ireecha
ዋዜማ ራዲዮ- ሰሞኑን ኢሕአዴግ-መራሹ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ሽፋን አድርጎ ህዝባዊ አመጹን ከቀለም አብዮት ጋር የሚያገናኝ ትርክት በማምጣት በዴሞክራሲያዊ ማሻሻያ ላይ በተጣለው የተስፋ ጭላንጭል ላይ በረዶ ቸልሶበታል፡፡ ከዐመታት በፊት የሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ቀለም አብዮት ለማስነሳት ምቹ እንዳልሆነ ሲናገር እንዳልነበር እና ላለፉት ሁለት ዐመታት የታየው የሕዘብ አመጽ ዋነኛ ገፊ ምክንያቱ ከውጭ ሳይሆን ከውስጥ ነው የሚለውን አቋሙን እንደገና ቀይሮ ሕዝባዊ አመጹ የውጭ ጠላቶች ስርዓቱን ለማፍረስ የጠነሰሱት ነው የሚል ትርክት ጀምሯል፡፡ ይሄም መንግስት ለአንድ ዐመት ይዞት የቆየውን በህዝባዊ አመጹ ላይ ያለውን አረዳድ ከመሰረቱ የሚቀይር ነው የሚሆነው፡፡ ይኸው የአተያይ ለውጥ ምናልባትም ዕሁድ የሚካሄደው የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ ምን ይዘት እንደሚኖረው ከወዲሁ ጠቋሚ ሆኗል፡፡

መንግስት ይህንን መሰረታዊ የአቋም ለውጥ ያመጣው ሰሞኑን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስት አመጹ የቀለም አብዮት መልክ እየያዘ ነው ሲል መግለጫ መስጠቱን ተከትሎ ነው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስት ሴክረታሪያት በአቶ ሲራጅ ፈጌሳ አማካኝነት በቅርቡ በሰጠው መግለጫ በአንዳንድ አካባቢዎች በተለይም በኦሮሚያ ክልል ከጸጥታ ሃይሎች ጦር መሳሪያ መንጠቅን እና ስልጣን የመፈለግ አዝማሚያ እየታየ በመሆኑ ሁኔታው የቀለም አብዮት መልክ ይዟል በማለት ነው የገለጸው፡፡ የሕወሃት ምክትል ሊቀመንበር እና የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረ ጺዮንም ይህንኑ የሚያጠናክር ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ የውጭ ሃይሎች ወይም ጠላቶች የተባሉት እንደተለመደው ግብጽ እና ኤርትራ ይኑ,ሁኑ ወይንስ ሌሎች መንግስታትን ያካተተ ስለመሆኑ ምንም የተሰጠ ፍንጭ የለም፡፡ [ዝርዝር የድምፅ ዘገባ ከግርጌ ያገኛሉ]

ባለፈው ዐመት ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝን ጨምሮ መንግስት በጠቅላላው ከእንግዲህ በውጭ ሃይሎች እያላከክን መቀጠል አንችልም፤ ህዝባዊ አመጹ ሀገር በቀል ችግር የወለደው ሀገር በቀል እንቅስቃሴ ነው በማለት ሲገልጹ የነበረ ሲሆን ግልጽ ማስረጃም ሆነ መረጃ ያልቀረበበት የሰሞኑ መግለጫ ግን ይህንኑ እምነት እንደገና የሚቀለብስ ሆኗል፡፡ ከእንግዲህ በኋላ የሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት እና ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱን ከውጭ ጠላቶች ጥቃት መመከት አለብኝ፤ ለህዝቡ ጥቄዎች ምላሽ መስጠት እንዳልችል የቀለም አብዮት አራማጅ ሃይሎች አቅጣጫውን ቀይረውብኛል የሚሉ ትርክቶች ናቸው ገናና ነው የሚወጡት፡፡ አሁን መንግስት የቀለም አብዮትን ለሁለተኛ ጊዜ የውስጥ ፖለቲካዊ ችግር ማስተንፈሻ ሊያደርገው መዘጋጀቱን ነው የምንረዳው፡፡

እናም ኢሕአዴግ የቀለም አብዮት ትርክትን አሁን ለምን አመጣው? ለመሆኑ ህዝባዊ አመጹ ከቀለም አብዮት ጋር የሚያገናኘው ባህሪ አለው ወይ? ከዚህ በኋላስ መንግስት ምን አይነት የፖለቲካ አቅጣጫ ሊከተል ይችላል? የሚሉት ጥያቄዎች መሰረታዊ ሆነው ብቅ ብለዋል፡፡

