civil-aviationቻላቸው ታደሰ

ዋዜማ ራዲዮ- መንግስት ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ አየር ክልል ያል ፍቃድ የገቡ 40 የውጭ ሀገር አብራሪዎችን ከ20 ቀላል አውሮፕላኖች ጋር ማክሰኞ ዕለት በቁጥጥር ስር አውሎ ከአራት ቀናት በኋላ አርብ ዕለት መልቀቁን አስታውቋል፡፡ አውሮፕላኖቹ ከሁለት እስከ አራት ሰው የሚይዙ አነስተኛ አውሮፕላኖች ሲሆኑ ዓላማቸውም ቱሪስቶችን ይዘው ከግሪክ ወደ ደቡብ አፍሪካ በርካታ ሀገራትን በአውሮፕላን በማቋረጥ የአየር ላይ ትዕይንት ማሳየት ነው።

መንግስት “ታጋቾች” የሚለውን ቃል ባይጠቀምም አውሮፕላኖቹ ግን ከአራት ቀናት በኋላ ግን ባለፈው አርብ በነጻ ተለቀዋል፡፡ ከታጋቾቹ መካከል እንግዘሊዛዊያን እና አሜሪካዊያን ዜጎች በመኖራቸው ዲፕሎማሲያዊ ጫናው ከፍ በማለቱ በአራት ቀናት ውስጥ ለመለቀቃቸው አስተዋጽዖ ሳያደርግ አልቀረም፡፡ ምናልባትም የአሜሪካ እና እንግሊዝ መንግስታት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወዲህ ዜጎቻቸው ወደ ኢትዮጵያ ከመጓዝ እንዲቆጠቡ ሲመክሩ በመቆየታቸው መንግስት ሌላ አተካሮ መፍጠር የፈለገ አይመስልም፡፡ በሌላ በኩል ግን ኢህአዴግ-መራሹ መንግስት እንዲህ ዓይነት ክስተቶችን ሃያልነቱን ለማሳየት እና ለሉዓላዊነቱ ያለውን ቀናኢነት ለማሳየት እየተጠቀመባቸው ሊሆን እንደሚችልም ግምቶች አሉ፡፡ የአሜሪካ ጸረ-ሽብር ግብረ ሃይል ከድሬዳዋ እስከ ኦጋዴን በረሃ በሚያደርጋቸው ወታደራዊ ቅኝቶች አንዳንዴ ከመንግስት ፍላጎት እና እውቅና ውጭ እንቅስቃሴዎችን እንደሚያደርግ በተለያዩ አጋጣሚዎች ውስጥ አዋቂዎች ሲገለጽ የቆየ ጉዳይ ነው፡፡

ክስተት በቀላሉ ቢፈታም በሀገሪቱ አየር ክልል ጥበቃ እና ተቋማዊነት ላይ ግን አንዳንድ ጥያቄዎችን እንድናነሳ የሚያስገድድ ነው፡፡

ሲቪል አቬሽን ባለስልጣን አውሮፕላኖቹ የአየር ክልል በመጣሳቸው በቁጥጥር ስር እንዳዋላቸው የገለፀው አውሮፕላኖቹ በኢትዮጵያ አየር ክልል ላይ ስለ መጥፋታቸው ዓለም ዓቀፍ መገናኛ ብዙሃን ከዘገቡ ከሁለት ቀናት በኋላ ነው፡፡ መንግስት መግለጫውን ለመስጠት ለምን ከ48 ሰዓት በላይ እንደፈጀበት እስካሁንም መልስ ማግኘት አልተቻለም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ መዘግየት ያልተለመደ በመሆኑ ከተቋማዊ እና ቅንጅታዊ አሰራር ችግር ጋር ሊያያዝ እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡

በ1994 ዓ.ም ሲቪል አቬሽን ባለስልጣን እንደገና የተቋቋመበት አዋጅ ቁጥር 273 በሀገሪቱ አየር ክልል እና በረራ ፍቃድ እና ክልከላ ላይ የተለያዩ መንግስታዊ አካላት ያላቸውን ሃላፊነት ዘርዝሮ ባያስቀምጥም ከሲቪል አቬሽን ሌላ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር፣ ደኅንነት እና መከላከያ ሚንስቴር ቀጥተኛ ድርሻ አላቸው፡፡ በደንብ በአዋጅ ባይደነገግም ለመንግስታዊ በረራዎች ፍቃድ የመስጠትም ሆነ የመከልከል ስልጣን ያለው ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ሲሆን መከላከያ ሚንስቴር ደሞ ወታደራዊ አውሮፕላኖች ጉዳይ ይመለከቱታል፡፡

