ዋዜማ ራዲዮ- መቀመጫውን በውጭ ሀገር ያደረገውና በአንጋፋዎቹ የኦሮሞ ብሄርተኞች አቶ ሌንጮ ለታ እና ዶክተር ዲማ ነገዎ የሚመራው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) ከመንግሥት ጋር የፖለቲካ ድርድር መጀመሩን ካሳወቀ ጥቂት ዐመታት ተቆጥረዋል፡፡ ሆኖም ስምምነት ሊደረስ ባለመቻሉ ኦዴግ ነፍጥ ካነሳው አርበኞች ግንቦት-7 ጋር የጋራ ጥምረት እስከ መመስረት ደርሶ ነበር፡፡
የኦዴግ መሪዎች ከአንዴም ሁለቴ ወደ አዲሳባ ተመላልሰው ለኢሕኤግ-መራሹ መንግስት የድርድር ጥያቄ አቅርበውና ከሦስት ዐመታት በፊትም መለስተኛ የድርድር ሙከራ አድርገው ውጤት አላገኙበትም ነበር፡፡ በኢሕአዴግ-መራሹ መንግስት እና በሀገሪቷ አንዳንድ ፖለቲካዊ ለውጦች መከሰታቸውን ተከትሎ በቅርቡ የተደረጉ ውይይቶችና ድርድሮች ግን ፍሬ ማስገኘታቸው ሲገለጽ ሰንብቷል፡፡ ሁለቱም ወገኖች አስተማማኝ ሊባል የሚችል የመጀመሪያ ደረጃ ስምምነት ላይ መድረሳቸውንም ይፋ አድርገዋል፡፡
ድርድር ተቋጭቶ ገና አጠቃላይ ስምምነት ያልተፈረመ ቢሆንም ባሁኑ ወቅት ወደ ስምምነት እንዲዳረሱ ያበቋቸው ምክንያቶች ምንድን ናቸው? ኦዴግ ወደ ሀገር ቤት ተመልሶ ሰላማዊ ትግሉን መቀጠሉስ በኦሮሞ ብሄር እና በሀገሪቱ ፖለቲካ ላይ ምን አንድምታዎች ይኖሩት ይሆን? የሚሉትን ጥያቄዎች በመጠኑ መፈተሸ ተገቢ ይሆናል፡፡ [ተጨማሪ የድምፅ ዘገባ ይመልከቱ አልያም ንባብዎን ይቀጥሉ]
የመጨረሻው ዕድል?
ኢሕአዴግ-መራሹ መንግስት እና በአንጋፋው የኦሮሞ ብሄርተኛ አቶ ሌንጮ ለታ የሚመራው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) ባጭር ጊዜ ተደራድረው ለውጤት መብቃታቸውን እየገለጹ ነው፡፡ በደርድሩም የኦሕዴድ መሪዎች ቅድሚያ ተሳታፊ እንደነበሩ መንግስት ገልጧል፡፡ ሁለቱ ወገኖች እዚህ ውጤት ላይ ሊደርሱ የቻሉት ደሞ በተለይ ባለፉት ጥቂት ወራት በኦሮሞ ብሄር እና ብሄሩ በኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት እና ፖለቲካ ውስጥ ባለውን ሚና ላይ ጉልህ አሻራ ያሳረፉ ፖለቲካዊ ክስተቶች ከመከሰታቸው ጋር የተያያዘ እንደሆነ መናገር ይቻላል፡፡