የሰሞኑ የቀለም አብዮት ትርክት የተሰማው ሦስት መሰረታዊ ክስተቶችን ታክኮ ነው ማለት ይቻላል፡፡ አንደኛው፣ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከውስጥም ሆነ ከውጭ ጠንከር ያለ ተቃውሞ የገጠመው መሆኑንና በፓርላማውም በከፍተኛ ተቃውሞ እና በአዋዛጋቢ ሆኔታ ታጅቦም ቢሆን መጽደቁ መነገሩን ተከትሎ መሆኑ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ባለፉት ጥቀቂት ቀናት በኦሮሚያ በርካታ ከተሞች አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመጣስ ከቤት የመቀመጥ እና ንግድ ቤቶችንና አውራ መንገዶችን የመዝጋት አድማ እየተካሄደ ባለበት ወቅት ነው፡፡ እንዲሁም በሶስተኛ ደረጃ መታየት የሚገባው ፍረጃው በሀገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር እውን እንዲሆን የራሱ የመንግስት አጋር ከሆኑት ምዕራባዊያን መንግስታት ግፊቱ እየጠነከረ ባለበት እና መንግስታቱም አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በተቃወሙበት ማግስት መምጣቱ ነው፡፡

ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጅ በኋላ ባሉት ቀናት የታዩት ተቃውሞዎች ቤት ውስጥ የመዋል፣ የንግድ አገልግሎቶችን እና አውራ ጎዳናዎችን መዝጋት የመሳሰሉ ሲሆኑ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጁ በፊት ጭምር የነበሩ ናቸው፡፡ ታዲያ በድንገት እንዴት የቀለም አብዮት ይዘት እንደያዙ ግራ አጋቢ ነው የሆነው፡፡ እናም ከኢሕአዴግ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርህ በማፈንገጥ የፌደራል ስልጣንን መያዝ እንደሚፈልግ በይፋ የተናገረው ደሞ ኦሕዴድ ብቻ ስለሆነ መንግስት በአዋጁ ሽፋን በሰላማዊ እና ሕጋዊ መድረክ ለተንጸባረቀው የኦሕዴድ አቋም ሕገ ወጥ መልክ ለመስጠት ያሰፈሰፈ ነው የሚመስለው፡፡

ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ባሻገር የቀለም አብዮት ፍረጃው የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሬክስ ቲለርሰን አዲሳባ ሊገቡ አንድ ቀን ሲቀራቸው መሰማቱ አዋጁን ጠንከር ባለ መግለጫ ለተቃወመው የአሜሬካ መንግስት ዲፕሎማሲያዊ ምላሽ ለመስጠት ታስቦ ሊሆን እንደሚችልም መገመት ይቻላል፡፡ አውሮፓዊያኑ እንግሊዝ፣ ስዊድን እና ጀርመንም የአሜሪካን ያህል የከረረ ባይሆንም አዋጁን እየተቹ ጎን ለጎን ደሞ መንግስት ሁሉን ዐቀፍ ለሆነ ፖለቲካዊ ውይይት በሩን እንዲከፍት በመጎትጎት ስለተጠመዱ “ሰላማዊ ህዝባዊ አመጽ” የሚባለው ነገር በውጭ ሃይሎች ግፊት ሕገ መንግስታዊ ስልጣንን በሃይል ወደመንጠቅ መለወጡን በመስበክ ዲፕሎማቶችን የማስበርገግ ስልት እንደሆነ ነው የሚታመነው፡፡

በምስራቅ አውሮፓ የታዩት የቀለም አብዮቶች በጠቅላላው የውጭ መንግስታት ጥቅሞች፣ የርዕዮተ ዐለም ልዩነት፣ ህዝባዊ አመጽ፣ የወጣት አደረጃጀቶች፣ ርዕዮት አራማጅ የሆኑ ድንበር ዘለል ዐለም ዐቀፍ ድርጅቶች፣ ግዙፍ የውጭ ገንዘብ ድጋፍ፣ የውስጥና የውጭ መገናኛ ብዙሃን የጋራ ጥምረት የመሳሰሉ ይዘቶችን አጣምሮ የያዘ ነበር፡፡ አሁን የእኛ ሀገር ሕዝባዊ ተቃውሞ ከላይ ከገለጽናቸው የቀለም አብዮት ባህሪያት የትኛውን ባህሪ እንደሚያሟላ በግልጽ የተገለጸ ነገር የለም፡፡

