PM Abiy Ahmed Economic Affairs Advisor Mamo Mihretu- Credit PM Office

ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ መንግስት እስካሁን ከተቋቋሙ በካፒታል አቅም ግዝፈታቸው ከቀዳሚዎቹ የሚመደብ የመንግስት የልማት ማስፋፊያ (የኢንቨስትመንት ግሩፕ) አቋቋመ። ተቋሙ “የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ግሩፕ” የሚሰኝ ሲሆን የመቋቋሚያ ካፒታሉም 100 ቢሊየን ብር መሆኑን ዋዜማ ራዲዮ ከሁነኛ ምንጮቿ ሰምታለች።

የኢንቨስትመንት ቡድኑን ለማቋቋም የተዘጋጀውን ደንብም ከትላንት በስቲያ ረቡዕ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባደረገው ሶስተኛ መደበኛ ስብሰባው አጽድቆት በነጋሪት ጋዜጣ እንዲታተም መወሰኑ ይፋ መደረጉ የሚታወቅ ነው።  
     
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ግሩፕ ንብረትነቱ ሙሉ በሙሉ የመንግስት መሆኑን እና የመቋቋሚያ ካፒታሉም በጥሬ ገንዘብና በንብረት 100 ቢሊየን ብር እንደሚሆን ዋዜማ ራዲዮ ከምንጮቿ ሰምታለች። 

 የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ግሩፕ በዋነኝነት ሁለት አላማ አለው።ከፍተኛ ጥቅም በሚያስገኙ ዘርፎች ላይ መዋእለ ነዋይ ፈሰስ ማድረግ የመጀመርያ ዓላማው ሲሆን በብዙ ኢኮኖሚያዊ መለኪያዎች ውጤታማ ስራዎችን እንዲያከናውን ይጠበቅበታል።

በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ላይ “የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ግሩፕ በዋናነት በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ በርካታ የመንግስት ሀብቶችን ወደ አንድ ተቋም በመሰብሰብ እና ውጤታማ የኩባንያ አስተዳደር በመፍጠር ከእነዚህ ሀብቶች የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በከፍተኛ ደረጃ በማሻሻልና ሀብቶቹን አሟጦ በመጠቀም የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እድገትና ተወዳዳሪነት በከፍተኛ ደረጃ የሚያሳድግ ስትራቴጂካዊ የልማትና የኢንቨስትመንት መሳሪያ እንደሚሆን” ታሳቢ መደረጉ ተገልጿል ።

የሐብት አስተዳደር ስራም ሌላው የኢንቨስትመንት ግሩፑ ዓላማ ነው።

የኢትዮጵያ መንግስት በዚህ የሐብት መጠን አይሁን እንጂ አምራች ኮርፖሬሽኖችን ከዚህ ቀደምም መስርቶ ያውቃል። በተለይ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣት በፊት ሀገሪቱን ሲያስተዳድር የቆየው ኢህአዴግ በርካታ የልማት ኮርፖሬሽኖችን እንዳቋቋመ ይታወቃል።

የተቋቋሙት ኮርፖሬሽኖች ለዜጎች የስራ እድልን ይፍጠሩ እንጂ የምርታማነት ውጤታቸው እጅግ የወረደ : ከዚያም ሲያልፍ ለከፍተኛ የሀገር ውስጥና የውጭ ዕዳ የተጋለጡ ሆነው ቆይተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ብልጽግና ፓርቲ የሚመራው መንግስት የኢኮኖሚ ማሻሻያ አንዱ ትኩረትም እነዚሁ በዕዳ የተዘፈቁ ኮርፖሬሽኖችን ከዕዳ ነፃ እንዲሆኑና ወደ ትርፋማነት እንዲሸጋገሩ ማስቻል እንደነበር ይታወሳል።

አዲሱ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ግሩፕ በቀጣይ ጥቂት ሳምንታት አመራር እንደሚመደብለት ምንጫችን ነግረውናል። [ዋዜማ ራዲዮ]