ሰኔ 23፣ 2012
ታዋቂው የአፋን ኦሮሞ ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ትናንት፣ ሰኞ ሰኔ 22 ቀን 2012፣ ምሽት ማንነታቸው ባልተወቁ ሰዎች አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በጥይት ተመትቶ ሕይወቱ አልፏል። ይህ ዜና የቀሰቀሰው ቁጣ በተለይ በኦሮሚያ ክልል እና በአዲስ አበባ ከተማ የጸጥታ ስጋት ፈጥሯል።
ውጥረቱን ተከትሎ ዛሬ ጠዋት ኢንተርኔት ተቋርጦ ነበር። እኩለ ቀን ገደማ ተመልሶ መከፈቱ ታውቋል። በሌላ በኩል የፌደራል ፖሊስ የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክን ቢሮ በመያዝ የተወሰኑ ጋዜጠኞች መታሰራቸውን ጣቢያው በማኅበራዊ መገናኛ አስታውቋል።
ዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ዛሬ ከማለዳ ጀምሮ ከወትሮ በመጠኑ የቀዘቀዘ እንቅስቃሴ ሲታይባት ውሏል። ሆኖም ይህን ዘገባ በምናጠናቅርበት ወቅት ይህ ነው የሚባል ከፍተኛ የጸጥታ ችግር ስለመፈጠሩ አልተዘገበም። ቢሆንም ውጥረቱ በጊዜ ካልረገበ አደገኛ የጸጥታና የመረጋጋት ጅግር ሊያስከት እንደሚችል በመንግሥት ውስጥ ያሉ ባለሞያዎች ሳይቀሩ ስጋታቸውን እየገለጹ መሆኑን ዋዜማ ተረድታለች። ችግሩ ከተባባሰ ከዚህ ቀደም ታይቶ እንደነበረው የጸጥታና የደኅንነት አካሉን መዋቅር መልሶ እንዳያናጋው ተሰግቷል። ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የመንግሥት ሐላፊዎች ተከታታይ መግለጫ እንደሚሰጡ እንደሚጠበቅ ተረድተናል።
ትናንት ምሽት የሃጫሉ ሞት ከተሰማ ብዙም ሳይቆይ የከተማዋ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ለኢቢሲ በሰጡት መግለጫ “የተወሰኑ ተጠርጣሪዎች” መያዛቸውንና ምርመራው መጀመሩን ገልጸው ነበር። የኮሚሽነሩ መግለጫ መረጃ ከመስጠት ይልቅ ሕዝቡን በማረጋጋት ላይ ያተኮረ ነበር።
በአቃቂ ቃሊት ክፍለ ከተማ፣ ገላን ኮንዶሚኒየም በሚባልው አካባቢ ከምሽቱ 3፡30 ገደማ ተፈጸመ በተባለው ጥቃት በጥይት የተመታው ሃጫሉ በአቅራቢያው ወደነበረ ሆስፒታል ቢወሰደም ሕይወቱን ማትረፍ ሳይቻል ቀርቷል። ፖሊስም ሆነ የሆስፒታል ምንጮች ሃጫሉ በስንት ጥይቶች እንደተመታና ምን አይነት ጉዳት ለሞት እንዳበቃው አልገለጹም።
አስከሬኑ ከጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል ወጥቶ ሌሊቱን ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ለአስከሬን ምርመራ መወሰዱን ሰምተናል። ዛሬ ማክሰኞ ረፋድ ላይም እጅግ በርካታ የድምጻዊ አድናቂዎች በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል አቅራቢያ በሚገኙት ጎዳናዎች ተሰብስበው ሀዘናቸውንና አድናቆታቸው በስሜት ሲገልጹ አርፍደዋል። አስቀድሞ አስከሬኑ የሃጫሉ የትውልድ ቦታ ወደ ሆነችው ወደ አምቦ ከተማ ይወሰዳል በሚል ጉዞ ቢጀመረም ቡራዩ አካባቢ ሲደርስ አስከሬኑን አስገድዶ ወደ አዲስ አበባ ለማስመለስ ጥረት ተደርጎ እንደነበር የክልሉ ም/ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ዛሬ ማምሻውን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። አስከሬኑ ወደ አዲስ አበባ ከተመለሰ በኋላ በሔሊኮፕተር አምቦ ደርሷል። የቀብሩ ሥርዓት በክልሉ መንግሥት ሃላፊነት ቤተሰቦች በሚፈቅዱት ሁኔታ የሚከናወን ይሆናል ተብሏል። ለሃጫሉ ክብርም የክልሉ ባንዲራ ለአምስት ቀናት ዝቅ ብሎ እንደሚውለበለብ አቶ ሽመልስ አስታውቀዋል።