የዋዜማ ውስጥ አዋቂ ምንጮች እንደሚገልጹት ግን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በሦስቱ መስሪያ ቤቶች ሲሰራበት የነበረው አሰራር በተለምዶ እንጂ ወጥ የሆነ፣ ተቋማዊ ሃላፊነት የሚወሰድበት አልነበረም፡፡ በተለይ መከላከያ ሚንስቴር የጉዳዩን አንገብጋነት የሚመጥን አንዳችም ተቋማዊ አሰራርም ሆነ ለስራው ፍላጎት እንደሌለው ውስጥ ዋቂ ምንጮቹ ይገልፃሉ፡፡ “በመሆኑም” ይላሉ የዋዜማ ምንጮች “…በሦስቱ መስሪያ ቤቶች መካከል ቅንጅታዊ አሰራር እና ተጠያቂነት ያለበት ግልጽ ሃላፊነት በመጥፋቱ ከአየር ክልል መፍቀድ እና መከልከል ጋር በተያያዘ ችግሮች ሲከሰቱ ኖረዋል::” የጋምቤላዎቹ አውሮፕላኖች እገታ ዜና መዘግየትም ከዚሁ ጋር ሊያያዝ እንደሚችል ያሰምሩበታል፡፡ አንድ በውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ስለ ጉዳዩ የሚያውቁ ምንጭ ለዋዜማ እንደነገሩት ከዓመታት በፊት አንድ የአውሮፓዊት ሀገር ኢምባሲ በመቀሌ አካባቢ በበረሃ እባብ ለተነደፈ ዜጋው አስቸኳይ ነፍስ አድን ለማድረግ ከኬንያ አውሮፕላን አስነስቶ በቀጥታ ወደ መቀሌ ለመብረር ቢጠይቅም ቶሎ ፍቃድ የሚሰጠው አካል ጠፍቶ ነበር፡፡ ይህም የሆነው ሰሜኑ ክፍል ከፊል የውሮፕላን በረራ ዕግዳ ስለተጣለበት እና ትክክለኛው ፈቃጅ አካል ማን መሆን እንዳለበት በግልጽ ባለመታወቁ ነው፡፡

ታጋቾቹ አውሮፕላኖቹ ባለፈው አርብ ከእገታ መለቀቃቸውን አስመልክቶ መንግስት የሰጠው ምክንያት ደሞ ግራ አጋቢ ነው፡፡ አውሮፕላኖቹ ጋምቤላ ያረፉት ወደ ኬንያ እና ደቡብ አፍሪካ ለሚያደርጉት ጉዞ ነዳጅለመሙላት እንደነበር ተረጋግጧል ሲሉ ነበር የመንግስት የመንግስት መገናኛ ብዙሃን የዘገቡት፡፡ በሌላ በኩል ደሞ አብራሪዎቹ ዓለም ዓቀፍ ህግን በመጣስ ፈቃድ ሳይሰጣቸው ወደ ኢትዮጵያ አየር ክልል በመግባታቸውምርመራ የተደረገባቸው መሆኑን በመግለጥ ርስበርሱ የሚጋጭ መልዕክት አስተላልፏል፡፡

የሲቪል አቬሽን ባለስልጣን ዳይሬክተሩ ለውጭ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት ቃል “አብራሪዎቹ አየር ክልሉን ማቋረጥ እንደማይችሉ ከተነገራቸው በኋላ ነው ጋምቤላ ያረፉት” ብለዋል፡፡ “አየር ክልሉን ግን ለማቋረጥ ጥያቄ አቅርበው ነበር መሰለኝ” ያሉት ሃላፊው ቦሌ ዓለም ዓቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እንጂ ጋምቤላ ማረፍ እንደማይችሉ እንደተነገራቸው አክለው ገልጸዋል፡፡ ሆኖም ከመንግስታዊ ልዩ በረራዎች ውጭ ላሉ በረራዎች በሙሉ ፍቃድ የሚሰጠው ሲቪል አቬሽን ራሱ ሆኖ ሳለ ሃላፊው “አብራሪዎቹ ፍቃድ አቅርበው ነበር መሰለኝ” ማለታቸው የበረራ ፍቃድ አሰጣጥ ተቋማዊነት ላይ አሁንም ችግሮች እንዳሉ ሊጠቁም ይችላል፡፡ ጎብኝዎችን ለያዙ አነስተኛ አውሮፕላኖች ከሲቪል አቬሽን ውጭ የትኛው አካል ሊመለከተው እንደሚችልም ግለጽ አይደለም፡፡

 