አንዱ ክስተት በአቶ ለማ መገርሳ የሚመራው አዲሱ የኦሕዴድ እና ኦሮሚያ ክልል አመራር የኦሮሞን ብሄር ከሚወክል በውጭ ካለ ተቃዋሚ ጋር ለመደራደር ፍቃደኛ መሆኑ ነው፡፡ ፌደራል መንግስቱ ሁለት አስቸኳይ ጊዜ አዋጆችን አውጆ ጸጥታ ሃይሉ ማሰማራቱ ለኦሕዴድ በረከተ መርግም ነበር የሆነለት፡፡ ምክንያቱም በኦሮሚያ ክልል ለተደረገው ጅምላ እስር እና የንጹሃን ተቃዋሚ ሰልፈኞች ግድያ ከተጠያቂነት እንዲድን አስችሎታልና፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ሊቀመንበሩ አብይ አሕመድ ጠቅላይ ሚንስትር መሆን መቻላቸው የድርጅቱን ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው የኦሮሞ ብሄርተኞችን ሞራል ከፍ አድርጓል ማለት ይቻላል፡፡ በጠቅላላው ኦሕዴድ በኢሕአዴግ ውስጥ የሃይል ሚዛኑን በአንጻራዊነት ለማጎልበት የቻለ ይመስላል፡፡ ለዚህም ሊሆን ይችላል ውጭ ባሉ ተቃዋዎች ሳይቀር አዲስ ትርክቶቹ እና የሰላም ጥሪው ለጊዜው ተዓማኒ ያገኘለት፡፡ ኦዴግ ሲመኘው የነበረውና ድንገትም ግማሽ ምዕተ ዓመት ያስቆጠረውን ትልሙን የሚያሳካበት የመጨረሻው ዕድል ይመስላል።
ኦህዴድ ተፎካካሪ ወይስ አጋር?
ሌላኛው ክስተት ዋናው ተቃዋሚ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግሬስ አመራሮቹ እነ ዶክተር መረራ ጉዲና እና በቀለ ገርባ ከእስር ከተለቀቁለት ወዲህ ለኦሕዴድ በጎ አመለካከት ማሳደር ብቻ ሳይሆን ውለታ ጭምር የተሰማው ሆኖ መታየቱ ነው፡፡ የኦፌኮው አቶ በቀለ ገርባም ሰሞኑን በሀገረ አሜሪካ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ቃለ ምልልስ የአሁኑ ኦሕዴድ እንደ ጠላት ሳይሆን መልካም ሃሳብ እንዳለው እና ሃላፊነትን መወጣት እንደሚችል ተፎካካሪ ፓርቲ እንደሚያያቸው የገለጡ ሲሆን ይህኑንም በንግግር ብቻ ሳይሆን በተግባርም እያዩት መሆኑን መስክረዋል፡፡
እነዚህ ጉልህ ክስተቶችም በድምሩ ጠለቅ ያለ ፖለቲካዊ አንድምታ ያላቸው ናቸው፡፡ ባንድ በኩል የኦሮሞ ብሄርተኞች በብሄሩ የዴሞክራሲ፣ የእኩልነት፣ የመልካም አስተዳደር፣ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ተጠቃሚነት እና ኦሮምኛ ቋንቋን የፌደራል ቋንቋ ማድረግ በመሳሰሉ አንኳር ጥያቄዎቹ ላይ ከሞላ ጎደል መስማማት ብቻ ሳይሆን ተባብረው ለመስራትም ምቹ ሁኔታ እየፈጠረላቸው ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኦሕዴድ እና በኦፌኮ መካከል ያለው ልዩነት ሳስቷል ማለት ይቻላል፡፡