ከዚህ አንጻር ምናልባት መንግስት ከምዕራባዊያን አጋሮቹ የሚመጣበትን የዴሞክራሲያዊ ሽግግር ግፊት ላለመቀበል ከፈለገ ነገሩን ከርዕዮተ ዐለም ወይም ከድንበር ዘለል ዐለም ዐቀፍ ተቋማት አንጻር ሊቃኘው ያስብ ይሆናል፡፡ በዚህም የኒዮ ሊበራል ሃይሎች የራሳቸውን ዲሞክራሲ በሃይል ለመጫን ሲሉ ወይም አንጡራ ሃብታችን ለመቀራመት ሲሉ በልማታዊ እና አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመራችን ላይ የቃጡብን ሴራ ነው የሚል ትርክት ይዞ ብቅ ሊል ይችላል፡፡ በሺህዎች የሚቆጠሩ ድሃ ገበሬዎችን ከቀያቸው እያፈናቀለ ሰፋፊ ለም መሬቶችን ለውጭ ኩባንያዎች በርካሽ የቸበቸበ መንግስት እንደምን በጥቅምና ርዕዮተ ዐለም የተቃኘ የቀለም አብዮት ስጋት ሊያድርበት ይችላል? የሚለው ጥያቄ ግራ አጋቢ የሚሆነውም ለዚህ ነው፡፡

ምናልባት ግብጽን እና ኤርትራ ላይ የሚንጠለጠል ከሆነም የጅኦፖለቲካ ጥቅም ያላቸው ሃይሎች ሀገሪቱን ለማዳከም እና ህገ መንግስታዊ ሥርዓቷን በማፍረስ ሥርዓት አልበኝነትን ለማስፈን የህዝባችን ፍትሃዊ ጥያቄ ቀልብሰውታል ከሚል የሚያልፍ እንዳልሆነ መናገር ይቻላል፡፡

ቀለም አብዮት የሚባለው ጽንሰ ሃሳብ በዋናነት በፖለቲካ መዝገበ ቃላት ጥቅም ላይ የዋለው ከ15 ዐመታት በፊት በምስራቅ አውሮፓ ሀገራት ስልጣን ላይ የነበሩ የፖለቲካ ልሂቃንን በተደራጀ በሰላማዊ ሕዝባዊ አመጽ በተለይም ምርጫን ተገን በማድረግ ከስልጣን ለማስወገድ የተደረገውን ሙከራ ለመግለጽ ነበር፡፡ አላማውም የሥርዓት ለውጥ ሳይሆን የፖለቲካ ልሂቃንን በመለወጥ ላይ ብቻ ያተኮረ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ አሁን ኢሕአዴግ ትርክቱን ያመጣው ግን የህዝቡ ጥያቄ ከመንግስት ለውጥ አልፎ የሥርዓት ለውጥ መሆን ከጀመረ በኋላ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይህም ርስበርሱ ይጋጫል፡፡

ቀለም አብዮቶች ባብዛኛው ምርጫን ተገን አድርገው የሚነሱ ሰላማዊ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ሲሆኑ ሕአዴግ ግን በህገ መንግስታዊ ሥርዓቱ፣ በጸጥታ ሃይሎች፣ በልማት ተቋማት እና ንጹሃን ዜጎች ላይ በጦር መሳሪያ የተደገፈ ጥቃት እየተደረገ መሆኑን ሲሰብክ ነው የኖረው፡፡ ይህም ከቀለም አብዮት ባህሪ ጋር የሚጣጣም ትርክት አይደለም፡፡

