ዋዜማ- የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (አልያም በፌደራሉ መንግሥቱ አጠራር ኦነግ-ሸኔ) እና የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ባደረጓቸው ኹለት ዙር ድርድሮች ወደ ስምምነት ለመድረሰ ተቃርበው ነበር። በኹለተኛው ዙር ድርድር የመጨረሻ ሰዓት ላይ በተፈጠረ አለመግባባት፣ ተስፋ የተጣለበት ድርድር ያለውጤት መጠናቀቁም ሲነገር ሰንብቷል። ያ ድርድር ስለምን ከሸፈ? ተደራዳሪዎቹስ ሊስማሙባቸው ያልቻሏቸው አጀንዳዎች ምንድን ነበሩ? እነዚኽን እና መሰል ጥያቄዎችን አስመልክቶ፣ ዋዜማ ያሰባሰበቻቸውን መረጃዎች እንደሚከተለው አሰናድተነዋል።  

 የታንዛኒያው ጠረጴዛ

ዕለተ ማክሰኞ ሚያዝያ 17 2015 ዓ.ም.፣ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (ኦነሠ) ተደራዳሪዎች ዛንዚባር ላይ መገናኘታቸው ሲረጋገጥ፣ የአገሪቷ የሰላም ቆሌ ይራዳቸዋል ብለው ተስፋ ያደረጉ ብዙዎች ነበሩ። በፕሪቶሪያ ከሕወሓት ጋራ የተፈፀመው የሰላም ስምምነት የፈጠረው መነቃቃት፣ ለመንግሥትም ሆነ ለኦነሠ ብርታት ሳይፈጥርላቸው አልቀረም ነበር። ተደራዳሪዎቹ የሄዱባት ታንዛኒያ፣ ነጻነቷን ካገኘችበት እ.ኤ.አ. ከኅዳር 1954 ወዲህ፣ ከአጎራባቾቿ ጋራ ስትነፃፀር የጎላ የእርስ በእርስ ጦርነት ያላገጠማት ሰላማዊ አገር ነች። እንዲያውም የጎረቤት አገር ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ እና ደቡብ ሱዳንን ውስጣዊ ሰላም ያሰፍናሉ የተባሉ በርካታ የሰላም ድርድሮች እና ስምምነቶች የተከወኑባትም አገር ነች። ቢያንስ ከዚኽ አኳያም፣ የኢትዮጵያም ሰዎች አንዳች ስምምነት ላይ ይደርሳሉ የሚል ተስፋ አርብቦ ነበር። 

መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ ተደራዳሪዎቹ ወደ ዛንዚባር እና ዳሬ ሰላም ሲሄዱም ሆነ ሲመለሱ፣ እንዲስማሙ ሊያደርጓቸው የሚችሉ  ውጫዊ እና ውስጣዊ ኹኔታዎች አልነበሩም። ከታንዛኒያው ጠረጴዛ ቀደም ብሎም፣ የኢትዮጵያን መንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን ለማቀራረብ አገር ቤት የተደረጉ በርካታ ሙከራዎች በተደጋጋሚ ከሽፈዋል። የዛንዚባሩ ድርድር እንደሚካሄድ ማረጋገጫው የተሰማውም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ ሚያዝያ 15 2015 ዓ.ም. የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት እንዲያበቃ አስተዋፅኦ አበርክተዋል ለተባሉት የተለያዩ አካላት በተዘጋጀው የዕውቅና ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝተው፣ መንግሥታቸው ከኦነሠ ተወካዮች ጋራ በዛንዚባር ደሴት ለድርድር እንደሚቀመጥ ሲያስታውቁ ነበር።

“ከኦነግ-ሸኔ ጋራ ከነገ ወዲያ ታንዛኒያ ውስጥ ድርድር ይጀመራል” ሲሉ አስታወቁ። ኦነሠ በበኩሉ፣ በማግስቱ ባወጣው መግለጫ የድርድር ቀጠሮ መኖሩን አረጋገጠ። በዚኽ መግለጫው ግን፣ “ሸኔ” እየተባለ መጠራቱን አጥብቆ አወገዘ። “በስሜ ጥሩኝ” ሲል ያሳሰበው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፣ ከዚህ ውጭ ባለ ስም መጠራቱ “የተሳሳተ፣ ማንነቴንና አላማዬን አዛብቶ ለማቅረብ የሚደረግ ሙከራ ነው” ሲልም መንግሥት ከዚኽ ተግባሩ እንዲታቀብ አሳሰቦ አለፈ። 

