በአዲስ አበባ የሚዘጋጁ የስዕል አውደ ርዕይ (Exhibition) ላይ የቀረቡ ስዕሎች የዕይታ ጊዜያቸው ከተጠናቀቀ በኋላ በተራው ነዋሪ መኖሪያ ቤት የመግባት ዕድላቸው አነስተኛ ነው፡፡ ስዕሎቹን የራስ ለማድረግ የከተማዋ ቱጃር ነጋዴ አሊያም ዲፕሎማት ወይም ደግሞ እግር የጣለው ፈረንጅ መሆን ግድ የሚል ይመስላል፡፡ ከየስዕሎቹ ግርጌ የሚለጠፉ ዋጋዎች ይህንን ይመሰክራሉ፡፡
ሸራተን አዲስ በሚያዘጋጀው ዓመታዊ የስዕል አውደ ርዕይ ላይ የሚቀርቡ አንዳንድ ስራዎች እስከ ግማሽ ሚሊዮን ብር ይጠራባቸዋል፡፡ መደበኛ መነሻቸው በመቶ ሺህዎች የሆኑ፤ አንዳንድ ጊዜም ዋጋቸው በድርድር ብቻ የሚገለጹ አይቀመሴ የስዕል ስራዎችን በአይን ብቻ ጎበኝቶ መመለስ ተለምዷል፡፡
ስዕል የመግዛት ፍላጎትን የሚያሳካ እና የስዕል አምሮትን የሚቆርጥ የስነጥበብ ሽያጭ ባዛር በአዲስ አበባ ተዘጋጅቷል፡፡ ከመቶ በላይ የአገሪቷ ሰዓሊያን፣ ቀራፂያን እና “ክርኤቲቭ” ፎቶግራፈሮች የተሳተፉበት የስነጥበብ ሽያጭ ባዛር ነገ ቅዳሜ መጋቢት 17 በብሔራዊ ሙዝየም ይከፈታል፡፡
የአውደ ርዕዩ አዘጋጅ የሆነው የኢትዮጵያ ሰዓሊያን እና ቀራፂያን ማህበር ዋና ፀሐፊ ሰይፉ አበበ ባዛሩ “ሰዓሊውን ከገዢው ጋር ለማገናኘት ታስቦ የተዘጋጀ ነው” ይላሉ፡፡ “ከዚህ በፊት እሰከ አርባ የሚደርሱ አርቲስቶች ብቻ ነበር በአንድ ላይ መጋበዝ የቻልነው፡፡ በአሁኑ ግን እስከ መቶ ይደርሳሉ” ሲሉ የጥበበኞቹ ቁጥር መጨመሩን ይናገራሉ፡፡
በዚህ ባዛር ላይ እያንዳንዱ አርቲስት እስከ አስር የሚደርሱ ስራዎች ይዞ እንዲቀርብ ስለተጋበዘ በብሔራዊ ሙዝየም ከሚገኘው አዳራሽ በተጨማሪ በሙዝየሙ ግቢ ውስጥ በሚተከሉ ድንኳኖች ወደ አንድ ሺህ የሚደርሱ የስነጥበብ ስራዎች ሽያጭ ይከናወናል፡፡
ለአስራ ሁለት ቀናት እስከ መጋቢት 28 ድረስ የሚቆየው ባዛር ህፃናትንም ከጥበቡ ማዕድ እንዲካፈሉ ጋብዟል፡፡ ባዛሩ በሚቆይባቸው ቀናት ባሉ ቅዳሜና እሁድ እስከ አስራ ሁለት አመት እድሜ ለደረሱ ልጆች ስዕሎችን እንዲስሉና እንዲማሩ ልዩ ቦታ ተዘጋጅቶላቸዋል፡፡