አንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡
በተለይ ለተርታ ለደንበኞቻቸው የሚፈቅዱት ዕለታዊ ወጭ አንዳንዶ ከ10 ሺሕ ብር ያልበለጠ ሲሆን፣ ከፍተኛ የደንበኞች ቅሬታ እያስተገዱ ነው፡፡ በብሔራዊ ባንክ ሕግ መሰረት አንድ የባንክ ደንበኛ በቀን እስከ 50 ሺሕ ብር ጥሬ ገንዘብ የማውጣት መብት አለው፡፡
ከተከሰተ ወራት ያስቆጠረው የጥሬ ገንዘብ እጥረት አሁን ላይ በተለይ የግል ባንኮችን በእጅጉ እየፈተነ መሆኑን ዋዜማ ከተለያዩ የባንክ ምንጮቿ ሰምታለች፡፡ ቀድም ሲል በተለይ አነስተኛ አቅም ካለቸው ባንኮች መካከል የሚመደቡት ላይ በርትቶ የነበረው የጥሬ ገንዘብ እጥረት፣ አሁን ላይ አንጋፋ የግል ንግድ ባንኮች ላይም መበርታቱን ዋዜማ ከራሳቸው ከባንኮቹ ምንጮቿ አረጋግጣለች፡፡
ችግሩ ከበረታባቸው የግል ባንኮች መካከል አንዱ በተለይ የነዳጅ ክፍያ በቴሌ ብር አማካኝነት እንዲሰበሰብ መወሰኑን ተከትሎ፣ በየቀኑ ከነዳጅ አዳዮች የሚያገኘውን በሚሊየን የሚቆጠር የጥሬ ገንዘብ ገቢ ማጣቱ ችግር ውስጥ እንዳስገባው የባንኩ ምንጮች ነገረውናል፡፡
የግል ንግድ ባንኮች በገጠማቸው የመከፈል አቅም ውስንነት በርካታ የባንክ ደንበኞቻቸው የሚያንቀሳቅሱትን ገንዘብ ወደ መንግሥታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ማዞራቸውን ከግል ባንኮች ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እስካሁን የጥሬ ገንዘብ እጥረት ውስጥ ካለመግባቱም በላይ ከዚህ ቀደሙ የተሻለ ጥሬ ገንዘብ በስፋት እየሰበሰበ ነው፡፡ ባንኩ ደንበኞች ገንዘባቸውን በሚፈልጉበት ጊዜ ብሔራዊ ባንክ ባስቀመጠው ጣሪያ ልክ፣ ያለገደብ ጥሬ ገንዘብ ማውጣት የሚችሉበት ብቸኛ ባንክ ሆኗል፡፡
ዋዜማ በባንኮች በኩል ያገኘችውን የጥሬ ገንዘብ እጥረት ችግር የባንኮች ተቆጣጣሪ አካል እንዴት እንደሚመለከተው የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥን ፍቃዱ ደግፌን የጠየቀች ሲሆን፣ ባንኮች በሚሉት ደረጃ እጥረት መኖሩን የባንኩ መረጃ እንደማያመላክት ነግረዋታል፡፡
ፍቃዱ ጉዳዩን “እኔ ባለኝ መረጃ ባንኮች ላይ በሚባለው ደረጃ የጥሬ ገንዘብ እጥረት (ሊኪዩዲቲ) የለም” ብለዋል፡፡ ባንኮች ከነዳጅ አዳዮችና ከሌሎች የተለያዩ ደንበኞች በየእለቱ ያገኙት የነበረውን የጥሬ ገንዘብ ገቢ በግዴታ ወደ ቴሌ ብር ስርዓት መቀየሩን ተክትሎ ገጥሞናል ያሉትን ችግር በተመለከተ፣ ምክትል ገዥው ለዋዜማ በሰጧት አስተያየት፣ “እጥረት አለብን ካሉ ተወዳድሮ መሰብሰብ ነው የሚከለክል ሕግ የለም” በማለት ገልጸውታል፡፡ [ዋዜማ]