Chrstian Tadele, MP and one of the prisoners at Awash

ዋዜማ- የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጂ አፈጻጸም ጋር በተገናኘ በቁጥርጥር ስር ውለው በአዋሽ አርባ ወታደራዊ እዝ ማሰልጠኛ ካምፕ ውስጥ የሚገኙ እስረኞች የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል እንዲደረግ አሳሰበ፡፡

ኮሚሽኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጂ አፈጻጸም ሁኔታን በተመለከተ ቅዳሜ ነሃሴ 27 ቀን 2015 ዓ.ም አመሻሹ ባወጣው መግለጫ ታሳሪዎች ያሉበት አካባቢ ከፍተኛ ሙቀት ያለው መሆኑን ጠቅሶ የታሰሩ ግለሶቦች  አንድም በብሄር አማራ በመሆናቸው አልያም እምነታቸው ኦርቶዶክስ ክርስቲያን በመሆናቸው እንደታሰሩ ባደረኩት ምልከታ ከታሳሪዎች ስምቻለሁ ብሏል፡፡

ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለን ጨምሮ አምስት የኮሚሽኑ ባለሙያዎች የሚገኙበት ቡድን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሠረት በቁጥጥር ሥር ውለው ካምፕ ውስጥ ተይዘው የሚገኙትን ታሳሪዎች ነሐሴ 26 ቀን 2015 ዓ.ም. መጎብኘቱን አስታውቋል፡፡

በጉብኝቱ ወቅት ከታሳሪዎቹ ተቀበልኩት ባለው ቃል በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦች በምን ምክንያት በቁጥጥር ስር እንደዋሉ መረጃ የሌላቸው፣ አንዳንዶቹ ስለመታሰራች ቤተሰብ ምንም መረጃ እንደሌለው፣ በካምፕ ውስጥ ያሉ ታሳሪዎች ከቤተሰብ ጋር በአካልም ይሁን በስልክ መገናኘት አለመቻላቸውንም ተረድቻለሁ ብሏል፡፡ በመሆኑም የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል መቀጠሉ አስፈላጊ በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ለኮሚሽኑ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ አሳስቧል፡፡

ከታሳሪዎች መካከል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ፣  እንዲሁም የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል አቶ ዮሐንስ ቧያለው፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባል የሆኑት ዶ/ር ካሳ  ተሻገር፤  እንዲሁም  ጋዜጠኛ  በቃሉ  አላምረው፣  አባይ  ዘውዱ እንደሚገኙበት አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም ቴዎድሮስ ዘርፉ፤ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባል አቶ ስንታየሁ  ቸኮል፣  አቶ  በለጠ ጌትነት፤ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ውስጥ  በኃላፊነት  ይሠሩ  የነበሩት  አቶ ከፋለ እሱባለውን ጨምሮ በአጠቃላይ 53 እስረኞች መጎብኘቱን በመግለጫው አትቷል፡፡

በአዋሽ አርባ ካምፕ ታስረው የሚገኙት በአዲስ አበባ ከተማና ከአማራ ክልል የተለያዩ ቦታዎች በተለያየ ጊዜ ተይዘው ከነሐሴ 15 እስከ ነሐሴ 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ የተወሰዱ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡

ኮሚሽኑ ታሳሪዎቹን ለብቻቸውና ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የፖሊስ ኃላፊዎች ማነጋገሩን የገለጸ ሲሆን የፖሊስ ኃላፊዎች ጊዜያዊ ማቆያ ጣቢያ ማምጣት ያስፈለገው አዲስ አበባ የሚገኘው የፌዴራል ፖሊስ ማቆያ ጣቢያ ላይ ከፍተኛ መጣበብ በመፈጠሩ ስለመሆኑ አስረድቷል፡፡

ይሁን እንጂ የአዋሽ አርባ አካባቢ ከፍተኛ ሙቀት ያለበት አካባቢ በመሆኑ በግቢው ውስጥ ካሉት ቤቶች ውስጥ የተሻለ በሆነው ሰፊ  አዳራሽ  ውስጥ  የመኝታ አልጋ ተዘጋጅቶ ታሳሪዎቹ በአንድ ላይ አብረው የተያዙ መሆኑን፣ ነፋስ ለመቀበል መንቀሳቀስ እንዲችሉ መነጋገሩንም አብራርቷል፡፡

የምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለና አቶ ዮሐንስ ቧያለው ወደ አዲስ አበባ ለሕክምና ተወስደው የህክምና አገልግሎት አግኝተው መመለሳቸውንም ስምቻለሁ ብሏል፡፡

ይሁን እንጂ ከቦታው ርቀት አንጻር አብዛኛዎቹ ታሳሪዎች ቤተሰብ እንዳይጉላላ ጉብኝቱን እንደማይፈልጉ መግለጻቸውንና ይልቁን በስልክ ለመነጋገር እንዲችሉ መጠየቃቸውንና ገልጾ ለዚህም ይረዳ ዘንድ ዝግጅቱ እየተጠናቀቀ ስለሆነ በቅርቡ በስልክ ለመነጋገር እንዲችሉ እንደሚደረግ መወያየቱን ኮሚሽኑ አክሎ ገልጿል፡፡

