መስፍን ነጋሽ ለዋዜማ ራዲዮ
የእነ ሌንጮ ለታ ቡድን ወደ አገር ቤት መመለሱ መልካም ዜና ነው። ሆኖም የግለሰቦቹ መመለስም ሆነ የድርጅታቸው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) አገር ቤት መግባት ያለው ፖለቲካዊ ፋይዳ መጋነን የለበትም። በመሠረቱ አሁን ባለው የፖለቲካ አሰላለፍ ግለሰቦቹም ሆኑ ድርጅታቸው ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ ተጽእኖ የላቸውም። በድርጅታዊ አቅምም ይሁን በርእዮተ ዓለማዊ ተዋስኦ ለአገር ቤቱ ፖለቲካ የሚጨምሩለት ሁነኛ ግብአት የለም።
እነዲማ በታሪክና በትግል ውርስ በኦሮሞ ብሔረተኝነት ትግል ውስጥ የሚታወቁ ቢሆኑም ዛሬ ላይ ያለቻቸው አንድ ብቸኛ ልዩ መገበያያ የመገንጠል ፖለቲካ የማይሳካም የማያዋጣም መሆኑን ተቀብለው “ችግራችንን በአገረ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነን እንፍታ” የሚል በሳል አቋም መውሰዳቸው ነው። ይህ አቋም ግን በስደት ፖለቲካ እና በኦሮሞ ብሔረተኝነት ዜና መዋዕል ውስጥ ካልሆነ በስተቀር፣ ኢትዮጵያ አሁን በደረሰችበት ሁኔታ ከሌሎች የሚያስመርጥ የፖለቲካ አጀንዳ አይደለም።
በድርጅታዊ አቅምም ቢሆን ኦዴግ አብዛኞቹ አባላቱ ያሉት በውጭ አገር ነው፤ ስንት አባላት እንዳሉት ባናውቅም። በመሠረቱ ድርጅቱ በነሌንጮ የቀደመ ፖለቲካዊ ዝና እና በስደት ፖለቲካ ድባብ ውስጥ ባይፈጠር ኖሮ ማንም ከቁም ነገር አይቆጥረውም ነበር። የግለሰቦቹን ፖለቲካዊ ቁመና ትልቅነት የሚካድ ባይሆንም፣ ድርጅታቸው ግን በዚህ ቁመና ጥላ ስር የበቀለ ሐረግ ነው። ከዚህ አኳያ፣ ኦዴግ ኦሮሚያ ውስጥ ራሱን የቻለ ፓርቲ ሆኖ ለአንድ ዓመት መቀጠሉን በጣም እጠራጠራለሁ።
የሰዎቹ መመለስ ፋይዳ በወሳኝ መልኩ ምናልባት ሊመነጭ የሚችለው ከኢሕዴግ ጋራ ያደርጉታል በተባለው “ድርድር” ውጤት እና መመለሳቸው የፖለቲካ ስደተኞች ምጽአት ማሳያ ከመሆኑ አንጻር ብቻ ነው። እነሌንጮ የታወቁ የፖለቲካ ስደተኞች እንደመሆናቸው መጠን፣ መመለሳቸው ቢያንስ በኦሮሞ ፖለቲከኞች አካባቢ ትልቅ ምሳሌያዊ ፋይዳ ይኖረዋል። የእነርሱ መመለስ ለሌሎች በስደት ላሉ ፖለቲከኞች ብዙ ትርጉም የማይሰጠው በሁለት ምክንያቶች ነው። አንዱ፣ ሰዎቹ ድሮውንም በአነስተኛ መደራደሪያዎች ለመመለስ ተዘጋጅተው ሲጠብቁ እንደነበር በስፋት መታመኑ ነው። ሁለተኛው ደግሞ፣ በርእዮተ ዓለምም ሆነ በፖሊሲ ከህወሓት/ኢሕአዴግ ብዙም የተለዩ ባለመሆናቸው ለገዢው ፓርቲ የስጋት ምንጭ የመሆን እድላቸው ዝቅተኛ መሆኑ ነው። በእርግጥም፣ ጠሚ ዐቢይ በትኩረት የሚሰብኩት የእርቅ መንፈስ የአገር ቤቱን ተዋስኦ መቆጣጠሩ፣ ኦሕዴድ ከደረሰበት ፖለቲካዊ ቁመና ጋራ ተደምሮ፣ ገዢው ፓርቲ እነሌንጮን “ቢመጡ የማይጎዱ፣ ቢቀሩ የሚያሳጡ” አድርጎ እንዲመለከታቸው ሳያደርገው አልቀረም። ተጨማሪ ምክንያት ለሚፈልግ ደግሞ፣ ዋነኛ ታራቂዎቹ (ኦሕዴድ እና ኦዴግ) የኦሮሞ ብሔረተኝነት አቀንቃኞች መሆናቸው የብሔር መሳሳብ ተደርጎ መታየቱ የሚናቅ ምልከታ አይሆንም።
ድርድር የተባለው ነገር መጋረጃው ያልተገለጠ ቴአትር ነው። ቃለ ተውኔቱ ተጽፎ ያለቀ ስለመሆኑም አናውቅም። ቀደም ሲል ካነሳናቸው ነጥቦች አኳያ፣ ኦዴግ በየትኞቹ ፖለቲካዊ ምክንያቶች ለተደራዳሪነት በቅድሚያ እንደተመረጠ አይታወቅም። ሌላው ቀርቶ፣ መንግሥት ከኦፌኮ (መድረክ የሚባለው ስብስብ አለ?) ጋራ ሳይደራደር፣ ከኦዴግ ጋራ የሚደራደርበት አግባብ ግልጽ አይደለም።
ምናልባት ከኦዴግ ጋራ የሚደረገው ንግግር (ድርድር?) ወደፊት ስለሚደረገው ድርድር ከሆነ የምናየው ነው። ከዚያ ባለፈ፣ ኦዴግ በሕገ መንግሥቱ ላይ ይህ ነው የሚባል ጥያቄ ያለው ስለመሆኑ አልሰማሁም፤ አምልጦኝ ይሆናል። ከዚያ በመለስ ባሉት የጸረ ሽብር ሕጉን በመሳሰሉት ሕጎች፣ ምርጫ ቦርድን በመሳሰሉ ተቋማት ላይም ቢሆን ኦዴግን ለብቻ ተደራዳሪነት የሚያስጠራ ምክንያት የለም። ኦዴግ ከመመሥረቱ በፊት ያሉ ፓርቲዎች፣ በውጭም በውስጥም፣ ሕጎቹ እንዲሻሻሉ ወይም እንዲሻሩ ሲጣሩ ባጅተዋል። ታዲያ ኦዴግን በአናት አምጥቶ ቀዳሚ ተደራዳሪ ያደረገው ምንድን ነው? አላወቅንም።
ወጣም ወረደ፣ ኦዴግም ሆነ አመራሮቹ ብቸኛ የፖለቲካ ሜዳቸው ኦሮሚያ እስከሆነች ድረስ ቢያንስ ራሳቸውን ለማስተዋወቅ ብዙ ችግር አይኖርባቸውም። ሆኖም፣ ወደ ኦሕዴድ ወይም ኦፌኮ ካልተጠቃለሉ፣ በኦሮሚያ ምርጫ ማሸነፍ የሚችሉበት ተጨባጭ ሁኔታ የለም። ትልቅ ሕልውናዊ ፈተና የሚጠብቃቸው በአገር አቀፍ የፖለቲካ ሜዳ ለመወዳደር ከፈለጉ ነው። ያን ጊዜ የነሌንጮ የፖለቲካ ታሪክ ብዙ ማብራራት የሚጠይቅ የፖለቲካ እዳ ሆኖ ይመጣል። በስተእርጅና ወደዚህ ማራቶን የሚገቡ አይመስለኝም፣ አድካሚ ጉዞ ነው።
በአትኩሮት ሲያዩት፣ የኦዴግ አመላለስ ወደ ባህር የሚፈስ ትንሽ ወንዝ አይነት ነው። የባህሩን ውሃ በመልክ፣ በመጠን፣ በይዘት ወይም በውስጣዊ ንቅናቄው(ማእበል መጠኑ) በጉልህ የሚቀይር ላይሆን ይችላል፤ ሆኖም የባህሩ ውሃ የድሮ ውሃ ሆኖ አይቀርም። ኦዴግ “ባንስም ጠጅ ነኝ” ብሎ በህወሃት/ኢሕአዴግ ሠራሹ የአገሪቱ የፖለቲካ ባህር ላይ የሚታይ ለውጥ የሚያመጣ ከሆነ ሳናየው አንቀርም። የባሕሩን ውሃ እናስተውላለን።