የክስተቶቹ ሌላኛው አንድምታ ኦሮሞ ብሄርን ከእናት ሀገሩ መገንጠል የሚለው ፖለቲካዊ ግብ የኦሮሞ ብሄርተኝነት መስበኪያ እና የፖለቲካ ማደራጃ ሃሳብ ሆኖ እንዳይቀጥል ጉልህ ተጽዕኖ መፍጠራቸው የማይቀር መሆኑ ነው፡፡ አቶ ሌንጮና ዶክተር ዲማ ነግዎም የኢትዮጵያ ይቅርና የምስራቅ አፍሪካ ክፍለ አህጉር ሕዝቦች በታሪክ፣ ባህል እና ቋንቋ የተሳሰሩ በመሆናቸው ወደ ውሀደት እንጅ ወደመገነጣጠል የሚሄዱበት ዕድል እንደሌለ በመግለጽ ነበር ከእናት ድርጅታቸው ኦነግ የተለዩት፡፡ እናም የአሁኑ የአዴግ ውሳኔ የመገንጠል አላማን ይዞ የሚንገታገተውን ኦነግን ከምንጊዜውም በላይ እንዲገለል ያደርገው ይሆን? ብሎ ማሰብ ይችላል፡፡
በርግጥ አስመራ የመሸጉ የኦነግ መሪዎችም ይህንኑ አዝማሚያ በመገንዘብ ይመስላል ለሁለት ዐመታት የዘለቀውን የኦሮሚያውን ሕዝባዊ አመጽ የሚመራው ድርጅታቸው እንደሆነ መስበክ ጀምረው ነበር፡፡ ዳሩ ሌላው ይቅርና ውጭ ሀገር በርዕዮተ ዐለም ለኦነግ የሚቀርቡ የብሄሩ ብሄርተኞች ሳይቀሩ ሕዝቡ በራሱ እያካሄደው ያለውን መራራ ትግል በዋዛ የመንጠቅ ፖለቲካዊ ብልጣብልትነት እንደሆነ ጠቅሰው ነው ያጣጣሉባቸው፡፡
ባጠቃላይ ኦሕዴድ ከተዘፈቀበት አሳፋሪ ማጥ ማገገም በመጀመሩ፣ ኦፌኮ ደሞ ምንም እንኳ ሕዝባዊ አመጹን ባይመራውም የሕዝቡን ብሶት በቻለመው መጠን በማስተጋባቱ እና ኦዴግም ወደ ሀገር ለመመለስ በመስማማቱ ግንባር ቀደሙ ተጎጅ ኦነግ እንደሚሆን አንድና ሁለት የለውም፡፡
አርበኞች ግንቦት ሰባት ባጣ ቆየኝ?
ሌላው የኦዴግ ወደ ሀገር ቤት መመለስ የሚያስከትለው ተጠባቂ አንድምታ ከኦሮሞ ብሄር ፖለቲካ ወጣ ያለ ነው፡፡ የአቶ ሌንጮ ለታ ኦዴግ ከአርበኞች ግንቦት-7 ጋር ጥምረት ከፈጸመ ገና አንድ ዐመቱ ነው፡፡ ኦዴግ ከአርበኞች ግንቦት-7 ጋር ጥምረቱን ሲፈርም በአርበኞች ግንቦት-7 ሽፋን የሕዝብ ግንኙነት ሥራውን እንዲሰራ እንዲሁም የማይገባውን የገንዘብ እና የፖለቲካ ድጋፍ እንዲያገኝ ከማድረግ ባለፈ ለግንቦት-7 ጠሜታ እንደማይኖረው ያስጠነቀቁ ወገኖች ነበሩ፡፡ አርበኞች ግንቦት-7 ግን ከብሄር ተኮር ደርጅት ጋር ጥምረት መፍጠሩን እንደ ትልቅ ፖለቲካዊ ድል ነበር የቆጠረው፡፡
በርግጥ ኦዴግ ለአርበኞች ግንቦት-7 ያበረከተው ሽምቅ ተዋጊ ሃይል የለም፡፡ እንዲሁ “ኢሕአዴግ-መራሹን መንግስት በማናቸውም ስልት ከሥልጣን እናስወግደው” በሚል የጋራ ጥላ ስር የተስማሙ በመሆናቸው ማለታችን ነው፡፡ እናም የኦዴግ ወደ ሀገር ቤት መመለስ በአርበኞች ግንቦት-7 ላይ የሚኖረው አንድምታ በዋናነት ፖለቲካዊ ነው የሚሆነው፡፡
