Sileshi Bekele (Phd) MoWE and Chief #GERD Negotiator

ከ31 ቢሊየን ሜትሪክ ኪዩብ ማለፍ የለብንም ይላሉ ባለሙያዎች፣ የድርድሩ ቡድን መሪ የተለየ ሀሳብ አላቸው

ዋዜማ ራዲዮ- አሜሪካ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውሀ አሞላልና አለቃቅ እንዲሁም በድርቅ ማካካሻ ላይ ኢትዮጵያ ግብጽና ሱዳንን ለማደራደር የሄደችበት መንገድ ችግር ከገጠመው በኋላ ኢትዮጵያ በራሷ የስምምነት ሰነድ እያዘጋጀች መሆኑ ተነግሯል። በፈረንጆቹ አቆጣጠር የካቲት ወር መጨረሻ ይፈረምበታል የተባለው ሰነድ ከመፈረም የተረፈው የኢትዮጵያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው በራሳቸው ተነሳሽነት ወደ ዋሽንግተን ለዚህ ጉዳይ አልሄድም በማለታቸው መሆኑን ዋዜማ ራዲዮ ሰምታለች። አሜሪካ ያዘጋጀችው የስምምነት ሰነድ ላይ ኢትዮጵያ አልፈርምም ማለቷ ተገቢ ውሳኔ በመሆኑ ከበርካታ ዜጎች ይሁንታን አግኝቷል።


አሁንም ግን በኢትዮጵያ በኩል እየተዘጋጀ ነው የተባለው የታላቁ ህዳሴ ግድብ የውሀ አያያዝና አለቃቀቅ ሰነድ ላይም እየተነሱ ያሉና መስተካከል ያለባቸው ይዘቶች እንዳሉ ዋዜማ ራዲዮ ለሙያው ቅርብ ከሆኑ ምንጮቿ ሰምታለች። በነዚህ ይዘቶች ላይም በውሀ መስኖና ኤነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለና በተዋቀረው የተደራዳሪዎች ቡድን መካከል ክርክሮች እንዳሉ መረዳት ችለናል።

ዝቅተኛው የመደራደሪያ ነጥባችን የቱጋ ነው?

ዋናው የክርክሩ መነሻም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውሀ በሚሞላበት ጊዜ በየአመቱ በትንሹ መልቀቅ ያለበት የውሀ መጠን ነው። አብዛኞቹ የሰነዱ አዘጋጅ የድርድሩ አባላት የህዳሴው ግድብ በሚሞላበት ጊዜ በየአመቱ ወደ ታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት መለቀቅ አለበት የሚሉት የውሀ መጠን 31 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ እንዲሆን ነው ሀሳብ ያቀረቡት። የውሀ መስኖና ኤነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ ደግሞ ግድቡ በሚሞላበት ጊዜ አመታዊ ፍሰቱ 37 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ይሁን የሚል አቋም ነው ያላቸው። ሚኒስትሩ በሚሰጧቸው መግለጫዎችና ቃለ መጠይቆች ይህንን የፍሰት መጠን ደጋግመው ሲያስምሩበትና ከግብጽ ጋር መቀራረብ የተፈጠረበት ነው እያሉ ደጋግመው ሲያነሱ ይሰማሉ።

የሶስትዮሽ የድርድር ሂደቱን በቅርበት የሚያውቁ የዋዜማ ምንጮች እንደነገሩን ግን ከሆነ ኢትዮጵያ ግድቡን ስትሞላ በየአመቱ ወደታችኛው ተፋሰስ ሀገራት በትንሹ እንዲለቀቅ መስማማት ያለባት 31 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሀ እንጂ ከዚህ በላይ ወይንም እንደሚባለው 37 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ በፍጹም መሆን የለበትም። በግድቡ ውሀ አያያዝ ላይ ኢትዮጵያ እያዘጋጀችው ያለው ሰነድም በግድቡ አሞላል ወቅት ስለሚለቀቀው ውሀ ሲጠቅስ 31 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ላይ ነው መጽናት ያለበት ብለው ያምናሉ።