መንግስት አያይዞም አውሮፕላኖቹ ሲቪል በመሆናቸው በሀገሪቱ ላይ የሚያደርሱት አንዳችም ጉዳት እንደሌለ ስለታወቀ መለቀቃቸውን ገልጧል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አባባል ግን ካለፈው የመንግስት ድርጊት ጋር በቀጥታ ይጋጫል፡፡ ለምን ቢሉ መንግስት ከሁለት ዓመት በፊት ሁለት የሱዳን የጦር ሄሊኮፕተሮች በታላቁ ህዳሴ ግድብ አቅጣጫ የኢትዮጵያን አየር ክልል ጥሰው በገቡ በማግሰቱ ለቋቸው ነበር። ወዳጅ ሀገሮችን ጨምሮ በየትኞቹም ሀገራት የሚደረገው ሄሊኮፕተሮቹን ከነአብራሪዎቻቸው አግቶ ጥልቅ ምርመራ ማድረግ ነው፡፡ ቢያንስ ሄሊኮፕተሮቹ ተመርምረው ሲለቀቁ አብራሪዎቻቸው ግን በእገታ ስር መቆየት ነበረባቸው፡፡ መንግስት ግን ከሱዳን አቻው ማብራሪያ ስለመጠየቁ የተሰማ አንዳችም ነገር የለም፡፡

ከሱዳን ድንበር 40 ኪሎሜትር በሚርቀው ታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ‘ግብጽ በሱዳን ወታደራዊ ጣቢያ መገንባት ታስባለች” የሚሉ ወሬዎች በነበሩበት ወቅት ነው እንግዲህ መንግስት ኢህአዴግ-መራሹ መንግስት የጦር ሄሊኮፕተሮቹን በጥድፊያ የለቀቀው፡፡ በጊዜው በድንበሩ አካባቢ ባሉት የሱዳን ግዛቶች ጦርነት ያልነበረ መሆኑ የጦር ሄሊኮፕተሮቹ ለምን ተልዕኮ እንደተሰማሩ ግልጽ ሳይሆን ተድበስብሶ ቀርቷል፡፡ አብራሪዎች ለምን አየር ክልሉን ጥሰው እንደገቡ አንዳችም ምርመራ ስለመደረጉ አልተገለጸም፡፡ ባንጻሩ የተሰጠው መግለጫ ሄሊኮፕተሮቹ አቅጣጫ ስተው በስህተት ወደ ኢትዮጵያ አየር ክልል መግባታቸው ስለተረጋገጠ ተለቀዋል የሚል መሆኑ ብዙዎችን ያስደመመ ነበር፡፡ አንድ ሉዓላዊ አየር ክልል ጎብኝዎችን በያዘ ሲቪል አውሮፕላን ሲጣስ እና በጦር ሄሊኮፕተር ሲጣስ አንድምታው የትየለሌ መሆኑ ግን አያጠያይቅም፡፡

ዓለም ዓቀፉን የሲቪል አቬሽን ድርጅት ያቋቋመው እና የዓለም ዓቀፍ አየር ትራንስፖርት ደንቦችን የደነገገው፣ የቺካጎ ኮንቬሽን ተብሎ የሚታወቀው ዓለም ዓቀፍ የአየር በረራ ኮንቬንሽን የተረቀቀው በ1944 ነበር፡፡ ኢትዮጵያም ከ54ቱ መስራች ሀገራት አንዷ ናት፡፡ በ1994 ዓ.ም ተሻሽሎ በወጣው ሲቪል አቬሽን ባለስልጣን በተቋቋመበት አዋጅ ክልከላዎች እና የአየር ክልል አጠቃቀም በሚለው ክፍል ላይ በሚመለከተው የመንግስት አካል ፍቃድ ወይም በልዩ ስምምነት ካልሆነ በስተቀር ማንኛውም የውጭ መንግስት አውሮፕላን በኢትዮጵያ አየር ክልል ውስጥ መብረር አይችልም የሚል ሀረግ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ የዓለም ዓቀፉ ኮንቬንሽን ድንጋጌም ተመሳሳይ ነው፡፡