የቀለም አብዮት አንዱ ገጽታ የወጣት አደረጃጀቶች ዋነኛ የሰላማዊ ተቃውሞ እና አድማ ተወናይ መሆናቸው እንደሆነ ብዙ የተባለበት ሲሆን በሀገራችን በሚታየው ሕዝባዊ ቀቃውሞም ግንባር ቀደሙ ሃይል ወጣቱ ሆኖ ነው የተገኘው፡፡ ያም ሆኖ የኢሕአዴግ መንግስት በተለምዶ ቄሮ ስለሚባለው የኦሮሚያ ክልል ወጣቶች ተቃውሞ አደረጃጀት፣ አላማ እና የውስጥና የውጭ ግንኙነት መረብ ያለው ስለመሆኑ እና አለመሆኑ ምንም የገለጸው ነገር የለም፡፡ ምናልባትም ግልጽ መረጃ ያለውም አይመስልም፡፡ የእስካኑ የህዝቡ በተለይም የወጣቱ ተቃውሞ ግን ሀገር በቀል እንጅ ከውስጥም ሆነ ከውጭ ጠንካራ መረብ የዘረጋ መሆኑን የሚያሳይ ፍንጭ የለም፡፡ በርግጥ የሰሞኑ የመንግስት ትርክት በተቃውሞው ተሳታፊዎች ላይ በተለይም በኦሮሚያ ክልል መጠነ-ሰፊ ዘመቻ በማድረግ ስረ መሰረቱን ለማወቅና ሙሉ በሙሉ የተቃውሞ መዋቅሩን ከስሩ ለመመንገል መቁረጡን የሚጠቁም ነው፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ለቀለም እና ለዐረቡ ዐለም የጸደይ አብዮቶች እርሾ የነበሩት ማህበራዊ ሜዲያዎች ተደራሽነም በኢትዮጵያ በጣም ውስን መሆኑ እንደተበቀ ሆኖ መንግስት እንዳሻው ሲዘጋቸው ስለኖረ ዋነኛ የተቃውሞ አሳላጭ መሳሪያ ናቸው ማለት አይቻልም፡፡

በምስራቅ አውሮፓ እንደታየው ለዲሞክራሲ እድገት የሚውል ግዙፍ የገንዘብ ዕርዳታ ከውጭ መንግስታትና ድርጅቶች የሚቀበሉ ሲቪክ ማህበራት አሉ እንዳይባል ደሞ የሲቪል ማህበራት ሕጉ ይህን አይነቱን ነገር ከከለከለ ዐመታት ተቆጥረዋልል፡፡ እንዲያውም በተቃራኒው የአሜሪካውን ዩኤስአይዲ ጨምሮ የምዕራባዊያኑ ገንዘብ ዕርዳታ ወደ መንግስት ተቋማት ካዝና ነው ሲፈስ የኖረው፡፡ በቀዳሚነት በቀለም አብዮት እጃቸው እንዳለበት የሚነገርላቸው እንደ National Endowment for Democracy and Open Society Institute የመሳሰሉት የምዕራባዊያን ተቋማት እንኳ በኢትዮጵያ ምንም እንቅስቃሴ የላቸውም፡፡

ባጭሩ ህዝባዊ አመጽ ከመኖሩ እና ወጣቶች በግንባር ቀደምትነት ተወናይ ከመሆናቸው በስተቀር በኦሮሚያና አማራ ክልል እየታየ ያለውን ጸረ-መንግስት ተቃውሞ ከቀለም አብዮት ለመፈረጅ የሚያበቃ ውስጣዊና ውጫዊ ሁኔታ የለም፡፡ እናም አዲሱ ትርክት የመጣው ለገሪቱ ፖለቲካዊ ቀውስ ውጫዊ ገጽታ በመስጠት ጥያቄዎችን ለማፈን፣ ዴሞክራሲያዊ ምዳሩን ዘግቶ ለማቆየት እና ከምዕራባዊያን የሚሰነዘረውን ግፊት በሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት ስም ለማክሸፍ መወሰኑን ነው የሚጠቁመን፡፡ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ለዚሁ አላማ ሲባል እንደወጣ ግልጽ የሚያደርግ አካሄድ ነው፡፡

በዚህ አተያይ መሰረት ከዚህ በኋላ የህዝብ ጥያቄ የሚባው ነገር ከሥራ አጥነት፣ ከፍትሃዊ ሃብት ክፍፍል፣ ከዴሞክራሲና መብት ጥያቄዎች ጋር መገናኘቱ ቀርቶ በምትኩ ከመንግስት የሚሰማው ትርክት የመንግስት ስልጣንን በአመጽ የመንጠቅ፣ ሀገሪቱን የማፈራረስ እና ለውጭ መንግስታት ብዝበዛ የተመቸ ደካማ ወይም አጎብዳጅ መንግስት ለመፍጠር ያለመ ሴራ እየተካሄደ መሆኑን የሚያቀነቅን ትርክት ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ ይህም ተቃውሞውን እና የሀገሪቱን ፖለቲካዊ ቀውስ ያባብሰው እንደሆነ እንጅ ሌላ ውጤት እንደማይኖረው አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመጣስ እየተደረገ ያለው ተቃውሞ በቂ ማስረጃ ይሆናል ማለት ይቻላል፡፡[ዝርዝር የድምፅ ዘገባ ከግርጌ ያገኛሉ]

https://youtu.be/J4RnXJumz7M