ዋዜማ- የአማራ ክልል መንግሥት በሁሉም የክልሉ ከተሞች ሁሉንም አይነት የከተማ መሬት አገልግሎቶች ማገዱን ዋዜማ ተረድታለች።

የክልሉ መንግሥት ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት የክልሉ ከተሞች የከተማ መሬት ማስተላለፍ፣ ማዘጋጀትና አገልግሎት መስጠት ሥራዎች ሙሉ በሙሉ እንዲያቆሙ ትዕዛዝ ተላልፎላቸዋል።

በክልሉ የከተማና መሰረተ ልማት በምክትል ቢሮ ኃላፊው አሰፋ ሲሳይ ተፈርሞ፣ ለሁሉም ከተማ አስተዳደሮች እና ዞኖች የከተማ መሰረተ ልማት መምሪያዎች በተላለፈው ደብዳቤ መሰረት አገልግሎቱ ከጳጉሜ 2/2015 ጀምሮ ታግዷል።

ዋዜማ የተመለከተችው የክልሉ ውሳኔ የተላለፈበት ደብዳቤ፣ በሁሉም ከተሞች የታገደው የከተማ መሬት አገልግሎ የጊዜ ቆይታ ላልተወሰነ ጊዜ መሆኑን ይገልጻል።

የክልሉ መንግሥት አገልግሎቱን ያገደው በክልሉ በተፈጠረው ወቅታዊ የጸጥታ መደፍረስ፣ ብልሹ አሰራር መስፋፋቱን እንደ ምክንያት በመጥቀስ ነው። በተከሰተው ወቅታዊ የጸጥታ ችግር ምክንያት በተወሰኑ ከተሞች ሕገ ወጥ ተግባር እየተሰራ መሆኑን ማረጋገጡን ደብዳቤው ገልጿል።

ቢሮው ከተሞች በስራቸው ለሚገኙ ክፍለ ከተሞች፣ እንዲሁም የዞን ከተማና መሠረተ ልማት መምሪያዎች ውሳኔውን እንዲያስተላልፉ ታዘዋል። ትዕዛዙን እንዲያስፈጽሙ ኃላፊነት የተሰጣቸው አካላት ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር  እንዲያደርጉ  ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል።

በክልሉ ከተሞች በመሬት ሥራዎች ላይ ተፈጽሟል የተባለው ብልሹ አሰራር፣ የክልሉ መንግስት በቀጣይ በሚሰጠው አቅጣጫ መሠረት አስፈላጊ የሆነ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ ቢሮው ጠቁሟል።

ዋዜማ ስለ ውሳኔው የጠየቀቻቸው ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ፣ እንደ አዲስ የተደራጀው የክልሉ አመራር በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችን እንደገና የማደራጀት ሥራን ተከትሎ የተወሰነ ውሳኔ መሆኑን ጠቁመዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ካቢኔ እስከታችኛው የመንግሥት መዋቅር ድረስ፣ አጠቃላይ የፖለቲካና የጸጥታ አመራሩን እንደ አዲስ ለማደራጀት ውሳኔ ማሳለፉን የሥራ ኃላፊው አስታውሰዋል። በውሳኔው መሰረት የአመራር ሹም ሽረቱ በሚፈጸምበት ወቅት ነባሩ አመራር ህገወጥ ተግባር እንዳይፈፅም ለመከላከል ተብሎ ያለመ ውሳኔ እንደሆነም ኃላፊው ገልጸዋል።

የአመራር ሹም ሽረቱን እስከታችኛው የመንግሥት እርከን ለማስፈጸም የተያዘው ዕቅድ፣ በክልል፣ በዞንና በከተማ አስተዳደሮች ደረጃ በስፋት መከናወኑንም ምንጩ ለዋዜማ አብራርተዋል።

ክልሉ ግጭት ውስጥ ከገባ በኋላ የመንግሥት አግልግሎት በስፋት መቋረጡን ምንጩ ተናግረዋል።

የክልሉን መንግሥት አመራር በየደረጃው እንደ አዲስ ማደራጀት ክልሉን ከችግር ያወጣ እንደሆነ እስተያየታቸውን የጠየቅናቸው አመራሩ፣ አሁን ላይ ውጤቱን መመዘን እንደማይቻል ገልጸዋል።

የአመራር ለውጡ የመንግሥት አገልግሎት መስተጓጎሎችን ሊፈጥር እንደሚችል እና ሌሎች ያልተጠበቁ ችግሮችን ሊወልድም  ይችላል ብለዋል። 

በክልሉ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎ እና በክልሉ የሚንቀሳቀሱት በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ በተቀሰቀሰበት ሰሞን፣ የክልሉ ገንዘብ ቢሮ የበርካታ ዞኖች፣ ከተሞና ወረዳዎችን የባንክ ሂሳብ እንዳይንቀሳቀስ ማገዱን ዋዜማ መዘገቧ የሚታወስ ነው፡፡

እገዳው የተጣለው ብሔራዊ ባንክ ከአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ በቀረበለት ጥያቄ መሰረት፣ የክልሉ መንግሥት የባንክ ሒሳቦችን እንዳይንቀሳቀሱ ጥሎት የነበረውን እገዳ ካነሳ በኋላ ነው፡፡ [ዋዜማ]