የሶስትዮሽ ድርድሩ ያለውጤት ተጠናቋል
ዋዜማ ራዲዮ- የከረረ የዲፕሎማሲና የፀጥታ ውዝግብ መንስዔ የሆነው የሕዳሴው ግድብ ውሀ መያዝ መጀመሩንና ወደ ኋላ የማይመለስበት ደረጃ ላይ መድረሱን ዋዜማ ራዲዮ ከተለያዩ ምንጮች አረጋግጣለች።
መንግስት የግድቡን የውሀ ሙሌት መጀመር በይፋ ባይገልፅም ባለፉት ቀናት ግድቡ ውሀ መያዝ መጀመሩንና ወደ ግድቡ እየገባ ያለው የውሀ መጠን የመጀመሪያ ዓመት የግድቡን ሙሌት መጠን ለማሳካት ያስችላል ተብሎ ይገመታል።
ዋዜማ ስለሙሌቱ ባደረገችው ማጣራት ትናንት ሰኞ ሐምሌ ስድስት 2012 የነበረው ወደ ግድቡ የሚገባ የውሀ ፍሰት 4, 400 ሜትር ኪዩብ በሰከንድ የነበረ ሲሆን ከስር ያለው የመፋሰሻ ቱቦ (Culvert box) ደግሞ 1,700 ሜትር ኪዩብ በሰከንድ ገደማ ሲያስተላልፍ ውሏል።
የውሀ ፍሰቱ በየዕለቱ የተለያየ መጠን እንደሚኖረውና በነሐሴ ወር ከአሁኑ የበለጠ የውሀ መጠን ወደግድቡ እንደሚገባም የሜቶዎሮሎጂ ትንበያ ያመለክታል። በሂደትም ግድቡ በመጀመሪያው ዓመት ሙሌት የታቀደውን 4.9 ቢሊየን ሜትሪክ ኪዩብ ውሀ ያሳካል ተብሎ ታምኖበታል።
ግድቡ ውሀ መያዝ የሚያስችለው ከባህር ጠለል በላይ ወይም 560 ሜትር ከፍታ ላይ መድረሱን በቅርቡ በመንግስት በይፋ የገለፀ ሲሆን የሀይድሮ ስቲል (የብረታብረትና መስል ስራዎች) ግንባታም ተጠናቋል።
ግድቡ አሁን ከደረሰበት የግንባታ ደረጃ አንፃር ውሀ ሳይሞላ መቆየት የማይችልበት ተፈጥሯዊ አስገዳጅ ምክንያቶች መኖራቸውን ባለሙያዎች ያብራራሉ።
ግድቡ በሁለት ተርባይኖች የመጀመሪያ የሀይል ማመንጨት ስራውን በቀጣዩ ዓመት መገባደጃ ላይ ይጀምራል የሚል መርሀግብርም ተይዟል።
የዘንድሮው የዝናብ ሁኔታ ለግድቡ ሙሌት የሚያስፈልገውን የውሀ መጠን ለማሟላት የተመቸ መሆኑንና ወደታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት የሚደርሰው ውሀ ላይ ይህ ነው የሚባል መስተጓጎል ሳይፈጠር ለማከናወን እንደሚቻልም ባለሙያዎች አስረድተውናል።
በግድቡ ዙሪያ በግብፅ በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል ሲደረግ የነበረው የምስለ-ድምፅ የርቀት ድርድር ያለ ስምምነት መጠናቀቁን የግብፁ ውጪ ጉዳይ ሚንስትር ሰማ ሽኩሪ ሰኞ ማምሻውን ለሀገራችው ቴሌቭዥን ተናግረዋል።
ዋዜማ ከኢትዮጵያ ወገን እንደሰማችው ግብፅ በድርድሩ ለማሳከት ያሰበቻቸውና ኢትዮጵያ በዓባይ ተፋሰስ ላይ ሌላ ተጨማሪ ግንባታ እንዳታካሂድ የህግ ግዴታ የሚጥል ምክረ ሀሳብ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል። የሕዳሴ ግድብ አስተዳደርና ቁጥጥር ላይ የተደረገው ድርድርም የታሰበውን ውጤት አላስገኘም።
ግብፅ ተገዳ የገባችበትና የአፍሪቃ ህብረት ያመቻቸው ድርድር ከተሰተጓጎለ ጉዳዩን ወደ መንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት መልሳ ለመውሰድ ፍላጎት ቢኖራትም ከቅርብ አጋሮቿ ጭምር ጉዳዩ ወደ ፀጥታው ምክር ቤት እንዳይሄድ ተመክራለች።
በፀጥታው ምክር ቤት ተደርጎ በነበረው የመጀመሪያ ክርክር ምክር ቤቱ የመሰረተ ልማት ጉዳዮችን ውዝግብ ማየት ከጀመረ ማለቂያ የሌላቸው ጉዳዮች ወደ ድርጅቱ እንደሚመጡና ይህም ከተቋቋመበት ዓላማ ያፈነገጠ መሆኑን ኢትዮጵያ በአምባሳደሯ ታዬ ዐፅቀሥላሤ አስረድታለች። የመንግስታቱ ድርጅትም ጉዳዩ በአፍሪቃ ህብረት ሸምጋይነት መታየቱን ደግፎ ከኢትዮጵያ አቋም ጋር ተስማምቷል። [ዋዜማ ራዲዮ]
To reach Wazema Radio Editors you can write to wazemaradio@gmail.com