እንደ ባለሙያዎቹ አስተያየት ይህ አቋም ታሪካዊ ድጋፍ አለው።በኢትዮጵያ ከ1977 አ.ም ጀምሮ ለተወሰኑ አመታት ድርቅ ሲከሰት የአባይ ውሀ አመታዊ ፍሰት 31 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ነበር።ይህም በአንጻሩ በቅርብ አመታት የተከሰተ ድርቅ የአባይ ውሀ ፍሰት ምን ያክል እንደሚወርድ ያሳየ ነው።የአባይ ውሀ ፍሰት 31 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ድረስ ቢወርድም ግብጽ ላይ በወቅቱ የተለየ ተጽእኖ አለማሳረፉ ተረጋግጧል። ይልቁንም በወቅቱ የተከሰተው ድርቅ ኢትዮጵያን መጉዳቱ ነው የሚታወሰው።

ዝቅተኛ አመታዊ ፍሰት ድርቅ እንኳ ቢከሰት የሚለቀቀውን ውሀ የሚያሳይ እንደመሆኑና ከዚህ ቀደም በድርቅ ሳቢያ በነበረ የ31 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ፍሰት ግብጽ የተለየ ችግር ስላላጋጠማት የኢትዮጵያ ሰነድም ማካተት ያለበት ይሄንኑ ቁጥር መሆን አለበት ነው የተባለው።

37 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ በሚለው መስማማት ግን ፣ የውሀው ፍሰት ግድቡ በሚሞላበት ጊዜ ዝቅ ቢል የህዳሴው ግድብ አሞላል ላይ ከፍተኛ መዘግየትን ያስከትላል። ለአብነት ውሀው በሚሞላበት የሆነ አመት ላይ የአባይ ወንዝ ፍሰት 40 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ቢሆን ኢትዮጵያ 37 ቢሊየን ሜትር ኪዩብን ለመልቀቅ ብትስማማ ሶስት ቢሊየን ሜትር ኩዩብ ውሀ ነው በዚያ አመት መያዝ የምትችለው። ይህ ደግሞ የግድብ አሞላል ጊዜን በእጅጉ የሚያራዝም ይሆናል። ስለዚህ የዚህ ቁጥር አወሳሰን ላይ ጥንቃቄ ያስፈልጋል።ግብጽ ግድቡ በሚሞላ ጊዜ ከፍ ያለ መጠን ውሀ ይለቀቅልኝ የምትለው ግድቡ ቶሎ እንዳይሞላ ነው።

ተስማምተን እንጨባበጥ!


የውሀ መስኖና ኤነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ 37 ቢሊየን ሜትር ኩዩብ ላይ የቆሙበት ምክንያት መነሻ እንዳለው ነው የሰማነው።አሜሪካና የአለም ባንክ የሶስትዮሽ ድርድር ውስጥ ገብተው አራት ስብሰባዎች እንዲደረጉ ሲወሰን ግብጽ ግድቡ ሲሞላ በየአመቱ 40 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ይለቀቅልኝ የሚል አቋም ላይ ነበረች።ኢትዮጵያ ደግሞ 31 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ላይ። ታድያ ካርቱም ላይ የሱዳኑ ተወካይ በኢትዮጵያና ግብጽ መሀል ገብተው አማካዩ ላይ ማለትም በ35 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ አመታዊ ፍሰት ላይ እንዲስማሙ ያደርጋሉ። የግብጹ የውሀ ሚኒስትር መሀመድ አብደል አቲ ግን የድርድር ቡድኔ በ35 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ አልስማማም አለኝ ብለው ሀሳባቸውን ቀይረው መጡ።

