- በዚህ ወር ለነዳጅ ሲደረግ የቆየው ድጐማ ሙሉ በሙሉ ይነሳል
- ከፈረንጆቹ 2026 መጨረሻ ጀምሮ ብሔራዊ ባንክ ከወርቅ ንግድ ቀስ በቀስ ወጥቶ የግል ባንኮች የወርቅ ንግድ ውስጥ ይገባሉ
- ብሔራዊ ባንክ በዓመታዊ የባንኮች የብድር አቅርቦት ምጣኔ ላይ ጥሎ የነበረውን ገደብ በፈረንጆቹ 2026 ማብቂያ ይነሳል…..
ዋዜማ- የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ አስተዳደር ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ከደረጋቸው ለውጦች አንዱና በተፅዕኖው የበርካታ ዜጎችን ሕይወት የሚነካው የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሀ ግብር ነው። የአለም የገንዘብ ድርጅትን ቅድመ ሁኔታዎች የተከተለውንና መንግስት “ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ” ሲል የጠራው ፕሮግራም በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2019 ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም በትግራዩ ጦርነት ሳቢያ ተጓትቶ የሁለተኛውና “የተሟላ” ነው የተባለው መርሀ ግብር በ2024 (ሐምሌ 2016) ተጀምሯል።
ይህን ማሻሻያ በተመለከተ የአለም የገንዘብ ድርጅት(IMF) ከሰሞኑ በሂደቱ ላይ ጥልቅ ግምገማ አድርጓል። ከኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ጋር በዝግ ባደረገው ውይይት የተነሱ ፍሬ ሐሳቦች፣ የተወሰዱ እርምጃዎችና ወደፊት የተያዙ ዕቅዶች ተዘርዝረዋል። የግምገማውንም ሪፖርት ዘለግ አድርጎ ፅፏል። ዋዜማ ሪፖርቱን ተመልክታ አንኳር ነጥቦችን እንዲህ አሰናድታለች።
የኢትዮጵያን የምጣኔ ሀብት ሽግግር (Reform) ሁለተኛ ምዕራፍን ለመደገፍ ሐምሌ 2016 ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በገባው ውል መሠረት ለውጡ እስካሁን የደረሰበትን ደረጃ የሚዳስስ ሪፖርት ነው ተቋሙ ያወጣው፡፡
በእርግጥ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ‹‹ሀገር በቀል›› ብሎ የሰየመውን ሪፎርም መተግበር የጀመረው በፈረንጆቹ በ2019 ቢሆንም በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ተድበስብሶና ተጓቶ ቆይቶ ነበር፡፡
ከJuly 2024 ጀምሮ ሲተገበር የቆየውም ሁለተኛው ምዕራፍ የ‹‹ሀገር በቀል›› ለውጥ ሙሉ በሙሉ በIMF የተቀረፀው የIMF መዋቅራዊ ሽግግር (Structural Adjustment-SAP) መሆኑ ይታወቃል፡፡