ይህን ዘገባ እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ የድምጻዊ ቀብር የት እንደሚፈጸም ቁርጥ ያለ ውሳኔ አለመሰጠቱን አውቀናል። ውሳኔውን የሚሰጡት አካሎች ማንነትም ግልጽ አይደለም። አንድ ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ሃላፊ፣ የሃጫሉ ቀብር ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካና የደኅንነት አንደምታ ያለው ጉዳይ በመሆኑ “የመንግሥት አካላት ከትናንት ምሽት ጀምሮ በጥብቅ እየተነጋገሩበት” መሆኑን እኩለ ቀን ገደማ ለዋዜማ አረጋግጠዋል። በሌላ በኩል፣ ተሰሚነት ያላቸው የኦሮሞ ፖለቲካ መሪዎችና አክቲቪስቶች ቀብሩ በአዲስ አበባ እንዲፈጸም ፍላጎት እንዳላቸው ያሰባሰብናቸው አስተያየቶች ይጠቁማሉ።
የድምጻዊው ሞት ከተሰማ በኋላ በማኅበራዊና በመደበኛ ሚዲያ (ዩ ትዩብን ጨምሮ) በርካቶች ልባዊ ሐዘናቸውን እየገለጹ ነው። ሆኖም በቁጭትና በእልህ ስሜት የሚቀርቡት ስሜት ቆስቋሽ አስተያየቶች አመጽ ሊጋብዙ እንደሚችሉ ታዛቢዎች እያስጠነቀቁ ነው። የጸጥታ መሥሪያ ቤቱ በበኩሉ ሁኔታው የደኅንነት አደጋ ሊጋብዝ እንደሚችል በማመን ከወትሮው ለየት ያለ ክትትል ሲያደርግ ማደሩን ሰምተናል።
ዛሬ ከጠዋት ጀምሮ ጠቅላይ ሚኒስትሩንና የኦሮሚያ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድርን ጨምሮ በርከት ያሉ ከፍተኛ የመንግሥት መሪዎች ሀዘናቸውን ሲገልጹ፣ ገዳዮች ለሕግ እንደሚቀርቡ ሲያሳስቡ፣ ሕዝቡ እንዲረጋጋ ሲማጸኑ ቢያረፍዱም በተለይ በኦሮሚያ ክልል ሰልፎችንና ተቃውሞዎችን ማስቀረት አልቻሉም። በአዲስ አበባ አስከሬኑ ሲሸኝ በነበርበት አካባቢ በጸጥታ ኅይሉና በሰልፈኖቹ መካከል በተፈጠር አለመግባባት ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ መጠቀሙ ተዘግቧል። በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ ከተሞች ወጣቶች የተቃውሞ ድምጻቸውን እያሰሙና በመንግሥት ተቋማት ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን፣ በመንግሥት ሃይሎች ተፈጸመ በተባለ ምላሽም ሁለት ሰዎች ጭሮ ላይ መሞታቸውን ቢቢሲ ኦሮሚኛ ዘግቧል። በሐረር ከተማ የሚገኘው የራስ መኮንን ሐውልት በተቃዋሚዎች መፍረሱን የሚያሳዩ ፎቶዎች በማኅበራዊ ሚዲያ እየተሰራጩ ነው።
ሃጫሉ ሁንዴሳ በኦሮሞ ሙዚቃ በተለይም ለአዲሱ ለውጥ ቁልፍ ሚና በነበረው የኦሮሞ ወጣቶች ተቃውሞ ወቅት እጅግ ገኖ የወጣ ድምጻዊና የዘፈን ግጥም ጸሐፊ ነው። በዘመኑ “የኦሮሞ ወጣቶችን የትግል ስሜትና የዴሞክራሲ ፍላጎት የእርሱን ያህል አጉልቶ ያወጣና በጥበበ የገለጸ የጥበብ ሰው ማግኘየት አይቻልም” ብለውናል አንድ አድናቂው። የሃጫሉ የሙዚቃ ሥራዎችና የትግል መልዕክቶች ከኦሮሞ ወጣቶች ባሻገርም አድናቆትን ያስገኙለት ነበሩ።
ማስተካከያ (ሰኔ 23፣ ምሽት 1፡00) – ቀደም ባለው የዚህ ዜና አይነቴ የሃጫሉ አስከሬን አዲስ አበባ ወደሚገኘው የኦሮሞ ባህል ማዕከል እንዲመለስ ተደርጓል ተብሎ የተዘገበው ትክክል ቢሆንም አስከትሎ በሔሊኮፕተር ወደ አምቦ መወሰዱን አለማካተታችን ስሕተት ነበር። በጉዳዩ ላይ ውዝግብ የነበረ ቢሆንም በመጨረሻ አስከሬኑ ወደ አምቦ መወሰዱን ዘግይቶ ተረድተናል። ዜናውም በዚሁ መረጃ ተስተካክሏል። ስለ ስሕተቱ ይቅርታ እንጠይቃለን።
የኢንተርኔትን መቋረጥ በተመለከተ እኛ ዘገባችንን ስንጽፍ ተመልሶ ተከፍቶ የነበረ ቢሆንም ቆይቶ መዘጋቱን ተረድተናል።
ሌሎች አዳዲስ መረጃዎች በዕለቱ “ለቸኮለ” ቅንብራችን ተካተዋል።
—–
የዋዜማ ሬዲዮ ባልደረቦች በሃጫሉ ሁንዴሳ ሞት የተሰማንን ሀዘን እንገልጻለን። ለቤተሰቦቹና ለወዳጅ አድናቂዎቹም መጽናናትን እንመኛለን።