የዛንዚባሩ ድርድር መተማመን ለመፍጠር እና በቀጣይ ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቀው ድርድር አካሄዶች ላይ ለመስማማት የታቀደ ነበር። የኦነሠ ቃል አቀባይ ድርድሩ በኖርዌይ እና በኬንያ አደራዳሪነት እንደሚከናወን፣ በቀጣይ ግን አሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረት እና ኢጋድ በሂደቱ እንደሚሳተፉ ለ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ በሰጡት ቃል አረጋግጠው ነበር። ኬንያ እና ኖርዌይ በጋራ በመሩት የዛንዚባሩ የመጀመሪያ የዝግጅት ድርድርም፣ ኹለት ስኬቶች ተመዝግበዋል። የዋዜማ ምንጮች እንደሚሉት፣ ኦነሠ ወደ ድርድሩ ከመግባቱ በፊትም ሆነ ዛንዚባር ላይ ቅድሚያ ሰጥቶ ያቀረበው ቁልፍ ጥያቄ፣ ድርድሩ በሦስተኛ ወገኖች አደራዳሪነት እንዲካሄድ እና ስምምነቱም በዋስትና ሰጪዎች አማካይነት እንዲደመደም ነበር። አሜሪካ፣ ኖርዌይ እና የአውሮፓ ኅብረት ዋስትና ሰጪዎች እንዲሆኑ የኦነሠ ጥብቅ ፍላጎት ነበር። የሦስተኛ ወገኖችን አደራዳሪነት ሲገፋ የሰነበተው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ በኦነሠ በኩል የቀረበውን ይኽንን የአደራዳሪዎችን እና የዋስትና ሰጪዎችን ጥያቄ ሲቀበል፣ ኹሉም ወገኖች ተስፋ አድሮባቸው ነበር። የኢትዮጵያ መንግሥት ተደራዳሪዎቹን ወደ ታንዛኒያ ሲልክም፣ በዚኽ ቅድመ ኹኔታ መስማማቱን ማመላከቱ አልቀረም። በዳሬ ሰላሙ ድርድር እንደታየው፣ በአደራዳሪነት እና በዋስትና ሰጪነት የተገኙት የአሜሪካ እና የኖርዌይ መንግሥታት፣ እንዲኹም የኢጋድ ተወካዮች ነበሩ። 

 በሦስት ቀናት ይጠናቀቃል የተባለው የዛንዚባሩ ድርድር፣ ለዘጠኝ ቀናት ተራዝሞ ሚያዝያ 25 ተጠናቀቀ። ንግግሩ ሲገባደድም፣  በቀጣይ  ይካሄዳል ተብሎ ተስፋ በተደረገበት የድርድሩ ቴክኒካዊ አካሄዶች፣  በሦስተኛ ወገን አደራዳሪዎች እና ዋስትና ሰጪዎች መኖር ላይ ከመስማማታቸው ባለፈ፣ ዳግም ለመገናኘትም ቃል ገብተው መለያየታቸው፣ ለተጠባቂው ሰላም ቀብድ ተደርጎ ተቆጠረ። 

ዳር ኤስ ሳላም (የሰላም ስፍራ)

  በዛንዚባሩ የመጀመሪያ ዙር ድርድር ገርበብ ተደርጎ የተተወው የሰላም በር፣ ኹለተኛውን ዙር ድርድር በተስፋ እንዲጠበቅ አድርጎታል። ኹለተኛውን ድርድር የተሳካ እንዲያደርጉት ከቀረቡት ጥያቄዎች አንዱ፣ አገር ቤት የሚገኙት የኦነሠ መሪዎች በድርድሩ በአካል የሚሳተፉበት ኹኔታ እንዲመቻች እንደነበር የዋዜማ ምንጮች ይናገራሉ። በዚኽ መሰረትም፣ በአሜሪካ አመቻችነት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊቱ መሪ ኩምሳ ድሪባ (በጫካ የትግል ስሙ ጃል መሮ) ፤ እንዲሁም  ምክትሉ እና የጉጂው የጦር ክንፍ መሪ ገመቹ ረጋሳ ወደ ዳሬ ሰላም እንዲጓዙ ተፈቅዶ በድርድሩ ተሳትፈዋል። ሆኖም የኦነሠ መሪዎች እና ተስፋ የተጣለባቸው አደራዳሪዎች መገኘት ድርድሩን ውጤታማ አላደረገውም። በዳሬ ሰላሙ ድርድር የአሜሪካ፣ የኖርዌይ፣ እና የኢጋድ ተወካዮች ተሳትፈዋል።