የዚህ ፕሮግራም ዋነኛ አመክንዮ ኢሕአዴግ በተከተለው ‹‹ልማታዊ መንግሥት” የኢኮኖሚ ርዕዮተ ዓለም (Growth model) ምክንያት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ “ለውድቀት ከመዳረጉም አልፎ ወደ ፖለቲካ ውድቀት በማምራት የ2010ሩን የመንግሥት ለውጥ ወልዷል” የሚል ነው፡፡
በመሆኑም፣ ኢሕአዴግ ያደረሰውን “የኢኮኖሚ ስብራት” ለማዳን የእድገት ርዕዮተ ዓለሙ ከመንግሥት – መር ወደ የግል ዘርፍ – መር (Private Sector led) መለወጥ አለበት በማለት፣ የብልጽግና መንግሥት ይህን ከልማታዊ መንግሥትነት ወደ የ‹‹ነፃ ገበያ›› አውድ የሚደረገውን ሽግግር አይ.ኤም.ኤፍ እንዲመራ አዲሱ መንግሥት የተስማማው፡፡
ምሰሶዎቹ
በለውጡ ለማሳካት የታቀዱት ዋና ዋና ምሰሶዎች የእዳ ጫና፣ የኑሮ ውድነት፣ ሥራ አጥነት፣ የበጀት ጉድለትና የውጭ ምንዛሬ እጥረት ይጠቀሳሉ፡፡ በመሠረታዊነት ፖለቲካውንም ፀጥታውንም የሚነካው ይህ ለውጥ፣ በስምምነቱ መሠረት ሽግግሩ የሚጠናቀቀው በአራት ዓመት ጉዞ በ2028 ነው፡፡
ይህንን የአራት ዓመት (48 ወራት) የመዋቅራዊ ሽግግር ለማሳካት 10.6 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል፡፡ ከዚህም ውስጥ፣ 3.4 ቢሊዮን አይ.ኤም.ኤፍ ራሱ፣ 3.7 ቢሊዮን ዶላሩን የዓለም ባንክ፣ እና የቀረው 3.4 ቢሊዮን በእዳ ሽግሽግ እንደሚሸፈን ከስምምነት ተደርሷል፡፡
ሪፖርቱ እንደሚያሳየው ምንም እንኳን የኢትዮጵያ መንግሥት በአይ.ኤም.ኤፍ የተሰጠውን ምክረ ሀሳብ በሙሉ ተግባራዊ ቢያደርግም ውጤቱ ግን ከታሰበው ግብ የራቀ ነው፡፡
በእስካሁኑ የለውጥ ሂደት ምን ውጤት ተገኘ?
የለውጡ የመጀመሪያ እቅድ የእዳ ጫናን መቀነስ ነው፡፡ ሌላኛው በብርና በዶላር (በባንክና በጥቁር ገበያ) መካከል ያለውን የተዛባ ገበያ (distorted market) ማቃናትና የውጭ ምንዛሬ ግኝት ማሻሻል ነው፡፡ ነገር ግን ለውጭ ምንዛሬ ማሻሻያ የተወሰደው እርምጃ የውጭ ዕዳ ጫና ለማቃለል የተያዘውን መንገድ አስተጓጎሎታል፡፡
ሐምሌ 2016 ዓ. ም በተደረገው ገበያ መር የምንዛሪ ለውጥ ምክንያት የአገሪቱ ዕዳ ከጠቅላላ ምርት ያለው ጥምረታ (Debt to GDP) ከ5.4 በመቶ ወደ 50.3 በመቶ ማሻቀቡን ሪፖርቱ ያትታል፡፡
ከዓለም አቀፍ ተበዳሪዎች ጋር ለአምስት ዓመታት ሲደረግ የቆየው ድርድር አሁንም የቀጠለ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ የ1 ቢሊዮን ዩሮቦንድ ድርድር ከዋና የውጭ ዕዳ ተነጥሎ ይታይልኝ ያለችው ጥያቄ ግን የኢትዮጵያን የድርድር ኮሚቴ በሚመሩት ቻይናና ፈረንሳይ ውድቅ መደረጉ ይታወቃል፡፡
የበጀት ጉድለት ስምምነቱ ለውጡ በተጀመረበት ከነበረበት 1.5 ከመቶ ወደ 0.6 ከመቶ ይወርዳል ተብሎ ቢታቀድም፣ በተቃራኒው በእጥፍ አድጐ በ3 በመቶ ላይ ቆሟል፡፡ ለዚህም በዋናነት ለኮሪደር ልማት፣ ለሪዞርትና ለፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኞች በግዴታ የተደረጉ ወጪዎች ምክንያት ሆነዋል፡፡