ያም ሆኖ የአየር ክልል ጥሰት ግን ላንድ ሀገር በእጅጉ አሳሳቢ የሚሆነው ከሀገር ደኅንነት እና ሉዓላዊነት ጋር የተያያዘ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ሁለት ሀገሮች ወይም አንደኛው ሀገር ጦርነት ላይ ካልሆነ በስተቀር የውጭ ሀገር አውሮፕላን አየር ክልል ጥሶ ገብቷል ብሎ መትቶ መጣልም በዓለም ዓቀፉ ህግ የተለመደ አይደለም፡፡ ምናልባት ችግሮች የሚፈጠሩት አውሮፕላኑ በማይታወቅ ወይም በተከለከለ መስመር ከገባ ነው፡፡ የሰሞኑ አውሮፕላኖች ወደ ኢትዮጵያ አየር ክልል የዘለቁት ግን በሲቪል አቬሽን በተፈቀዱ እና በሚታወቁ ዓለም ዓቀፍ የአውሮፕላን መግቢያ መስመሮች በኩል መሆኑ ጥሰቱን ቀለል ያደርገዋል፡፡

የሉዓላዊ አየር ክልል መከበር ጉዳይ ለሦስቱም የኢትዮጵያ ዘመናዊ መንግስታት ሁሌም አንገብጋቢ የብሄራዊ ደኅንነት ጉዳይ አድርገው ያዩታል፡፡ በዘመነ ኢህደዴግ ጊዜም በሰላም ወቅት ከባድ የአየር ክልል ጥሰቶች ስለማጋጠማቸው ማስረጃ የለም፡፡ በመሰረቱ ኢትዮጵያ በአራቱም አቅጣጫዎች ሉዓላዊ ድንበሯን በአየር በረራ መቆጣጠሪያ ራዳር መከታተል ከሚችሉት ጥቂት የአፍሪካ ሀገራት መካከል እንደሆነች ተደጋግሞ ይነሳል፡፡ በተለይ በሰሜን እና ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች ዘመናዊ ራዳሮች አሏት፡፡ የምስራቁ እና ደቡቡ ክፍሎች ግን ዘመናዊ ራዳር እንዳልተተከለላቸው ባለሙያዎች ይገልጣሉ፡፡ ከነጻ የአፍሪካ ሀገራት ቀዳሚው የሆነው የሲቪል አቬሽን ተቋሟም ባሁኑ ጊዜ ለበርካታ አፍሪካዊያን ሲቪል አቬሽን ባለሙያዎች ጭምር ስልጠና የሚሰጥበት ኮሌጅ ባለቤት ሆኗል፡፡ ባለስልጣኑ የአሜሪካው ፌደራል አቬሽን አስተዳደርን ጨምሮ በስመ ጥር ዓለም ዓቀፍ ገምጋሚዎች ተገምግሞ ዓለም ዓቀፍ ደረጃውን ያገኘ ተቋም መሆኑ ዝነኛ አድርጎታል፡፡

ሲቪል አቬሽን ከተቋቋመበት አዋጅ እና ዝርዝር ደንቦች ሌላ ሚንስትሮች ምክር ቤት እኤአ በ2004 በአዋጅ ቁጥር 432 የአቬሽን ደኅንነት አዋጅን አውጥቶ ስራ ላይ አውሏል፡፡ አዋጁን በዋናነት የማስፈጸም ስልጣን የተሰጠው ለደኅነነቱ መስሪያ ቤት ሲሆን፣ ሲቪል አቬሽን፣ መከላከያ እና ፌደራል ፖሊስም ድርሻ አላቸው፡፡

በጠቅላላው ግን ልፎ አልፎ አንዳንድ ክስተቶች ቢያጋጥሙም ሀገሪቷ በአየር ክልል ጥበቃ፣ በአውሮፕላን ናቭጌሽን ስርዓቷ፣ የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያዋ እና በረራ ደኅንነት በመሳሰሉት ዘርፎች ሀገሪቱ ለዓመታት የገነባችው የሰለጠነ የሰው ሃይል፣ ብቁ ተቋማት እና አሰራሮች ከአህጉሪቷ ግንባር ቀደም ናት፡፡ በጦርነት ጊዜ ካልሆነ በስተቀር አየር ክልሏም ብዙ ጊዜ ሲጣስ አይስተዋልም፡፡ የሱዳን ሄሊኮፕተሮች ከራዳር ውጭ ዝቅ ብለው በመብረር አየር ክልሉን ጥሰው መግባታቸው ንደተጠበቀ ሆኖ ባብዛኛው የሀገሪቱ አየር ክልል ጠንካራ ጥበቃ የሚደረግለት እንደሆነ ወታደራዊ ባለሙያዎች ይስማሙበታል፡፡ በአየር በበረራ ፍቃድ አሰጠጥ እና ክልከላ ዙሪያ ግን የተቋማዊ አሰራር ግድፈቶች የኢህአዴግ-መራሹ መንግስት መለያ ባህሪ መስለው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እንደቀጠሉ ዋዜማ ከውስጥ አዋቂዎች ያገኘቻቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