የግብፅ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች የሳላፊ እስልምና አራማጅ የሆነውንና አክራሪውን አል ኑር ፓርቲ እየተቀላቀሉ ነው። ይህ ለጆሮ እንግዳ የሆነ ነገር የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤክያንን አስቆጥቷል። መዝገቡ ሀይሉ ያሰናዳው ዘገባ የተብራራ መልስ ይዟል፣ አድምጡት።
የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ፓትርያርክ ዳግማዊ ታዋድሮስ የቤተክርስትያኒቱ አባላት የሰለፊ እስልምና አቀንቃኝ በኾነው አል ኑር የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ እንዳይገቡ አገዱ። በፓትርያርኩ ውሳኔ መሰረት “ኮፕት 38” ተብሎ የሚታወቀው ቡድን አባላትም ኾኑ ሌሎች ፓርቲውን የተቀላቀሉ ክርስቲያኖች ከቤተክርስትያኑ አባልነት ይታገዳሉ።
አልኑር የሚባለው የፖለቲካ ፓርቲ የሰለፊ እስልምና አራማጅ እንደኾነ ከመታወቁም በላይ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም በግብጽ ቤተክርስትያን ላይ ተጽእኖ የሚፈጥሩ ፈትዋዎችን ወይም ሐይማኖታዊ ድንጋጌዎችን በማሳለፍ የሚታወቅ ፓርቲ ነበር። ፓርቲው በግልጽም እንደሚናገረው ክርስቲያኖችን እንደአረማዊ ወይም በአረብኛው አጠራር “ካፊር” ናቸው ብሎ የሚያጠራ ፓርቲ ነው። በመኾኑም ክርስትያኖች በማንኛውም ስልጣን ላይ ተመርጠው ወይም ተሾመው በሀላፊነት እንዳይሰሩ የሚያግዱ ድንጋጌዎችን ሲያወጣ ቆይቷል። ይኧው የፖለቲካ ፓርቲ ሴቶችንም በዚሁ ዐይን የሚመለከትና በስልጣን ላይ መቀመጣቸውን የሚኮንን ፓርቲ ነበር።
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ 2014 የወጣው አዲሱ የግብጽ ሕገ መንግስት ግን የፖለቲካ ፓርቲዎች በሐይማኖት ላይ እንዳይመሰረቱ የሚያግድ ከመኾኑም በተጨማሪ ለፓርላማ መቀመጫ የሚወዳደሩ ፓርቲዎች ከንዑሳን የኅብረተሰብ ክፍል በኮታ የተወሰኑ ተመራጮችን እንዲያሳትፉ ያስገድዳል። በዚህም መሰረት ከአገሪቱ የፓርላማ መቀመጫዎች ቢያንስ24ቱ በግብጽ ኦርቶዶክስ ክርስትያኖች እንዲያዝ ከመወሰኑም በተጨማሪ ለሴቶች፣ ለአካል ጉዳተኞች እና ከአገራቸው ውጪ ለሚኖሩ ግብጻውያን የተወሰነ ኮታም አለው። ይህም እነዚህ የኅብረተሰቡ ክፍሎች በሁሉም ፓረቲዎች ውስጥ በኮታው መሰረት እንዲካተቱ የሚያስገድድ አድርጎታል።
ይህን የሕገ መንግስቱን ግዴታ እንደተጫነበት ቀምበር የሚቆጥረው አል ኑር ሳይወድ በግዱ ቀድሞ ያስተላለፋቸውን ፋትዋዎች እንዲጥስ ኾኗል። ይህም ፓርቲው በሩን ለክርስቲያኖች እና ለሴቶች እንዲከፍት አድርጎታል። ይህን የመሰለ አክራሪ ቡድን ከክርስትያኖች መካከል በአባልነት እና በተመራጭነት ሊቀላቀለው የሚፈልግ መኖሩ ግን ብዙዎችን አስገርሟል። አንዳንድ የቤተክርስትያኑ አባላት በሊቢያ በ አይ ኤስ የተሰዉትን ሰማእታት እንደመሳደብ ቢቆጥሩትም ከቤተክርስትያኒቱ ጋር የተኳረፉ ወጣት ክርስትያኖች ማኅበር ከኾነው “ኮፕት 38” ውስጥ የሚቀላቀላቸው አግኝተዋል።