የኑሮ ውድነት ሦስት እጥፍ ቀንሶ ነጠላ አሃዝ ወይም (9.7 በመቶ) መግባቱ እንደ ትልቅ ስኬት ተቆጥሯል፡፡ ይሁን እንጂ ይሄ አንደኛው ትልቁ ተቃርኖ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ የገንዘብ ሥርጭት በታሪክ ከፍተኛ በሆነበት፣ ምርታማነትና አቅርቦት በወረደበት እንዲሁም የምንዛሬ ለውጥ በተደረገበት ዘመን የኑሮ ውድነት ወርዷል የሚለው መደምደሚያ በሪፖርቱ አጥጋቢ ማብራሪያ አልተሰጠበትም፡፡
በሦስተኛ ደረጃ፣ የመንግሥት ገቢ ማሰባሰብን በተመለከተ፣ IMF ባዘዘው መሠረት መንግሥት ድጐማዎችን በማጠፍ፣ መሠረታዊ የአገልግሎት ታሪፎችን በሒደት ከፍ አድርጓል፡፡ በዚህም መሠረት መንግሥት በነዳጅ፣ ኤሌክትሪክ፣ ቴሌ፣ ማዳበሪያና ሌሎች የሚያደርገውን ድጐማ በማንሳት የመንግሥት ገቢን ሲያሳብጥ የሕዝቡን ኑሮ ግን አጐሳቁሏል፡፡ በዚህም በኑሮ ውድነቱ ምክንያት ከድህነት ወለል በታች የወደቁ ዜጐች ቁጥርና በሴፍቲኔት የሚታቀፉ ዜጐች ቁጥር በከተማና በገጠር በእጥፍ ጨምሯል፡፡
መንግሥት የራሱን ወጪ ለመሸፈን ከሌለው ሕዝብ ለመቁረጥ የዘየደው ከፍተኛ የግብር ምጣኔዎችና አዳዲስ የታክስ አይነቶች የሕዝቡን ገቢ ከማዳከም ባለፈ የንግዱን ማኅበረሰብ ከድጡ ወደ ማጡ አድርሰዋል፡፡
የታክስ ጂዲፒ ጥመርታ አሁን ካለበት 6 ከመቶ የIMF ፕሮግራም በሚያልቅበት በፈረንጆቹ 10.2 ከመቶ ለማድረስ ታቅዷል፡፡ ይህ እንዲሳካም የተለያዩ የታክስ ዓይነትና መጠን እንዲጀመር መንግሥት መስማማቱን የIMF የግምገማ ሪፖርት ይገልጻል፡፡
የገንዘብ ሚንስትሩ አህመድ ሺዴ ለIMF ዋና ዳይሬክተር ባለፈው ወር የጻፉት ደብዳቤም በዚህ የIMF ሰነድ ውስጥ ተካቷል፡፡ ደብዳቤው እንደሚለው መንግሥት ብዙ ዓይነት ታክሶችን ለመጣል እያሰበ ነው፡፡ ከእነዚህም አንዱ የተሽከርካሪ ባለቤትነት ግብር ሪፎርም ነው፡፡ ክልሎችና ፌደራል መንግስት ይኼን ግብር በሚሰበስቡበት ሁኔታ ላይ በቅርቡ በፓርላማ ምክክር እንደሚደረግም ሰነዱ ይገልጻል፡፡ ይህም 0.2 ከመቶ ጂዲፒ ሊሸፍን ይችላል፡፡
የብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ ክምችት ከ3 ቢሊዮን ዶላር ወደ 4.4 ቢሊዮን ማደጉን ሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡ በተለይ ባለፈው ዓመት ወርቅ ወደ 39 ቶን ማደጉና 470 ቶን ቡና መላኩ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ የወርቅ አቅርቦት ባለፈው ዓመት ያሻቀበው በትግራይ ከጦርነቱ ጀምሮ ተከማችቶ የነበረ ነው ሲል የIMF ሪፖርት ያትታል፡፡ ይህም እየቀነሰ ስለሚሄድ በ2018 ዓ.ም. ጠቅላላ የወርቅ አቅርቦቱ ወደ 30 ቶን ይቀንሳል፡፡
የሚወሰዱ አዳዲስ እርምጃዎች