የዳሬ ሰላሙ ድርድር በተጠናቀቀ በሰዓታት ውስጥ፣ ተደራዳሪዎቹ ወገኖች ለድርድሩ መክሸፍ አንዱ ሌላውን አውግዘዋል። በአደራዳሪነትም፣ በታዛቢነትም የተገኙት የአሜሪካው የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመር በቅርቡ ስለድርድሩ ያሉት ግን፣  ለሦስተኛ ጊዜ ወደ ድርድር የመመለስ ጉዳይ አይቀሬ መሆኑን የሚያመላክት ሆኖ ተቆጥሯል። ከሁለት ወር ገደማ በፊት፣ “ኢትዮጵያ-ተስፋ ወይስ የበረታ ስጋት” በሚል ርዕስ ስር፣ በሴኔቱ የውጪ ጉዳይ የአፍሪካ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ ፊት ቀርበው ማብራሪያ የሰጡት ሐመር፣ “በአጭር ጊዜ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት ይቻላል ብሎ መናገር ከባድ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል። ከዚያ ባለፈም፣ “ኹለቱም ወገኖች ለማመቻመች መዘጋጀት አለባቸው”ም ብለው ነበር። ከወዲኽ በኩል የተሰማው የኢጋድ መግለጫም፣ ኹለቱም ወገኖች ዳግም ወደ ድርድር እንዲመጡ የሚያሳስብ ነበር። ይህን ተስፋ እና ጥሪ በቅጡ ለመረዳትም፣ ተደራዳሪዎቹ ታንዛኒያ ላይ ለምን እንደተፋረሱ፣ ከዚያም አልፎ መሬት ያለውን የቡድኖቹ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ሚዛን መከታተልን ይጠይቃል።

ከድርድሩ ጀርባ

በዳሬ ሰላሙ ድርድር ውይይት ስለተደረገባቸው ጉዳዮች አደራዳሪዎቹም ሆኑ ታዛቢዎቹ እስከ አኹን በይፋ ያሉት ነገር የለም። ተደራዳሪዎቹ ግን፣  አንዱ ሌላውን “ከስምምነት የመድረስ ዓላማ አልነበረውም” ሲል አንዱ ሌላውን ይወቅሳል። ለድርድሩ ቅርብ የሆኑ አንድ ምንጭ፣ ኹለት ሳምንት በፈጀው የዳሬ ሰላሙ ድርድር “የጅል ጥያቄ” የሚባሉ ጉዳዮች እንደመደራደሪያ መቅረባቸውን ለዋዜማ አንስተውላታል። 

ኹለት ከፍተኛ የኦነሠ መሪዎች እና ሌሎች የዲያስፖራ ተወካዮች በአካል በተገኙበት ቀረቡ ከተባሉት ጥያቄዎች አንዱ፣ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት (ጨፌ ኦሮሚያ)ን ግማሽ መቀመጫ ያለውድድር እንዲሰጠው የሚጠይቅ ነበር። ዲፕሎማቱ እንደሚሉት፣ ይኽ ጥያቄ የቀረበው መንግሥት የኦነሠ ለሚያቀርባቸው አባላቱ፣ ከወረዳ ጀምሮ እስከ ክልል ካቢኔ ባሉ ቦታዎች ሹመት ለመስጠት እንደሚችል ባቀረበው ሃሳብ ላይ ተጨማሪ ተደርጎ ነው። የኦነሠ ተደራዳሪዎች፣ ተዋጊዎቻቸው ወደ ክልሉ የፖሊስ ኅይል እና የፌደራል መንግሥቱ ጦር ውስጥ እንዲካተቱ ያቀረቡት ጥያቄ የሚጠበቅ ቢሆንም፣ የኦነሠ የተዋጊዎቹን እና የጦር መሣሪያውን ብዛት በታዛቢዎች ፊት የመግለጥን ጉዳይ መቃወሙ፣ ተደራዳሪዎቹን ካላግባቡ ጉዳዮች አንዱ እንደነበር ምንጮች ለዋዜማ ተናግረዋል። 