“ኮፕት 38” እንደሌሎች ተመሳሳይ የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ማኅበራት ሁሉ ከግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ጋር የጋብቻና ፍቺን ጉዳይ በተመለከተ የተጋጨ ማኅበር ነው። ይህንንም የቤተክርስትያኒቱን ሕግ ለማለዘብ የሚታገል ቡድን ነው። ለማኅበሩ አባላት በጣም ከባድ የሕይወት ጉዳይ የኾነባቸው ነገር ለክርስትያኖች የፍቺን ፈቃድ የመስጠት ያላት ቤተክርስትያኒቱ ብቻ መኾኗ ነው። በቤተ ክርስትያኒቷ ሕግ ደግሞ ፍቺ የሚፈቀደው በአንድ ምክንያት ብቻ ነው። ይህም ምክንያት ከተጋቢዎቹ አንዱ የሚፈጽመው ለትዳሩ ያለመታመን ነገር ወይም አመንዝራ መኾን ብቻ ነው።
ከዚህ ምክንያት የሚደረግ ፍቺንም ይሁን ከፍቺው በኋላ ለሚደረግ ጋብቻ ቤተክርስትያኒቱ እውቅና አትሰጥም። ለ“ኮፕት 38” ና ሌሎች እርሱን መሰል ማኅበራት ይህ በጣም አሳሳቢ ጉዳይ ነው። ምክንያቱም ብዙ ወጣት ተጋቢዎች በትዳራቸው ላይ እክል ሲያጋጥማቸው ጋብቻቸውን ለመፍታት ያላቸው አማራጭ የእስልምና ሐይማኖትን መቀበል ብቻ ነው። ይህን የመሰለ ለፍቺ ሲባል ሐይማኖትን የመቀየር ጉዳይም እየተበራከተ ነው። “ኮፕት 38” ይህን የመሰሉ 1200 የፍቺ ጉዳዮች እንደምሳሌ ይጠቅሳሉ።
ቤተክርስትያኒቱ አሁን ካላት አቋም የለዘበ ሕግ ያወጣችበት ወቅት ነበር። ምንም እንኳን ብዙም ባይዘልቅም እኤአ በ1938 የወጣው ሕግ በ9 ልዩ ልዩ ምክንያቶች የሚደረጉ ፍቺዎችን ይቀበል ነበር። እነዚህም ምክንያቶች የማይታረቁ አለመግባባቶችን ጨምሮ የግድያ ሙከራን እና በሩካቤ ስጋ አለመጣጣምን የሚያካትት ነበር። ይሁንና ይህ ሕግ እኤአ በ 1942 ተሽሮ አሁን ያለው የጠበቀ የፍቺ ሕግ ተግባራዊ ኾኗል። “ኮፕት 38” የሚባለው ማኅበርም ስሙን የያዘው ከዚሁ የ 1938ቱ ለዘብተኛ የፍቺ ሕግ ጋር ራሱን በማዛመድ ነው። ዓላማውም የ 1938ቱ ሕግ እንዲመለስ መወትወት ነው።
ያም ኾኖ የዚህ ቡድን ውትወታ ከቤተክርስትያኒቱ በኩል ተሰሚነት አላገኘም። ሟቹ ፓትርያርክ ሺኖዳም ኾኑ ተተኪያቸው ታዋድሮስ ይህን የማኅበራቱን ውሳኔ የማይቀበሉ በመኾናቸውም ምክንያት ማኅበራቱ ጉዳያቸውን ለማስፈጸም በፖለቲካው በኩል ተጽእኖ ለማድረግ ሙከራ ሲያደርጉ ቆይተዋል። ለአዲሱ ሕገ መንግስት አርቃቂ ቡድንም ይህ ጉዳይ እንዲታይላቸው ደብዳቤም ልከው ነበር። አሁን ከሰለፊ እምነት አራማጁ ፓርቲ ጋርም የሚያደርጉት ውል ምንም እንኳ ለብዙዎች ካለ እጀታ የመዋደድ ርምጃ ተደርጎ ቢቆጠርም ከዚሁጥረታቸው የመነጨ ነው። ይህን የቤተክርስቲያኒቱንም ስልጣን ለመቀነስም ከአል ኑር የተሻለ ምርጫም እንደሌለ ያስባሉ። ምክንያቱም አል ኑር ከገብጽ ፓርቲዎች ሁሉ የሸሪያ ሕግ የአገሪቱ ብቸኛ ሕግ እንዲኾን የሚሰራ ፓርቲ ስለኾነ ነው።
ሰሞኑን በገብጽ ቤተክርስትያን ውስጥ ያለው ፍጥጫም ቀጥሏል። ፓትርያርክ ታዋድሮስ አል ኑርን በአባልነትም ይሁን በተመራጭነት የተቀላቀሉትን ክርስትያኖች አውግዞ ለመለየት እየተዘጋጁ ነው። ይህ የፓትርያርኩ ውሳኔ ግን ለአንዳንዶች በፖለቲካ ውስጥ ጣልቃ እንደ መግባት እና ማንም ሰው ባመነበት የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ አባል የመኾንን ነጻነት የሚጋፋ ጉዳይ ነው። ቤተ ክርስትያኒቱ ግን ይህን በፖለቲካ ጉዳይ ጣልቃ እንደመግባት አትቆጥረውም። ይልቁንም ርምጃው ከስርአቷ ውጭ የኾኑትን አባላቷን ለማረም እንደሚደረግ ተግሳጽ የሚቆጠር ክርስቲያናዊ ትግባሯ እንደኾነ ትናገራለች።