ዋዜማ ራዲዮ- የህዳሴ ግድብ ውሀ የሚተኛበት ቦታ ላይ ያለው የደን ምንጣሮ ስራ ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ተነጥቆ ለአማራ እና ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ወጣቶች ሊሰጥ ነው።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሀይል እንዲያመነጭ የሚያስፈልገው ቦታ ወደሁዋላ 246 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚተኛ ሲሆን በጥቅሉ ደን የሚመነጠርበት ስፋት 180 ሺህ ሄክታር ስኩዌር ያህል ነው ።ይህን ደን የመመንጠር ስራ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ከአራት አመት በፊት ለብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ሰጥቶት እንደነበር ይታወቃል።ለስራው ቅድመ ክፍያም ሜቴክ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል 2.7 ቢሊየን ብር ተከፍሎታል።
ሆኖም ሜቴክ ስራውን በሰብ ኮንትራት በማህበር ለተደራጁ ወጣቶች መስጠቱ የሚታወስ ነው።በበርካታ ማህበራት ከተደራጁ ወጣቶች ጋር የ56 ሺህ ሄክታር መሬት ደን ምንጣሮን በ700 ሚሊየን ብር እንዲሰሩለትም ውል አሰሯል። ነገር ግን እነዚህ ማህበራት ስራውን ከሰሩ በሁዋላ ሜቴክ የተመነጠረው መሬት አለካክ ተገቢ አይደለም በሚልና ሌሎች ማስፈራሪያዎች ለማህበራቱ 340 ሚሊየን ብር ቀሪ ክፍያ እንዳልፈጸመና ; በዚህም ሳቢያ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ሄዶ ማህበራቱ በግልጽ በሚታይ የፍርድ ቤቶች ኢ ፍትሀዊ አሰራር በሜቴክ ተሸንፈው ለኪሳራ ተዳርገናል ማለታቸውን ዋዜማ ራዲዮ ከዚህ ቀደም መዘገቧ የሚታወስ ነው።ሜቴክ ለደን ምንጣሮው ስራ ከኤሌክትሪክ ሀይል 2.7 ቢሊየን ብር ቢቀበልም ከሁለት ቢሊየን ብር በላይ የሚሆነውን ገንዘብ የት እንዳደረሰው ግልጽ አይደለም ተብሏል።
የሜቴክ የቀድሞ አመራሮች በተከሱበት ጉዳይም ይኸው ነገር መነሳቱ ይታወቃል።
ከተለያዩ ምንጮቻችን እንደተረዳነው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል የህዳሴው ግድብ አካባቢ የደን ምንጣሮን ውል ሙሉ ለሙሉ ከሜቴክ ነጥቆ የአማራና የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ወጣቶችን ለማሰማራት እየተሰናዳ ነው።የስራው ውልም በቤኒሻንጉልና አማራ ክልል ያሉ ወጣቶችን አደራጅቶ ለመስጠትም ነው የታሰበው።ምንጮቻችን እንዳሉንም ባከነ የተባለው ገንዘብ አስመልክቶ በህግ የሚታይ ይሆናል። የስራውን ውልና ተያያዥ ዝርዝር ጉዳዮችንም ለመጨረስ የሚመለከታቸው አካላት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ስምተናል። [ዋዜማ ራዲዮ]