- ብሔራዊ ባንክ ወርቅን በአለማቀፍ የግብይት ዋጋ ላይ 15 ከመቶ እየጨመረ ስለሚገዛ ባንኩ ኪሣራ ውስጥ በመግባቱ በፈረንጆቹ 2026 መጨረሻ ጀምሮ ብሔራዊ ባንክ ከወርቅ ንግድ ቀስ በቀስ ወጥቶ የግል ባንኮች የወርቅ ንግድ ውስጥ እንደሚገቡ ሪፖርቱ ያሳያል፡፡ በዚህም የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ተስማምተዋል፡፡
- ብሔራዊ ባንክ በዓመታዊ የባንኮች የብድር አቅርቦት ምጣኔ ላይ ጥሎ የነበረውን ገደብም በፈረንጆቹ 2026 ማብቂያ እንደሚያነሳ ተገልጿል፡፡ የብድር ገደቡ ከሁለት ዓመታት በፊት 14 ከመቶ የነበረ ሲሆን፣ ከዚያም ወደ 18 ከመቶ አሁን ደግሞ 24 ከመቶ ላይ ቆሟል፡፡ ገደቡ የተቀመጠው የገንዘብ ሥርጭትን ለመቆጣጠርና ግሽበትን ለመቀነስ ቢሆንም የኢንቨስትመንት ፍሰትና ንግድን ማሽመድመዱ ተገልጿል፡፡
- መንግሥት ሲያቀርብ የቆየው የተለያዩ ድጐማዎች ቀስ በቀስ ለማንሳት ከIMF ጋር በገባው ስምምነት መሠረት እያከናወነ ነው፡፡ በዚህ ወር (February 2026) ለነዳጅ ሲደረግ የቆየው ድጐማ ሙሉ በሙሉ ይነሳል፡፡ በየጊዜው ሲደረግ የቆየው የነዳጅ ድጐማ ማንሳት ሲጀመር እስካሁን የዲዝል ድጐማ በ42 ከመቶ የቀነሰ ሲሆን የጋዞሊን ድጐማ ደግሞ በ43 ከመቶ ቀንሷል፡፡ በተመሳሳይ የኤሌክትሪክ ታሪፍም በየጊዜው (Quarterly) እየጨመረ ይቀጥላል፡፡ ለማዳበሪያ የሚደረገው ድጐማም ቀስ በቀስ ይነሳል ይላል ሰነዱ፡፡ የኤሌክትሪክ ታሪፍ ከፍ እየተደረገ ከሄደ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ከድጐማ ውጭ ይሆናል፡፡
- ለኮይሻ የኤሌክትሪክ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ ከሚያስፈልገው የ700 ሚሊዮን ዶላር ውጭ መንግሥት ብድር እንዳይወስድም ገደብ ተጥሏል፡፡ በተለይ የክልል መንግሥታትና የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ብድር እንዳይወስዱ የIMF ሰነድ ያሳስባል፡፡ በዚህም የገንዘብ ሚንስትሩ ተስማምተዋል፡፡
- የቴሌ 40 ከመቶ ሽያጭ፣ የስኳር ፕሮጀክቶች ፕራይቬታይዜሽን፣ የውጭ እርዳታ መቀነስ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት (FDI) መቀዛቀዝና ሌሎችም ጫናዎች ጠቅላላ ከውጭ የሚጠበቅን የገንዘብ ፍሰት ቀንሷል፡፡ ከግጭትና አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ የመንግሥትን ወጪ ሊያበዙና ጫና ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ሪፖርቱ ያትታል፡፡