የኦዴግ አመራሩ ሌንጮ ባቲ ሰሞኑን ሲናገሩ ድርጅታቸው ከአርበኞች ግንቦት-7 ጋር መስራቱን እንደማያቆም ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጅ የመጨረሻውን ስምምነት ከመፈራረማቸው በፊት ግን ሙሉ ፍች እንዲፈጽሙ ሊጠየቁ እንደሚችሉ ነው በስፋት የሚጠበቀው፡፡ ትጥቅ ትግልንም በይፋ ማውገዛቸው አይቀርም፡፡ መሪዎቹም ድሮ የኦነግ ከፍተኛ አመራሮች ሳሉ በአሸባሪነት የተፈረጁበት ወንጀል ሊነሳላቸው የሚችለውም ይህንኑ ቅድመ ሁኔታ ካሟሉ ብቻ እንደሚሆን አንድና ሁለት የለውም፡፡ ምናልባት ኢሕአዴግ በኦዴግ አቀራራቢነት ከአርበኞች ግንቦት 7 ጋር ድርድር ይጀምር እንደሆነም ወደፊት ይታያል፡፡
መንግስት እና ኦዴግ እስከዛሬ ስምምነት ሳይደርሱ ቆይተው አሁን ሊስማሙ የቻሉባቸው ምክንያቶች እንዳሉ ግልጽ ነው፡፡
መንግስት ከኦነግ ጋር ያደረጋቸው ድርድሮች ፍሬያማ አለመሆናቸው አንዱ ምክንያት ነው፡፡ የመንግስት እና ኦነግ ድርድር ደሞ ታሪካዊ ዕዳ የተጫነው እንደነበር ግልጽ ነው፡፡ ምክንያቱም ኦነግ ከሸግግር መንግስቱ ተገፍቶ እንደወጣ ስለሚናገር ለዐመታት በሕወሃት/ኢሕአዴግ ላይ ቂም ቋጥሮ የኖረ ድርጅት ነው፡፡ ይህም ለመተማመን እንቅፋት መሆኑ አልቀረም፡፡ ብዙም አላዋጣውም እንጅ ኦነግ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ማግስት በኤርትራ መጠለያ በማግኘቱ ለተወሰነ ጊዜ በትጥቅ ትግል ላይ ተስፋ ጥሎ እንደነበርም መገመት አያዳግትም፡፡
ኦነግ በሦስት አንጃዎች መከፈሉም ሌላው እንቅፋት ነው፡፡ በተለይ ኦዴግ ከአብራኩ መውጣቱ ለሕወሃት/ኢሕአዴግ ከሰማይ የወረደ መና ነው የሆነለት፡፡ ምንም እንኳ የኦዴግ አመራሮች የኦነግ መሪዎች የነበሩ ቢሆኑም ኦዴግ እንደ ድርጅት ግን የተጠቂነት ስነ ልቦና ሰለባ አይደለም፡፡ እንዲያውም የኢትዮጵያን አንድነት የተቀበለና ወደፊት የሚያይ ፖለቲካዊ አላማ መያዙ ከኦነግ በተለየ ለጊዜው የሚመጥን አድርጎታል፡፡ እናም መንግስት ኦነግን ትቶ ከኦዴግ ጋር ቢደራደር ተጠቃሚ እንደሚሆን ስላሰበ ይሆናል ስምምነቱን የፈለገው፡፡ ኦዴግ አሁን ባለው አቋሙ የመንግስት ስጋት ባልሆነበት ሁኔታ መንግስት ግን ፈጥኖ ወደ ስምምነት መድረሱም ይህንኑ ስሌት ነው የሚያጠናክርልን፡፡
ኦዴግ ህገ መንግስቱን ይቀበላል፣ ታዲያ ከወንበር ውጪ ስለምን ሊደራደር ይችላል?