ታህሳስ 29 እና 30 2012 አ.ም አዲስ አበባ ላይ የቀጠለው ስብሰባ ላይ ይኸው ንትርክ አልቋጭ ስላለ የኢትዮጵያው ውሀ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ ከመቀመጫቸው ተነስተው “በ37 ቢሊየን ሜትር ኩብ ተስማምተን እንጨባበጥ : ይሄን ሀሳቤን የኔ ቡድን ባይቀበለኝም ግን እንስማማ ” ይላሉ። ግብጾች 37 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ አመታዊ ፍሰትን አንቀበልም አሉ። ይሄም የመጣው በኢትዮጵያ በኩል የአቋም መለሳለስ በተደጋጋሚ ስለታየ ግብጾች ይበልጥ የአቋም መለሳለስ እንዲኖር በመጠበቃቸው ነው።

የኢትዮጵያ ውሀ መስኖና ኤነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለም ይህ ቁጥር ላይ የቆሙትም ሀገሪቱ በታዛቢዎች ፊት የያዘችው አቋም በመሆኑ ሀሳብ መቀየሩ ተገቢ አይደለም ብለው ስላሰቡ መሆኑን ሰምተናል።ሆኖም ግብጾች እያሳዩ ካለው ተለዋዋጭነት አንጻር ይሄ እዚህ ግባ ሊባል የማይችልና በተለያዩ መንገዶች በቀላሉ ኢትዮጵያ አቋሟን ወደ ሚጠቅማት 31 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ማምጣት ትችላለች ብለውናል ምንጮቻችን።

ከዝቅተኛ የመደራደሪያ ነጥብ መነሳት ጉዳት አለው

የጉዳዩን ፖለቲካዊነት የበለጠ የተገነዘቡ የድርድር ቡድኑ አባል በዚህ ሳምንት ለዋዜማ እንዳስረዱት ” በድርድር ላይ አቋም መቀያየር ተዓማኒነትን ይቀንሳል። ይሁንና ግብፆች ከያዙት የእጅ ጥምዘዛ አንፃር ከዝቅተኛ የመደራደሪያ ነጥብ መነሳት ጉዳት አለው።
ማንም ሊረዳው የሚገባው ግን በዲፕሎማሲም ሆነ በድርድሩ የተሻለ የመደራደር ቁመና ያለት ኢትዮጵያ ናት። ይህን ሳንጠቀም ብንቀር ጉድለቱ የኛ ነው” ይላሉ ተደራዳሪው።
ድርድሩ ቴክኒካዊ እንዲሆን እንፈልግ ነበር፣ በቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ ጥሩ ቁመና አለን። አሁን ግን ጉዳዩ የፖለቲካ መልክ ስለያዘ ተለዋዋጭ ባህሪያት እንዳሉት ባለሙያው አስረድተውናል።


የህዳሴው ግድብ አንዴ ከተሞላ በሁዋላ በሚኖረው የረጅም ጊዜ የግድቡ ኦፕሬሽን ወቅት በየአመቱ የሚለቀቀው ውሀም ከዚህ ቀደም ሊፈረም ተቃርቦ እንደነበረው ሰነድ ኢትዮጵያን በተለያዩ ቁጥሮች ግዴታ ውስጥ የሚጥል ሳይሆን ግድቡ አንዴ ከሞላ በሁዋላ የሚኖር ትነትና ለሀገር ውስጥ የወደፊት ተጠቃሚዎች ሊውል የሚችለው ተቀናንሶ የተለያዩ ሁኔታዎችንም አገናዝቦ በመቶኛ ብቻ ነው መቀመጥ ያለበት ።

የአዘጋጁ ማስታወሻየሕዳሴው ግድብን በተመለከት ከሀገራችን በኩል ያሉትን ሁሉንም መረጃዎች ለማቅረብ የጉዳዩ ስሱነትና ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት ከግንዛቤ በማስገባት የተወሰነውን እዚህ ማቅረብ አልቻልንም። እንደምትረዱን ተሰፋ እናደርጋለን። [ዋዜማ ራዲዮ]

To reach Wazema Editors you can write to an email wazemaradio@gmail.com