- የባንክ ዘርፉ ለውጭ መስፈርቱንና የ5 ቢሊዮን ብር ዝቅተኛ ካፒታል ግዴታን በፈረንጆች 2026 መጨረሻ ማሟላት የሚያቅታቸው የአገር ውስጥ ባንኮች እጣ ፈንታቸው ሁለት መሆኑን ሰነዱ ይዘረዝራል፡፡ የመጀመሪያው ደካማ የሆኑ ባንኮች እንዲቀላቀሉ (merger) ሲሆን ሌላኛው መሸጥ (acquisition) ነው፡፡ ለዚህም እንዲረዳ ብሔራዊ ባንክ የmerger & arquisition መመሪያ እያዘጋጀ መሆኑን አቶ አህመድ ሺዴ ለIMF በላኩት ደብዳቤ አረጋግጠዋል፡፡
- ከአበዳሪዎች ጋር ሲደረግ የቆየው ድርድር ከአምስት ዓመታት በኋላም እስካሁን ባለመሳካቱና ባለመጠናቀቁ የኢትዮጵያ ዕዳ ጫና አሁንም አሳሳቢ ነው፡፡ ተጋላጭነቱም ከፍተኛ ነው፡፡ በተለይ በምንዛሪ ለውጡ (currency floating) ምክንያት የመንግሥት ዕዳ በከፍተኛ ሁኔታ ያሻቀበ ሲሆን የዕዳ ጂዲፒ ጥመርታ ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል ውስጥ ከ35.4 በመቶ ወደ 50.3 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡ እስከ ደርግ ውድቀት ድረስ የተወሰዱ 525 ሚሊዮን ዶላር ብድሮችን ሊቢያ፣ ሩሲያ (የቀድሞዋ ሶቪየት)፣ የቀድሞ ዩጐዝላቪያ ይቅር ብለዋል፡፡
- በአማራ፣ ኦሮሚያና ትግራይ ግጭት ሊባባስ እንደሚችልና ኢኮኖሚውን ሊያናጋ የሚችል የምርት እጥረት ሊያስከትል ይችላል ይላል፡፡ ግጭቱን ለማስቀረት መንግሥት በሠላማዊ ንግግር ችግሮችን እንዲፈታና የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትን እንዲረጋገጥ ያሳስባል፡፡በኢትዮጵያና ኤርትራ መካልም ከፍተኛ ግጭት ሊከሰት ስለሚችል መንግሥት የዲሎማሲ ጥረት ከማድረግ ጐን ለጐን ቀጣናዊ መረጋጋት መሥራት እንዳለበት ያስቀምጣል፡፡
የIMF ሰነዱ የዋጋ ግሽበት አሁን ካለበት 17.6 በመቶ በፈረንጆች 2028 ወደ ነጠላ አሃዝ ያወርዳል ሲል መንግሥት ግን አሁን የዋጋ ግሽበት ነጠላ አሃዝ ነው ይላል፡፡
ብሔራዊ ባንክ
ብሔራዊ ባንክ በዚህ ዓመት መጨረሻ በውጭ ምንዛሪና በአስመጪዎች ላይ የሚያደርገውን ማንኛውንም ገደብ ያነሳል ይላል ሰነዱ፡፡
የውጭ ኢንቨስተሮች ከኢትዮጵያ ትርፍና ካፒታል ወደ ውጭ ለመውሰድ ቢፈልጉ (repatriation) የታክስ ክሊራንስ አምጡ የሚባል ገደብ ይነሳል፡፡ አስመጪ ለመሆን የሚጠየቀው የብሔራዊ ባንክ ሰርተፍኬትም ይቀራል፡፡
ላኪዎች ከሚያገኙት ዶላር ግማሹን ለመንግሥት ሰጡ የሚባለው ገደብም ሙሉ በሙሉ ይነሳል፡፡ ብሔራዊ ባንክ በወርቅ ንግድ እንዴት መውጣት እንዳለበት እቅድ ያወጣል፡፡ መንግሥት የብሔራዊ ባንክን ካፒታል በዚህ ዓመት ያሳድጋል፡፡ የፖለቲካ ተሿሚ ያልሆኑ በሙያተኝነት ብቻ የሚታወቁ አራት አባላት የብሔራዊ ባንክ ቦርድ ውስጥ ይመረጣሉ፡፡
ብሔራዊ ባንክ የምንዛሬ ለውጡን ተከትሎ ከገባበት ከፍተኛ ኪሣራ መውጣት አለበት ይላል ሰነዱ፡፡ በቅርቡ ተመልሶ እየሰፋ ያለውን በባንክና በጥቁር ገበያ መካከል ያለውን ልዩነትም ማጥበብ እንዳለበት ያሳስባል፡፡