አሁን መንግስት ወደ ለውጥ እንቅስቃሴ ለመግባት መዘጋጀቱን ኦዴግ ያመነ ስለመሆኑ ከመግለጫው መታዘብ ይቻላል፡፡ እንደ ፖለቲካ ድርጅት መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ እና የወደፊቱንም አስቀድሞ በመተንበይ ሁነኛ ተወናይ ሆኖ ለመቀጠል ሲል ከመንግስት ጋር መስማማት ምትክ የሌለው ፖለቲካዊ ስሌት ሳይሆንለት አልቀረም፡፡ ከእንግዲህ የፖለቲካ ትግል ማካሄድም በኦሮሞ ሕዝብ ውስጥ ተሁኖ ብቻ እንደሆነ አምኗል፡፡ በዚህ ውሳኔው ሳቢያም ምናልባት ከኦነግ ካልሆነ በስተቀር ከደጋፊዎቹና በውጭ ካሉ የብሄሩ መብት ተሟጋቾች የጠነከረ ትችት የሚገጥመው አይመስልም፡፡
መቼም መሪዎቹ አንዴ ሀገር ውስጥ ከገቡ የሚመጣውን ሁሉ ለመቀበል ተዘጋጅተው እንጅ ሁኔታዎች ካልተመቿቸው ድርጅታቸውን ይዘው ዳግም ሊሰደዱ እንደማይሆን መጠበቅ ይቻላል፡፡
ምንም እንኳ የድርድር ጥያቄውን ቀደም ብሎ ያቀረበ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኦሮሞ ብሄር ተቃውሞ መንግስትን ማስጎብደድ መቻሉም የኦዴግ መሪዎች “አሁን ሕዝባችን ስለነቃ የከፋ ነገር ቢመጣብንም ለመንግስት አሳልፎ አይሰጠንም” ወደሚል ድምዳሜ ሳያደርሳቸው አልቀረም፡፡
ሌላው ለስምምነቱ ምቹ ሁኔታ የፈጠረው ኦዴግ ከብሄር ተኮሩ ፌደራላዊ ሥርዓት ጋር ጠብ የሌለው መሆኑ ነው፡፡ እናም የሥርዓቱ መሃንዲስ ሕወሃት “ኦዴግ ለሥርዓቱ አደጋ ይሆናል” የሚል ስጋት እምብዛም አይኖርበትም፡፡ እንዲያውም ስምምነቱ የሕወሃት አንጋፋ መሪዎች በዕድሜ ሳቢያ ከመድረኩ ገለል እያሉ የመሪነቱን ሚና ለኦሕዴድ ከማስረከባቸው ጋር እንደሚያያዝ ቢገመት ከእውነት የራቀ አይሆንም፡፡ ኦዴግን መሳብ ሥርዓቱን ከአንድነት ሃይሎች የሚጠብቅ ጠንካራ የኦሮሞ ብሄርተኛ ሃይል ከወዲሁ ለማደራጀት ይጠቅማቸዋልና፡፡
ኦዴግ ለሕወሃት/ኢሕአዴግ ሁነኛ ስጋት ቢፈጥር እንኳ ኦሕዴድ ቁመናውን እያሻሻለ ከሄደ በነጻ ምርጫ ጭምር ተቀባይነቱን አስጠብቆ እንደሚቀጥል እምነት ተይዞ የተገባበትም ይሆናል፡፡
ኦዴግ ገና ከተመሰረተ አምስት ዐመታት ቢሆነውም መሪዎቹ በብሄሩ ፖለቲካ ግማሽ ክፍለ ዘመን ሙሉ ጥርሳቸውን የነቀሉ መሆናቸው ጠንካራ ጎናቸው ቢሆንም አሁን ኦሕዴድ እና ኦፌኮ ካላቸው አቋም አንጻር ግን የኦሮሞን ሕዝብ ማማለል መቻላቸው ጥርጣሬ ማጫሩ አይቀርም፡፡ በሌላ በኩል መሪዎቹ የኦነግ ከፍተና አመራር ሳሉ ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር ያላወራረዱት ሒሳብ አለባቸው የሚሉ የተቃውሞ ድምጾች አሉባቸው፡፡ በርግጥም ይሄ ዋናው የኦዴግ መሪዎች የፖለቲካ ጠባሳ ሆኖ መቀጠሉ አይቀርም፡፡ ታሪካዊ ቅሬታው ራሱን ኦዴግን፣ ኢሕአዴግን እና በተለይም ኦሕዴድን ምን ያህል ዋጋ እንደሚያስከፍላቸው ግን ከወዲሁ ለመገመት ይከብዳል፡፡ [ተጨማሪ የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ ]
https://youtu.be/ZZWgBm4PuCA