ዋዜማ – በታንዛንያ በሁለት ዙር ተካሂዶ ባለቀ ሰዓት የተሰተጓጎለውን የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊትንና የመንግስትን ድርድር ለሶስተኛ ዙር ለማስቀጠል እንዲሁም የአማራ ክልል ፋኖ ታጣቂዎችን ወደ ድርድር ለማምጣት በአሜሪካ እና በአውሮፓ ህብረት በኩል የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ዋዜማ ከዲፕሎማቲክ ምንጮች ሰምታለች።
የፌደራሉ መንግስትና የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ድርድር በስልጣን ድልድልና በአሸባሪነት ፍረጃ እንዲሁም ጉልህ ባልሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ በተነሱ አለመግባባቶች ከሁለት ወራት በፊት ሳይሳካ መቅረቱ ይታወሳል። ድርድሩ ለምን እንዳልተሳካና የድርድሩ ዋና ዋና ነጥቦችን እዚህ ማስፈንጠሪያ ላይ ያገኙታል።
የአሜሪካ መንግስት ዋና አደራዳሪ ማይክ ሀመር ከኢጋድና የአፍሪቃ ህብረት ጋር በመሆን ድርድሩን ለማስቀጠል የሚያስችል ውይይት ከመንግስት ጋር ለማድረግ እና የፕሪቶሪያውን ስምምነት አተገባበር ለመገምገም ባለፉት ቀናት ወደ አዲስ አበባ አቅንተው ነበር። በቆይታቸውም ድርድሩን ማስቀጠል የሚያስችሉ ዝርዝር ጉዳዮችን ከሚመለከታቸው ጋር መወያየታቸውን ምንጮች ነግረውናል።
ከኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት በተጨማሪ በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሱ የፋኖ ታጣቂዎች ጋር ድርድር ማድረግ የሚቻልበት ጉዳይ ላይ ባለፉት ሁለት ወራት በአሜሪካ መንግስትና በአውሮፓ ህብረት እንዲሁም በእንግሊዝ መንግስት በኩል ጥረቶች ሲደረጉ ሰንብተዋል።
ከአማራ ክልል ሀይሎች ጋር ድርድር ለማድረግ እጅግ ፈታኝ የሆነው በተበታተነ መልኩ ያለው አደረጃጀት ታጣቂዎቹንም ሆነ ያሏቸውን ጥያቄዎች ይዞ በአንድ ድምፅ ሊቀርብ የሚችል ሀይል አለመኖሩ መሆኑን ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ያስረዳሉ።
በሀገርቤትም ሆነ በውጪ ያሉ የፋኖ አደረጃጀቶች የተለያዩ መሆናቸው ቅድመ ድርድር ለመጀመር የሚያስችል ውይይት ለማድረግ እንኳ ፈታኝ ሆኖ ቆይቷል። ከታጣቂዎቹ ወገን ወደ ድርድር መምጣት ላይ ተቃውሞ ያላቸውና ጥያቄያቸውን በመሳሪያ ሀይል እንፈታለን ብለው የሚያምኑ እንዳሉም ምንጮች አልሸሸጉም። ይህን የተጠሪነት ችግር ለመፍታት ድርድሩ በቅድሚያ በሀገር ቤት በአቀራራቢ ሽማግሌዎች በኩል እንዲጀመርና ሁሉን ያማከሉ ተደራዳሪዎች እንዲለዩ ሀሳብ ያቀረቡም መኖራቸውን ስምተናል።
በሌላ ወገን ድርድሩ በአማራ ክልል መንግስትና በታጣቂዎች መካከል እንዲደረግ የሚያስችል ሀሳብ ያላቸው የአውሮፓ ዲፕሎማቶች የክልሉን ፕሬዝዳንት አረጋ ከበደን በሁለት ዙር ማወያየታቸው ታውቋል።
የፌደራሉ መንግስት ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር ድርድር ለማድረ አስቻይ ሁኔታዎች መኖራቸው ላይ ጥርጣሬ እንዳለው ገልፆ፣ ለሚደረጉ ማናቸውም ድርድሮች በሩ ክፍት መሆኑን ነግሮናል ብለዋል ዲፕሎማቶቹ።
እነዚህ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ያተኮሩ የሰላም ጥረቶች በእንጥልጥል ባሉበት ሰዓት በሶማሊያና በኢትዮጵያ መካከል የተፈጠረው ውጥረት እንዲሁም የሱዳኑ ጦርነት መባባስ ምዕራባውያኑን የበለጠ እንዳሳሰባቸው እየገለፁ ነው። [ዋዜማ]
To reach Wazema Editors, Please write wazemaradio@gmail.com