ዋዜማ- የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ፖለቲካ ፓርቲዎችና እጩዎቻቸው፣ እንዲሁም የግል እጩዎች የሚመሩበትን የምርጫ ስነምግባር ደንብ አውጥቷል፡፡ ፖለቲካ ፓርቲዎች አስገዳጅነት ያለውን የቦርዱን የምርጫ ስነ ምግባር ደንብ ፈርመው የተቀበሉ ሲሆን፣ የደንቡን ድንጋጌዎች ከጣሱ ቅጣት ይጠብቃቸዋል፡፡

በሰባት ምዕራፎችና በ30 አንቀጾች የተደራጀው “የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ማስፈጸሚያ የሥነምግባር ስርዓት” ደንብ የካቲት 14፣ 2018 ዓ፣ም በፓርቲዎች ተፈርሟል፡፡ የደንቡ ተፈጻሚነት ወሰን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወይም ለክልል ምክር ቤቶች፣ የፓርቲ እና የግል እጩ ተወዳዳሪዎች ላይ “ሁሉ” ተፈጻሚ ይሆናል ፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የፓርቲና የግል እጩ አጠቃላይ ግዴታዎች

  • የሕገ መንግሥት፣ የምርጫ ነክ ሕጎች አዋጆችን፣ መመሪያዎችን፣ እንዲሁም የቦርዱን ውሳኔዎችና ትዕዛዞች ሙሉ በሙሉ ማወቅና ማክበር
  • በፆታ፣ በዕድሜ፣ በሃይማኖት፣ በአካል ጉዳት፣ በፖለቲካ አቋም ወይም በመሰል ጉዳዮች ላይ ሣይመሰረቱ ሁሉንምሰው እኩል ማክበር
  • በምረጡን ዘመቻ ወቅት፣ ድምፅ በመስጠት ሂደት ፆታዊ ትንኮሳም ሆነ ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃት ከመፈጸም መቆጠብ
  • በመራጮች፣ በምርጫ አስፈፃሚዎች፣ ቅሬታ ሰሚ ሚቴ አባላት፣ እጩ ተወዳዳሪዎች፣ የሰብዓዊ መብት ክትትል ባለሙያዎች፣ የመናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች፣ የሲሺል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና የምርጫ ታዛቢዎች ላይ ምንም አይነት አሉታዊ ጫና ተፅእኖ ከማሳደር የመቆጠብ
  • ማንኛውም ምርጫ ለመወዳደር የተመዘገበ የፖለቲካ ፓርቲ ኃላፊዎቹ፣ እጩዎቹ፣ አባላቱና ደጋፊዎቹ መቼም፤ ማንንም ማስፈራራት እንደሌለባቸው በግልጽ የሚከለከል መመሪያ የማውጣት
  • ማንኛውም ፓርቲ በአባሉ፣ ባቀረባቸው እጩዎች ወይም በመሪው የተፈጸመን የአመፅ ድርጊት ወይም ለአመፅ የሚጋብዝ ተግባር በይፋ የማውገዝ
  • የሥነ ምግባር ድንጋጌዎቹን የማስተዋወቅና ሕገ ወጥ ድርጊቶችን የማውገዝ
  • በምርጫው ሂደት አውድ ውስጥ የቦርዱን ሠራተኞች፣ ታዘቢዎችንና መራጮችን ከማባበል፣ ዛቻ ከመሰንዘር፣ ከማስፈራራት፣ ከማስጨነቅ፣ ወደ ራስ ፍላጉት ከመጠምዘዝ ወይም በጉቦ ከመደለል ድርጊት የመቆጠብ እና መሰል ድርጊቶችን ለቦርዱ የማሳወቅ
  • ሁሉም ፈቃድ የተሰጣቸውን ታዛቢዎች፣ የሰብዓዊ መብት ክትትል ባለሙያዎች፣የመገናኛ ብዙሃን፣ እንደዚሁም የዕጩ ተወዳዳሪ ወኪሎች በመመሪያዎች፣ በትዕዛዞችና የአሠራር ሥነርዓቶች መሠረት የምርጫ ሂደቱን በነፃነት የመጎብኘትና የመታዘብ መብታቸውን የማክበር ግዴታ ተጥሎባቸዋል

የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ክልከላዎች

  • በማንኛውም ዓይነት ሃሳብ ምንም አይነት መደለያ ወይም ጉቦ ከመስጠት ፣ ኃይል ከመጠቀም ወይም በማንኛውም ዓይነት ድርጊት እጩ ተወዳዳሪዎችን ዕጩ ሆነው እንዲቀርቡ ወይም እንዳይቀርቡ፣ ከእጩ ተወዳዳሪነት እንዲወጡ ወይም እንዳይወጡ ማድረግ
  • ሥልጣንን መከታ በማድረግ መደለያ ወይም ቅጣት ወይም ሌላ የማስፈራሪያዘ ዘዴ መጠቀም
  • የምርጫ ዘመቻውን ሰላም የሚያናጋ ወይም ግጭት የሚቀሰቀስ፣ አመፅ የሚጋብዝ ወይም ስጋት የሚፈጥር ንግግር ማድረግ
  • ለምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ማንኛውም የአዳራሽ ስብሰባ፣ የአደባባይ ስብሰባ እና ሰልፎች እቅድ ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ
  • ሌሎች ፖለቲካ ፓርቲዎች ሀሳባቸውን በነጻነት አንዳያሰራጩ ስጋት እና ፍርሐት መፍጠር 
  • በማንኛውም ሁኔታ የሌሎች ፖለቲካ ፓርቲዎችን እና የግል እጩዎችን፣ እንዲሁም የመራጩን ሕዝብ እንቅስቃሴ ማደናቀፍ ወይም ማወክ
  • የሌሎች ፓርቲዎች ወይም እጩ ተወዳዳሪዎች የምርጫ ዘመቻ እንዲስተጓጎል፣ እንዲበላሽ፣ እንዲዳክም ወይም እንዲቋረጥ ማድረግ
  • በማንኛውም ዓይነት ድርጊት የፓርቲዎች እና እጩዎችን የምርጫ እንቅስቃሴ ማደናቀፍ
  • የፓርቲዎችን ልሳን፣ የምርጫ ማስታወቂያ፣ በራሪ ጽሑፍ ወይም ፖስተር አንዳይሰራጭ፣ እንዳይለጠፍ፣ አንዳይታይ፣ እንዲበላሽ ማወክ ወይም ማበላሽት
  • በይፋም ይሁን በስወር አመጽ አመፅን የሚቀስቅስ ይዘት ያለው በራሪ ወረቀት፣ የዜና መጽሔት ወይም ፓስተር ማሰራጨት
  • ከመራጮች ድምፅ ለማግኘት ማንኛውንም ዓይነት መደለያ መስጠት
  • ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታቻ የሆኑ ህጻናትን የምርጫ ቅስቀሳ ልብስ ማልበለስ፣ ፖስተር መስያዝ፣ በራሪ ወረቀቶች መስበተን፣ በምርጫ ቅስቀሳ ስብሰባና ሕዝባዊ ሰልፍ እንዲገኙ ማድረግ
  • ለምርጫ ቅስቀሳ በሚጠሩ ሕዝባዊ ስብሰባዎች፣ በምርጫ ወይም ድምጽ መስጫ 500 ሜትር ዙሪያ የጦር መሳሪያ ወይም ማንኛውም ጉዳት ሊያደረስ የሚችል ነገር ይዞ መገኘት የተከለከለ ነው

የጥሞና ጊዜ ክልከላዎች

  • ማንኛውም የምረጡን ዘመቻ ማድረግ
  • የምርጫ ቅስቀሳ ባህሪ ያላቸውን የአዲስ ፕሮጀክቶች የመሠረት ድንጋይ ማስቀመጥ፣ አዳዲስ ፕሮጀክቶች መቋቋማቸው መግለጽ፣ ማስመረቅና መሰል ድርጊቶች መፈጸም በጥብቅ የተከለኩ ናቸው 

ድምጽ መስጠት እና ቆጠራ ሂደት ክልከላዎች

  • በድምጽ አሰጣጡ ወይም በቆጠራው ጣልቃ መግባት ወይም በማንኛውም መልኩ ሂደቱን ማወክ 
  • ኃይል በመጠቀም፤ መደለያ በመስጠት ወይም በሌላ በማንኛውም አድራጎት መራጩ ሕዝብ ለአንድ ፓርቲ ወይም እጩ ድምጽ እንዲሰጥ ወይም እንዳይሰጥ ወይም ከመስጠት እንዲታቀብ ማድረግ
  • የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ሚስጥራዊነትን አልጠበቀም የሚል የሀሰት መረጃ መስጠት
  • ከቦርዱ ፍቃድ ያገኙ ጋዜጠኞችን፣ ታዛቢዎች፣ የፓርቲው ወኪሎች፣ የእጩ ወኪሎች ድምጽ አሰጣጥና ቆጠራ የመከታተል  የመከታተል መብታቸውን መገደብ
  • መራጮችች ድምፅ እንዲሰጡ በማንኛውም ዓይነት መንገድ መደለል፣ መገፋፋት ወይም ማስፈራራት
  • የምርጫ ውጤትን በተመለከተ ትንበያ መስራት እና ይፋ ማድረግ
  • ቦርዱ አረጋግጦ ይፋ የሚያደርገውን የምርጫ ውጤት የመቀበል፣ በውጤቱ ቅሬታ ካለ በሕግ አግባብ የመጠየቅ

የደንቡን ድንጋጌዎች ያላበረ ፓርቲ እና እጩ ላይ የሚጣል ቅጣት

  • በሌሎች አግባብነት ያላቸው ሕጎች የተደነገጉ እንደተጠበቆ ሆኖ የሥነ ምግባር ደንቡን ተካልፎ የተገኘ ማንኛውም፣ በምርጫው ለመወዳደር የተመዘገበ ፓርቲ፣ የፓርቲ ወይም የግል እጩ  ቦርድ ቅጣት ይጣልበታል (ስለ ቅጣት በደንቡ ላይ የተገለጸ ዝርዝር የለም)
  • በደንቡ ድንጋጌ ላይ ጥሰት ፈጽሞ ቅጣት የተላለፈበት አካል በቦርዱ ውሳኔ ቅር ከተሰኘ ፍርድ ቤት ይግባኝ የማለት መብት ተሰጥቶታል፡፡ [ዋዜማ]