በኦነሠ በኩል፣ ታጣቂዎቹ ወደ ፖሊስ እና መከላከያ ሲካተቱ የጦር መሣሪያቸውን ሳይፈቱ እንዲገቡ፣ ከፈቱም መሣሪያቸውን ለፌደራሉ መንግሥት ሳይሆን ለሦስተኛ ወገኖች ለማስረከብ የቀረበው መደራደሪያ፣ እጅግ ያልተጠበቀ ቢሆንም በአደራዳሪዎች ግፊት ታጣቂው ኅይል ጥያቄውን ማንሳቱንም ዋዜማ ሰምታለች። 

ኦነሠ፣ በሕዝብ እንደራሴዎቹ ምክር ቤት የተጣለበት የሽብርተኝነት ስያሜ፣ ስምምነት በተፈረመበት ቀን እንዲነሳለት መጠየቁም፣ በዚያ የነበሩት የመንግሥት ተደራዳሪዎች ሊስማሙበት የሚቻላቸው ርዕሰ-ጉዳይ እንዳልነበር ነገሩን በቅርበት የተከታተሉ ምንጭ ለዋዜማ ገልፀዋል።

በኹለተኛው የታንዛኒያው ንግግር ዋዜማ ላይ፣ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ልዑካን ቡድን፣ በአማጺው ቡድን ወታደራዊ አዛዥ  ኩምሳ ድሪባ (ጃል መሮ) እና በምክትላቸው ገመቹ ረጋሳ መሪነት ለንግግሩ ከታንዛኒያዋ ዳሬ ሰላም መግባቱን ቡድኑ ባወጣው መግለጫ አስታውቆ ነበር። ቡድኑ በዚኹ መግለጫው፣ ራሱን “የኦሮሞ ነጻነት ግንባር – የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት” በማለት ነበር የገለጠው። በንግግሩ ዙሪያም አስቀድሞ ለሕዝቡ መረጃ ያልሰጠው፣ የጦር አዛዦቹ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከሚገኙ የውጊያ ቀጠናዎች ወደ ታንዛኒያ በሰላም እስኪደርሱ እንደነበርም በመግለጫው ተመላክቶ ነበር። ለጦርነቱ “ሰላማዊ የፖለቲካ መፍትሄ” ለማፈላለግ ዝግጁነቱን የገለጠው ቡድኑ፣ የዳሬ ሰላሙ ንግግር ሲጠናቀቅ ተጨማሪ መረጃ እንደሚሰጥም ተናግሮ ነበር።

ንግግሩ ከተጠናቀቀ በኋላም፣ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ኹለተኛው ዙር የሰላም ድርድር ያለ ውጤት ለመበተኑ መንግሥትን ተጠያቂ የሚያደርግ መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል። ቡድኑ፣ መንግሥት መሠረታዊ ችግሮችን ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ፣ ብቸኛ ፍላጎቱ አመራሮቼን መመልመል ነበር ሲልም መንግሥትን ወቅሷል። በዛንዚባር እና ዳሬ ሰላም ንግግሮች፣ በኦሮሚያ ክልል መንግስታዊ አወቃቀር ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ የሚያመጡ አካታች ሃሳቦችን አቅርቦ እንደነበር የገለጠው ቡድኑ፣ ኾኖም በመንግሥት ግትርነት ሳቢያ ታሪካዊው አጋጣሚ ተበላሽቷል በማለት መግለጡ ይታወሳል። 

የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት በድርድሩ ጉዳይ ላይ ላነሳናቸው ማብራሪያ የሚፈልጉ ጥያቄዎች ነልስ እንዲሰጠን ለአንድ ወር ያህል ሙከራ ብናደርግም የተለያዩ ምክንያቶች በመደርደር ተገቢ ምላሽ አልሰጠንም። [ዋዜማ]