ከታሳሪዎች መካከል እጅግ አብዛኛዎቹ ታሳሪዎች ብሔራቸው አማራ፣ እምነታቸው ኦርቶዶክስ ክርስቲያን መሆኑንና ለእስር የተዳረጉት በብሔር ማንነታቸው ብቻ መሆኑን እንደሚያምኑ ገልጸውልኛል ብሏል፡፡

በሌላ በኩል በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በተያዙበትና ቤታቸው በተበረበረበት ወቅት በራሳቸውና በቤተሰብ አባል ላይ ድብደባ፣ ብሔር ተኮር ስድብ፣ ማጉላላት፣ ዛቻና ማስፈራራት እንደደረሰባቸው ከታሳሪዎች አንደበት መስማቱን አስታውቋል፡፡

በፌዴራል ፖሊስ ቁጥጥር ስር ከሆኑ በኋላ የተፈጸመ ድብደባ ወይም አካላዊ ጥቃት ባይኖርም ከፊሎቹ በተለይም ከአማራ ክልል ተይዘው የመጡ ሰዎች ከተያዙበት ጊዜ ጀምሮ ቤተሰቦቻቸው የት እንዳሉ እንኳን እንደማያውቁ ነግረውኛል ብሏል፡፡

የአዋሽ አርባ አካባቢ እጅግ ከፍተኛ ሙቀት ያለው በመሆኑና  ከአካባቢው  የአየር ጠባይ እንዲሁም ቦታው የወታደራዊ ካምፕ እንጂ መደበኛ የተጠርጣሪዎች ማቆያ ስፍራ ስላልሆነ ለጤንነታቸው፣ ለደኅንነታቸውና ለሕይወታቸው ሥጋት እንዳላቸውም አክሎ አስታውቋል፡፡

ታሪዎቹ አልባሳትን ጨምሮ ከቤተሰብ የሚፈልጉትን አቅርቦት ለማግኘት እንዳልቻሉ፣ ከፊሎቹ በሥራቸውም ሆነ በግል ሕይወታቸው ፈጽሞ በፖለቲካ ነክ ጉዳይ ተሳትፎ እንደሌሉና እንዴት ለእስር እንደበቁ ግርምት እንደፈጠረባቸው ስመናገራቸውም ያስረዳል፡፡

ኮሚሽኑም ከፖሊስ ኃፊዎች ጋር አካሄድኩት ባለው ውይይት በእስር ወቅት ተፈጽመዋል  ስለተባሉ  የሥነ ምግባር ጥሰቶች ተገቢው ማጣራት እንዲደረግ፣ ታሳሪዎቹ ከቤተሰብ ለሚፈልጉት አቅርቦት አዲስ አበባ በሚገኘው የፖሊስ ቢሮ አማካኝነት እንዲመቻች፣ ከቤተሰብ መገናኛ ስልክና ጉብኝት ለሚፈልጉም በአፋጣኝ እንደሚመቻች መግባባት ላይ መድረሱን በመግለጫው አስታውቋል፡፡

ኮሚሽኑ ከአዋጁ አፈጻጸም ጋር የተያያዙ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታን በተመለከተ አዋጁ ስራ ላይ ከዋለበት ሃምሌ 28 ቀን 2015 ዓ፣ም ጀምሮ የሚደርሱትን አቤቱታዎችና ጥቆማዎች ከመመርመር፣ መረጃዎችንና ማስረጃዎችን ከማሰባሰብ በተጨማሪ፣ ተጎጂዎችን፣ የተጎጂ ቤተሰቦችን፣ ምስክሮችንና ሌሎች የመረጃ ምንጮችን ንግግር እያደረኩ ነው ብሏል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድን ኃላፊዎችን ጨምሮ ከሚመለከታቸው የጸጥታ አካላት ጋር በመነጋገር የከትትልና የውትወታ ስራ እየሰረሁ ስመሆኑም አስታውቋል፡፡

በኮማንድ ፖስቱ ትዕዛዝ መታሰራቸው ከተገለጸው ታሳሪዎች በተጨማሪ በዚሁ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ዐውድ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ፤ በአማራ ክልል ባሕር ዳር፣ ደብረ ታቦር እና ጎንደር ከተሞችን ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎች፤ በኦሮሚያ ክልል በአዳማ፣ በቢሾፍቱ፣ በገላን እና በሸገር እንዲሁም ሌሎች ከተሞች፣ መደበኛ ያልሆኑ ቦታዎች ተይዘው ስለነበሩ ሰዎች፣ ከፊሎቹ የተለቀቁ ቢሆንም ይህ ጋዜጣዊ  መግለጫ  ይፋ  እስከሆነበት  ጊዜ ድረስ በእስር ላይ ስለሚገኙ ሰዎችና ከእነዚህም መካከል የኤርትራ ፍልሰተኞችን ጨምሮ ኮሚሽኑ ክትትል በማድረግ ስለመሆኑ አስታውቋል፡፡ [ዋዜማ]