የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ትግበራ ወሳኝ የሚባል ምዕራፍ ላይ ደርሷል። በቀጣይ ሳምንታት አደራዳሪዎች የስምምነቱን አፈፃፀም ዕውቅና ሰጥተው ቀሪውን ስራ ለመንግስትና ለሕወሓት የሚተውት ይሆናል። መንግስት ከሚያዚያ አጋማሽ በፊት በስምምነቱ የሚጠበቅበትን ለመፈፀም ጥድፊያ ላይ ነው። የዋዜማን ዘገባ አንብቡት
ዋዜማ- የአፍሪካ ህብረት የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እንዲያበቃ የተፈረመውን የሰላም ስምምነት የመከታተሉን ስራ ከሁለት ሳምንት በኋላ ለፌዴራል መንግስት እና ለሕወሓት ያስረክባል ተብሎ ይጠበቃል
የአፍሪካ ህብረት አደራዳሪ ቡድን በጥቅምት ወር መጨረሻ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እንዲያበቃ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተፈረመውን የሰላም ስምምነት የመከታተሉን ስራ ከሁለት ሳምንታት በኋላ አጠናቆ ለፌዴራል መንግስት እና ለሕወሓት ያስረክባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ዋዜማ ከዲፕሎማቲክ ምንጮቿ ሰምታለች።
በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት አመታት ሕወሓት እና በፌዴራል መንግስት መካከል የተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት በፕሪቶሪያ የፌዴራል መንግስትን በወከሉት ሬድዋን ሁሴን እና ሕወሓትን በወከሉት ጌታቸው ረዳ በተፈረመው የሰላም ስምምነት መቋጫ ማግኘቱ ይታወሳል።
በስምምነቱ መሰረትም መንግስት ለክልሉ የሚያስፈልጉ ሰብአዊ እርዳታዎች እንዲቀርቡ እንደሚያደርግ ፣ ሕወሓትም ትጥቅ እንደሚፈታ እና ለፌዴራል መንግስት እንደሚያስረክብ ፣ የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው አካባቢዎች ጉዳይ በህግ አግባብ እንደሚፈታ፣ እንዲሁም የታጣቂዎች ቀጣይ ህይወት ጉዳይም በተቋቋመው የብሄራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን እንደሚታይና ስምምነቱና በናይሮቢ የተደረሰው የአተገባበር ስምምነት ያብራራል።
የሰላም ስምምነቱ ይዘቶች መፈጸም አለመፈጸማቸውን የአፍሪካ ህብረት ሲከታተል መቆየቱ ይታወቃል። በዚህም መሰረት ከሁለት ሳምንታት በኋላ (ሚያዝያ 15 2015 አ.ም) በሚደረግ መርሀ ግብር አደራዳሪው የአፍሪካ ህብረት ለሰላም ስምምነቱ መፈጸም ለፌዴራል መንግስት እና ህወሀት ዕውቅና በመስጠት ቀጣይ ስራዎችን ለሁለቱ አካላት ያስረክባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ዋዜማ ከምንጮቿ ሰምታለች።
ሆኖም ከፌዴራል መንግስት እና ህወሀት የሰላም ስምምነት አፈጻጸም ጋር በተያያዘ በርካታ ጉድለቶችን የሚያነሱ ጉዳዩም ያሳስበናል የሚሉ ወገኖች አሉ።
በተለይ ለሕወሓት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት የታጠቃቸውን ከባድ መሳርያዎችን በሙሉ አላስረከም በሚል ቅሬታ ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) እና ከአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ጨምሮ ከተለያዩ አካላት ይሰማል። የፌዴራል መንግስትም የአንድ ዙር የመሳርያ ርክክብ ከመፈጸሙ ውጭ በጉዳዩ ላይ የሰጠው ማረጋገጫም ሆነ ማብራሪያ የለም።
በአማራ እና ትግራይ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው እና የጦርነቱም ማዕከል የነበሩት የወልቃይትና ራያ አካባቢዎች ጉዳይ በህግ አግባብ ይፈታል የሚለው የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ክፍል አተገባበር እስካሁን ግልጽ አይደለም።
ሰሞኑን የፌዴራል መንግስት የክልል ልዩ ኀይሎችን (በተለይ የአማራ ክልል ልዩ ኀይልን) ትጥቅ ማስፈታትና ወደ መደበኛ የፀጥታ መዋቅር የማስገባት ዘመቻ የሰላም ስምምነቱን አፈፃፀም ለማፋጠን ያለመ ይሁን አይሁን ዋዜማ ማረጋገጫ አላገኘችም።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን አዲስ አበባ መምጣት በኋላ በሰላም ስምምነት አፈፃፀሙ ላይ ፈጣን ለውጦች ታይተዋል። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕወሓት የሽብርተኝነት ስያሜ መፋቅ ፣ የትግራይ ሸግግር መንግስት መቋቋምና የአቶ ጌታቸው ረዳ የሽግግር መንግስቱን እንዲመሩ መመረጥ ፣ የፌዴራል መንግስት የክልሉን በጀት ለመልቀቅ መወሰን በሁለት ሳምንታት ውስጥ የተፈጸሙ ናቸው።
በመንግስት በኩል በሚቻል ፍጥነት የምዕራባውያን ን ይሁንታ አግኝቶ በጦርነቱ የተቋረጠውን ብድርና ዕርዳታ ማስመለስ አንዱ ግብ መሆኑን የመንግስት ምንጮች ያስረዳሉ። [ዋዜማ]