ሁሉም ባንኮች በየቀኑ የሚያደርጉት የውጭ ምንዛሬ ግብይት በየሳምንቱ መጨረሻ ለአለም የገንዘብ ድርጅት (IMF) በብሔራዊ ባንክ በኩል ይላካል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ (Ethiopia Investment Holdings-EIH)
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ከተቋቋመ እስካሁን የተጠቀለለ የሂሳብ ሪፖርት አቅርቦ ስለማያውቅ ከአንድ ወር በኋላ (March 2026) ሪፖርት ማዘጋጀትና ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡
መንግሥትና አይ.ኤም.ኤፍ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ሪፎርም ለማድረግ በገቡት ስምምነት መሠረት በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ንግድ ባንክ ላይ ጥናት እያደረገ ይገኛል፡፡ የጥናቱ ዓላማም ንግድ ባንክ እንዴት ከመንግሥትና ከሕዝብ ግዴታዎች እንደሚወጣና ሙሉ በሙሉ ትርፋማ ሥራዎች ላይ ብቻ እንደሚያተኩር ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ መንግሥት ከስሩ ካሉት አንዳንድ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የሚወስደውን የትርፍ ድርሻ የሚወስን (dividend policy) አርቅቋል፡፡
ከዚህ በፊት ከስምንት በላይ የስኳር ፕሮጀክቶችን ከመንግሥት ይዞታ ወደ ግል በሽያጭ ለማዞር ተጀምሮ በገዢ መጥፋት ምክንያት ተቋርጦ የነበረው ሥራም አሁን እንደሚቀጥል ሰነዱ ያሳያል፡፡ ለዚህም የስኳር ኢንዱስትሪዎቹ የሀብት ጥናት (asset valuation) ለማድረግ ዝግጅት ተጀምሯል፡፡ ነገር ግን የስኳር ኢንዱስትሪዎቹ ካሉበት አካባቢ አንፃር ያለው የፀጥታ ሁኔታ ካልተሻሻለ አሁንም ፕራይቬታይዜሽኑ ሊሳካ እንደማይችል ሰነዱ ያትታል፡፡
ንግድ ባንክ የመንግሥት የበጀት ጉድለት ለመሙላት በዝቅተኛ ወለድ የሚገዛቸውን የግምጃ ቤት ሰነድና የቦንድ ግዢዎች ቀስ በቀስ ያቆማል፡፡ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሙሉ በሙሉ ትርፋማ ወደሆኑ ሥራዎችና ሌሎች የንግድ ባንኮች የሚሠሩትን ሥራ እንዲሠራ አዲስ ጥናት እየተሠራ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በ2017 ዓ.ም. በምንዛሪ ለውጡ ምክንያት የ208 ቢሊዮን ብር ኪሣራ ደርሶበታል፡፡ በፈረንጆች 2026 የሚንስትሮች ምክር ቤት የድርጅቱን ካፒታል ለማሳደግ ተስማምቷል፡፡ [ዋዜማ]
የአዘጋጁ ማስታወሻ – የዋዜማን ዘገባዎች በመውሰድ የምትጠቀሙ ሌሎች ጋዜጠኞች ፣ የሙያው ስነምግባር በሚጠይቀው መሰረት ዘገባውን ሳታዛቡ እንድታቀርቡና ዋዜማን በምንጭነት እንድትጠቅሱ አደራ እንላለን።
